የመብት ጥሰትን የመከላከል ጥረት በደቡባዊ ኢትዮጵያ ክልሎች
ቅዳሜ፣ ሰኔ 21 2017
የኢትዮጵያ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዘው በዜጎች ላይ የሚከሰት የመብት ጥሰትን በጋራ ለመከላከልና ለማረም ያስችለኛል ያለውን ሥምምነት ከሦስት ክልላዊ መንግሥታት ጋር ትናንት በሀዋሳ ተፈራርሟል፡፡ ተቋሙ ሥምምነቱን ያካሄደው ከሲዳማ ፣ ከማዕከላዊ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥታት ጋር ነው ፡፡ ስምምነቱ የደሞዝ እና የይዞታ መፈናቀልን ጨምሮ በክልሎቹ የሚስተዋሉ የመብት ጥሰት አቤቱታዎች ላይ በቅንጅት ለመሥራት እንደሚያስችል የተቋሙ ሃላፊዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡
በወላይታ ዞን የመምህራን ደሞዝ አሁንም አልተከፈለም ፤ ትምህርትም አልተጀመረም
በክልሎቹ የሚስተዋሉ የመብት ጥሰቶች ምን አይነት ናቸው ?
አቶ አስረስ ግዛው በኢትዮጵያ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የሀዋሳ ቅርንጫ ጽህፈት ቤት ተጠባባቂ ሃላፊ ናቸው ፡፡ አቶ አስረስ እንደሚሉት በሦስቱ ክልሎች በየዓመቱ የመብት ጥሰት ተፈጸመብን ያሚሉ በርካታ ዜጎች ለተቋሙ አቤቱታቸውን ያቀርባሉ ፡፡ አቤት ባዮች ይዘው የሚቀርቡት ጉዳይ የተለያየ መሆኑን የጠቀሱት ተጠባባቂ ሃላፊው “ ከእነኝህም መካከል የደሞዝ አለመከፈል ፣ ከተከፈለም ያለሠራተኞች ይሁንታ መቁረጥ ፣ እንዲሁም ከይዞታ መፈናቀልና ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ አቤቱታዎች ይገኙበታል ፡፡ ይህ ሥምምነት እነኝህን አቤቱታዎች ከክልል መንግሥታት ጋር ተቀራርቦ ለመፍታት ያስችላል “ ብለዋል ፡፡
የመብት ጥሰትና የተወካዮች ም/ቤት ቋሚ ኮሚቴ ዉሳኔ
የመብት ጥሰቶች በትምህርቱ ዘርፍ ላይ
በደቡብና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ከደሞዝ ክፍያ አለመፈጸም ጋር በተያያዘ በርካታ አቤቱታዎች ሲቀርቡ፣ ዶቼ ቬሌም በተደጋጋሚ ቅሬታዎቹን ሲዘግብ ቆይቷል፡፡ በተለይም የመብት ጥሰቱ ጎልቶ በሚታይበት በትምህርት ዘርፉ ላይ የተወሰነ መሻሻል መኖሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አማኑኤል ጳውሎስ ይናገራሉ ፡፡ ነገር ግን አሁንም ያልተፈቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ለዶቼ ቬለ አስተያታቸውን የሰጡት የማህበሩ ፕሬዝዳንት “ በ2017 ዓ.ም መምህራን ሙሉ ደሞዝ የማግኘት ሁኔታ መሻሻል አሳይቷል ፡፡ ነገር ግን አሁንም በርካታ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ይስተዋላሉ ፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ ከፍቃዱ ውጭ ደሞዝን የመቁረጥ ፣ የትምህርት ማሻሻያ የሚፈቅደውን ክፍያ አለመፈጸም ፣ ከፍላጎት ወጭ ዝውውር ማድረግ ይጠቀሳሉ “ ብለዋል ፡፡
የሥምምነቱ ተስፋ
የኢትዮጵያ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ከክልሎቹ ጋር ያደረገው ስምምንት በጎ እርምጃ መሆኑን የተናገሩት የማህበሩ ፕሬዝዳንት “ በሥምምነቱ መሠረት መሥራት ከተቻለ ለመምህራንም ሆኑ ሌሎች ሠራተኞች ላይ ለሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል ያስችላል ፡፡ ተፈጽመው ሲገኙም በፍጥነት ለማረም ያስችላል የሚል ተስፋ አለኝ ፡፡ በተለይም አብዛኛው ጥሰት የሚፈጸመው በወረዳ መዋቅሮች ላይ ነው ፡፡ የተቋሙ እና የክልል መንገሥታቱ ተቀራርቦ መሥራት እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅሮች በመውረድ ጥሰቶችን በቅንጅት ለመፍታት ዕድል ይፈጥራል “ ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ