1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመታመኛ ድምጽ የተነፈጉት መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና መጪው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2017

ሾልዝ የመታመኛ ድምጽ እንደማያገኙ በሰፊው የተጠበቀ ነበር። ይህም ጥምር መንግስታቸው ሲፈርስ ለጎርጎሮሳዊው የካቲት 23 ለታቀደው አጠቃላይ ምርጫ መንገድ ጠርጓል። አሁን ትልቁ ሃላፊነት የሚወድቀው ምርጫውን በሚመራው በምርጫ ኮሚሽን ላይ ነው። ሾልዝ የመታመኛ ድምጹን ካጡ በኋላ የጀርመን ፕሬዝዳንት ሽታይንማየር ፓርላማውን እንዲበትኑ ጠይቀዋል።

መራኄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እንዲያፈርሱ ሲጠይቁ
መራኄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እንዲያፈርሱ ሲጠይቁ ምስል John MacDougall/Pool Photo/AP/picture alliance

የመታመኛ ድምጽ የተነፈጉት መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና መጪው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ

This browser does not support the audio element.

ጥምር መንግሥታቸው የፈረሰው የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የመታመኛ  ድምጽ እንዲሰጣቸው ትናንት ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ሆኖባቸዋል። 

«የተሰጡት 717 የምርጫ ካርዶች ናቸው ፣ 207ቱ የድጋፍ፣ 394 የተቃውሞ እንዲሁም 116 ድምፀ-ተዐቅቦ ናቸው። ለዴፈራል ምክር ቤቱ የመታመኛ ድምጽ ማረጋገጫ ቢያንስ 367 ድምጽ ማግኘት ይጠበቃል። የፌደራሉ መራኄ መንግሥት ያቀረቡት ጥያቄ የሚያስፈልገውን 367 ድምጽ  አላገኘም። ይህን ለፌደራል ጀርመን ፕሬዝዳንት ሳልዘገይ አሳውቃለሁ። »

የጀመርን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ባርብል ባስ ነበሩ ፣ የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የፌደራል ጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመታመኛ ድምጽ እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄ በቂ ድምጽ እንዳላገኘ ከድምጽ አሰጣጡ በኋላ ትናንት ያሳወቁት። ሾልዝ የመታመኛ ድምጽ እንደማያገኙ በሰፊው የተጠበቀ  ነበር።  ይህም የመሰረቱት ጥምር መንግሥት ከአንድ ወር በፊት ሲፈርስ ለመጪው ጎርጎሮሳዊው የካቲት 23 ለታቀደው አጠቃላይ ምርጫ መንገድ ጠርጓል።

አዲሱ የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ማናቸው?

ሾልዝ የመሰረቱት ሦስት ፓርቲዎች የተጣመሩበት መንግሥት የፈረሰው የጥምሩ መንግሥት አካል የነበረው የለዘብተኛው የነፃ ዴሞክራቶች ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር FDP መሪ ክርስቲያን ሊንድነር ሾልዝ ለሀገሪቱ ያስፈልጋታል ባሉት ብድር ባለመስማማታቸው ፓርቲው ከጥምሩ መንግሥት ከወጣ በኋላ ነው።ይህም የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ (SPD) እና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ከFDP ጋር ተጣምረው ሀገሪቱን በመሩባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት በፓርላማው የነበራቸውን አብላጫ ድምጽ አሳጥቶ እስከ አጠቃላዩ ምርጫ ድረስ አናሳ መንግሥት ሆነው እንዲቀጥሉ አድርጓል። ሾልዝ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የመታመኛ ድምጽ ጥያቄ ላይ  አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የሕግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ሶልሽ የመታመኛ ድምጹን እንደማያገኙ አስቀደምውም ያውቁ ነበር ብለዋል።

ሽታይንማየር ከቤልቭዩ ቤተ መንግሥት ቅጽር ግቢ ውጭምስል Annegret Hilse/REUTERS


 
ዶክተር ለማ እንደሚሉት ከአሁን በኋላ ትልቁ ሃላፊነት የሚወድቀው ምርጫውን በሚያስፈጽመው በጀርመን የምርጫ ኮሚሽን ላይ ነው። ሾልዝ የመታመኛ ድምጹን ካጡ በኋላ የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ፓርላማውን እንዲበትኑ ትናንትናውኑ ሀሳብ አቅርበውላቸዋል። ፕሬዝዳንት ሽታይንማየርም በሃሳቡ መስማማታቸውን እና አዲስ ምርጫም ለመጥራት በ21 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለባቸው። በፌደራል ጀርመን መንግሥት ታሪክ አንድ መራኄ መንግሥት የጀርመን ምክር ቤት የመታመኛ እንዲሰጠው ሲጠየቅ የትናንትናው ለስድስተኛ ጊዜ ነው። ጥያቄው የሚቀርበውም በጀርመን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 68 መሠረት ነው።

በጀርመኖቹ በዛክሰን አንሀልት እና ቱሪንገን ፌደራዊ ግዛቶች የተካሄደው ምርጫ ውጤትና መዘዙ
ፓርላማው በተበተነ በ60 ቀናት ውስጥ ምርጫ መካሄድ አለበት።  ሾልዝ ትናንት ለምክር ቤቱ እንዳስታወሱት ከርሳቸው የቀደሙት ሁለት መራኅያነ መንግሥት የምክር ቤቱን ድጋፍ ለማግኘት የመታመኛ ድምጽ ጠይቀው ነበር። ሌሎቹ ሦስት መራኅያነ መንግሥት ቪሊ ብራንት ፣ ሄልሙት ኮልና ጌርሀርድ ሽሮደር ግን በአንቀጽ 68 መሠረት አዲስ ምርጫ እንዲጠራም ነበር የጠየቁት። የኔም ግብ ተመሳሳይ ነው ብለው ነበር ሾልዝ። በዚህ ምርጫ ዜጎች የሀገራችን የፖለቲካ አካሄድ እንዲወስኑ እንደሚፈልጉም ተናግረው ነበር። በፌደራል ጀርመን  ወቅቱን ያልጠበቀ የምክር ቤት ምርጫ የተካሄደው ሦስት ጊዜ ነው። ይኽውም በጎርጎሮሳዊው 1972 ፣1983 እና በ2005 ዓ.ም. ነው።

ሾልዝ የጀርመን ምክር ቤት አባላትን የመታመኛ ድምጽ ሲጠይቁ ምስል Kay Nietfeld/dpa/picture-alliance

የመጀመሪያው ከነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ FDP ጋር ጀርመንን ይመሩ የነበሩት የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ የSPD መሪ ቪሊ ብራንት  በ1972 የመታመኛ ድምጽ እንዲሰጣቸው ምክር ቤቱን ከጠየቁ በኋላ የተጠራው ምርጫ ነው። የዚህ ምክንያቱም በወቅቱ ቀዝቃዛው ጦርነት ባስከተለው መሰነጣጠቅ በምክር ቤቱ የSPD እና የFDP አባላት ከምክር ቤቱ ለቀው መውጣት መጀመራቸው  መንግሥታቸውን አብላጫ ድምጽ እያሳጣ መሄዱ ነበር። ያኔ  4ተኛው የጀርመን መራኄ መንግሥት ቪሊ ብራንት መታመኛ ድምጽ ባለማግኘታቸው በህዳር 1972 በተጠራው ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ ዳግም ተመመርጠዋል። ከመራጩ ህዝብ 91.1 በመቶው ድምጽ በሰጠበት በዚህ ምርጫም ፓርቲያቸው SPD ያገኘው 45.8 በመቶ ድምጽ እስከዛሬ ፓርቲው በምርጫ ያሸነፈው ከፍተኛው የህዝብ ድምጽ ሆኗል።

በጀርመኖቹ በዛክሰን አንሀልት እና ቱሪንገን ፌደራዊ ግዛቶች የተካሄደው ምርጫ ውጤትና መዘዙ
ስድስተኛው የጀርመን መራኄ መንግሥት ሄልሙት ኮልና ተጣማሪያቸው FDP ስልጣን የያዙት በ1983 በተጠራ ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ ነበር ።ይህ የሆነውም የያኔው መራኄ መንግሥት ሶሻል ዴሞክራቱ ሄልሙት ሽሚት  በ1982 የመታመኛ ድምጽ ካጡ በኋላ ነበር።ይህም በጀርመን ሁለተኛው ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ ነው።የምርጫው ሂደት ቢያወዛግብም  መንግስታቸው በምክር ቤቱ አብላጫ ድምጽ በመያዙ ሊቀጥል ችሏል።

ሾልዝ የጀርመን ምክር ቤት አባላት የመታመኛ ድምጽ ከነፈጓቸው በኋላ ምስል Lisi Niesner/REUTERS


ሶስተኛው ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ ደግሞ በጎርጎሮሳዊው 2005 ዓም ነበር የተካሄደው። ያኔ የSPDው ጌርሃርድ ሽሮደር ከአረጓዴዎቹ ፓርቲ ጋር የመሰረቱትን ጥምር መንግሥት ነበር የሚመሩት። «አጀንዳ 2010» በተባለው በሽሮደር አወዛጋቢ የተሀድሶ እቅድ ምክንያት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፓርቲያቸው የሚሰጠው ድጋፍ በመቀነሱ የመታመኛ ድምጽ እንዲሰጣቸው ሽሮደር ጠየቁ። ይህም ሳይሳካላቸው ቀርቶ አዲስ ምርጫ ሲጠራ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ የCDU እጩ አንጌላ ሜርክል  ተመርጠው ለ16  ዓመታት ጀርመንን መርተዋል።

ከሁለት ወራት በኋላ በሚካሄደው ወቅቱን ያልጠበቀ የጀርመን ምርጫ ማን እንደሚያሸንፍ ከወዲሁ እርግጠኛ ሆኖ ለመገመት ቢያስቸግርም በህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች መሠረት ተቃዋሚው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ በጀርመንኛ ምህጻሩ  ሴ .ዴ. ኡ. ሊያሸንፍ ይችላል የሚል ግምት አለ። ቀኝ ጽንፈኛው «አማራጭ ለጀርመን»ና ግራ ጽንፈኛ የሚባለው አዲሱ ሳራ ቫግንክኔሽት ኅብረት ደግሞ ከእስካሁኑ የተሻለ ድምጽ የማግኘት እድል አላቸው እየተባለ ነው። 

 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW