1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመተከል ጥቃት፤ የኢሰመጉ መግለጫ እና የነዋሪዎች ስጋት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 5 2015

ኢሰመጉ ዛሬ ሐምሌ 5/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በወቅቱ የመንግስት ጸጥታ ሐይሎች ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ በቅርብ ርቀት ላይ በካምፕ ውስጥ የነበሩ ቢሆንም አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠቱን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓርብ በግልገል በለስ ከተማ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ነዋሪዎች ስጋት ገብቷቸዋል።

Äthiopien Gilgel Beles
ምስል Negassa Desalegn/DW

የግልገል በለሱ ጥቃት ሌላ ስጋት ደቅኗል

This browser does not support the audio element.

ሰኔ 30/2015 ዓ.ም በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ አስታወቀ፡፡ ኢሰመጉ ዛሬ ሐምሌ 5/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በወቅቱ የመንግስት ጸጥታ ሐይሎች ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ በቅርብ ርቀት ላይ በካምፕ ውስጥ የነበሩ  ቢሆንም አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠቱን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓርብ በግልገል በለስ ከተማ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ነዋሪዎች ስጋት ገብቷቸዋል። አንዳንዶቹ ወደ አጎራባች ወረዳዎች ለመሰደድም ተገደዋል። በክልሉ በተለይም በተከታታይ ጥቃቶች በሚፈጸሙባቸው አካባቢዎች በቂ የሆነ የጸጥታ ሐይል ባለመሰማራቱ ምክንያት ሰዎች ለጥቃት ሲጋለጡ እና በነጻነት እንዳይኖሩ ምክንያት መሆኑንም የኢሰመጉ መግለጫ ያመለክታል፡፡ በክልሉ በታጠቁ ቡድኖች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኙ ይገባል ብለዋል፡፡13 ሰዎች በግልገል በለስ ከተማ ተገደሉ

መንግስት የህዝቦችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በመወጣት በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት ከህግ ፊት እንዲቀርቡም አሳስቧል፡፡ ኢሰመጉ በአካባቢው የደረሰውን የጉዳት መጠን በዝርዝር በመግለጫው አልጠቀሰም፡፡ በክልሉ መንግስት በኩል ዛሬም ስለ ግልገል በለስ ጥቃት የተባለ ነገር የለም፡፡ ከመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ለሜሳ ዋቅወያ እና ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረኩት ጥረት አልተሳከም፡፡

ምስል DW/N. Dessalegn

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ መግለጫ እንደሚያመለክተው  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች በህጻናት፣ ሴቶችና አዛውንቶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽመዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት አርብ ታጣቂዎቹ በግልገል በለስ ከተማ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ሲሉ አካባቢውን ለቀው መፈናቀላቸውን ኢሰመጉ በመግለጫው አመልክቷል፡፡ በግልገል በለስ 01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ ከቅዳሜ ጀምሮ ከ1 ሺ በላይ ሰዎች ወደ አጎራባች ወረዳ ፓዌ መሰደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎች እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ ባገኙት አጋጣሚ ወደ አጎራባች ከተሞች በመሸሽ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡በመተከል ዞን የቀጠለው የነዋሪዎች ቅሬታ

ባለፈው ዓርብ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ካደረሱ ወዲህ ለህግ አለመቅረባቸውን ሌላው የከተማው ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ አራት ሰዓት ገደማም በከተማ ውስጥ ሲንቀሰቃሱ ማየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ትጥቅ ባለመፍታታቸው  ዛሬም ብዙ ቁጠር ያላቸው ነዋሪዎች በስጋት ምክንያት ወደ ጃዊ፣ቻግኒ እና መንደር 7 ወደ ተባሉ ቦታዎች መፈናቀላቸውን ተናግረዋል፡፡በመተከል ዞን የተቀሰቀሰ ግጭትና የደረሰ ጥቃት

በመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ ውስጥ ባለፈው ሳምንት አርብ በታጣቂዎች በደረሰው ጥቃት ከ10 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የክልሉ መንግስት በክልሉ ለሚኖሩ ሰዎች ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ በተደጋጋሚ በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እንዲያስቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡ በተጨማሪም ሰኔ 30/2015 ዓ.ም በግልገል በለስ ከተማ በነዋሪው ላይ ጥቃት የፈጸሙ አካላት ማንነት በማጣራት በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡   

ነጋሳ ደሳለኝ

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW