1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

የመነመነዉ ስራ የማግኘት ተስፋ

ዓርብ፣ ሐምሌ 21 2015

ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘንድሮም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች እየተመረቁ ይገኛሉ። ይሁንና ስራ የማግኘት እድላቸው አጠያያቂ ነው። «ተማሪውን የሚያስጨንቀው ሥራ አገኛለሁ ወይ የሚለው ሳይሆን ቤተሰቤን ተመርቄ እንዴት አስደስታለሁ የሚለው ነው። » ይላል ከተመራቂዎቹ አንዱ ለዶይቸ ቬለ።

Äthiopien | Hauptcampus der Universität Addis Abeba
ምስል Solomon Muchi/DW

የተንጨላጨለ ስራ የማግኘት ተስፋ

This browser does not support the audio element.

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ባለፈው ሳምንት  በተለያየ መርሐ ግብር ያስተማራቸውን 8,642 ተማሪዎች አስመርቋል።  ቴዎድሮስ ቀና ከአዲስ አበባ በህግ ሙያ በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ ተማሪዎች አንዱ ነው። « ደስታው ለኛ ለምንመረቀው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቻችን ለዘመዶቻችን ነበር።»

እንደ ቴዎድሮስ ከአዲስ አበባ ነገር ግን በጋዜጠኝነት እና ኮሚኒኬሽን የተመረቀችው ነፃነት አየነውም የምረቃ ስነ ሥርዓቱን ወደዋለች። « የክፍለ ሀገር ልጅ ነኝ እና ቤተሰቦቼ መጥተው በደንብ አከበርን፤ ሚሊኒየም አዳራሽ ነበር የተመረቅነው። እዛም የነበረው ፕሮግራም ቆንጆ ነበር» ትላለች።

በተመሳሳይ ዕለት -  ሐምሌ 13 ቀን  ተማሪ ናትናኤል አማረም  ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በኪነ ህንፃ ተመርቋል። ወደፊት ስራ የማግኘት እድሉ በጣም ስለሚያሰጋው ከራሱ ይልቅ በመመረቁ የሚደሰተው ለወላጆቹ ሲል ነው። «  ሀገር ሰላም ስላልሆነ እንደልባችን ተዘዋውረን ለመስራት ሞራል የለንም። እንደው ቤተሰብ ደስ ይበለው ብለን ነው እንጂ ሀገሬ ላይ ሰርቼ ተለውጬ የሚለው ሀሳብ በአጠቃላይ ሞቷል። እና ተስፋ አስቆራኝ ነው »

የ25 ዓመቱን  ናትናኤል  ከምንም በላይ ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረገው ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ ም በፓርላማ በተካሄደ መደበኛ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተናገሩት ነገር ነው። በዚህም መሠረት  ለ2016 ዓ.ም. የበጀት ዓመት የተያዘው አጠቃላይ የበጀት መጠን ለሚፈለጉ የልማት ሥራዎች በቂ ባለመኾኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደማይጀመሩ እና የአዲስ መንግሥታዊ ሠራተኞች ቅጥርም እንደማይፈጸም አስታውቀዋል፡፡ በዚህ አነጋጋሪ ሆኖ በሰነበተው የአዲስ ሰራተኞች ቅጥር ጉዳይ ላይ  ከ14 ቀን በኋላ ማብራሪያ የሰጡበት የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት የአዲስ ሰራተኛ ቅጥር እንዳይኖር የተደረገው የሀገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ ለማሻሻል በመታሰቡ ነው። መንግሥት ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ለዜጎቹ ሥራ መፍጠር ግዴታው እንደሆነ የህግ ምሩቁ ቴዎድሮስ ይናገራል። « አንደኛ የመንግሥት ስራ እንዲሰራ ከተፈለገ መንግሥት ሰዎችን መቅጠር አለበት። በምንም መንገድ የሰራተኛ እጥረት ሊኖር አይገባም። ይኼ ከመንግሥት ጥቅም አንፃር ነው። ከተመራቂዎች ጥቅም አንፃር ደግሞ አንድ ሰው ከተማረ በመንግሥትም ይሆን በተለያየ መንገድ ስራ ማግኘት አለበት።»

በጋዜጠኝነት የተመተቀችው ነፃነት እንደ ናትናኤል ተስፋዋ አልተሟጠጠም። ስራ ለማፈላለግ ብላ እዛው የተማረችበት  አዲስ አበባ ከተማ የምትገኘው ይህቺው የ 22 ዓመት ወጣት ግን በጥቂት ቀናት  የተረዳችው ፍለጋው ቀላል እንደማይሆን ነው። « እያፈላለኩኝ ነው። ሥራ የሚወጣባቸው ሊንኮችን እየተጠቀምን ከጓደኞቼ ጋር እያፈላለግን ነው።  ግን እስካሁን የሚወጡ ማስታወቂያዎች የስራ ልምድ ይጠይቃሉ።»

መውጫ ፈተና ተፈታኞች ሐዋሳምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ነፃነት ጋዜጠኝነት  ፈልጋ የተማረችው የትምህርት ዘርፍ ነው። « እንደአጋጣሚ ሆኖ እኛ የገባንበት አመት ዲፓርትመንታችንን ራሳችን ነበር የምንመርጠው እንጂ በውጤት አልነበረም።» ትላለች። ሌላዋ ምሩቅ ኢማን ጀማል ትባላለች። ከወላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የተመረቀችው  መማር በፈለገችው የውኃ አቅርቦት ጥናት ነው።  ይሁንና በዚህ ዘርፍ ስራ ማግኘቷ ያጠራጥራታል። « አሁን ባለው ሁኔታ ሀገራችን ላይ ስራ ማግኘት በጣም ከባድ ነው።አሁን ተመርቄ አሁን ላገኝ አይደለም ። ከአመት በፊት ተመርቀው ስራ ያላገኙም አሉ።»

አንዳንድ የ2015 ዓም ተመራቂዎች ራሳቸውን ከሌላ አመት ተመራቂዎች ጋር ሲያነፃፅሩ ገና ከ12 ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አንስቶ  እስኪመረቁ ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች  ከባድ ጫና እንደገጠማቸው ይናገራሉ።  ኢማን ይህን አስተያየት ምክንያቶችን በመዘርዘር ትጋራለች።«  ኮቪድም ነበር፤ አንዳንድ እረብሻዎችም ነበሩ። ያንን ሁሉ አልፈን መጨረሻ ላይ የመውጫ ፈተና የሚለው መጣ። ይኼ ሁሉ ጫና ከባድ ነበር። ከኮቪድ በኋላ የአንድ ሴሚስቴር ትምህርት በ 43 ቀን መጨረስ ነበረብን። እና ያልተማርናቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። »

ኢትዮጵያ ውስጥ ከግል ዘርፉ ይልቅ ሰራተኞችን በመቅጠር ደረጃ ቀዳሚነቱን ቦታ የሚይዙት የመንግሥት ተቋማት ናቸው። እንደዚያም ሆኖ የህግ ምሩቁ ቴዎድሮስ መንግሥት ባይቀጥረውም እንኳን በተማረበት ዘርፍ በግል ድርጅትም ስራ የማፈላለግ ዕድል አለው። « በመንግሥት ደረጃ ቅጥር የለም የሚል ነገር ሰምተናል። ይህ እኛን የሚያካትት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ። ሁለተኛው አማራጭ በግል ደረጃ በተለያዩ ለምሳሌ ባንኮች ውስጥ፤ ወይም ሌሎች ተቋሞች ውስጥ የህግ ክፍል የሚያስፈልጓቸው ተቋማት ስላሉ እነዛ ላይ ቅጥር ሊደረግ ይችላል። ስለዚህ እንደዚህ አይነት መንገዶችን ነው እየጠበቅን ያለነው።»

የቴዎድሮስ ሌላው አማራጭ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰጠውን ነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቅሞ የድረ ምረቃውን ትምህርት መቀጠል ነው። እንደዚህ አይነት አማራጭ ግን አብዛኛው ምሩቅ አይኖረውም።  «መንግሥት በየዓመቱ አዳዲስ ሰራተኞችን የማይቀጥር ከሆነ የተማረ የሰው ኃይል ስደትን እንደሚያበረታታ እና በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግር ሊፈጥር እንደሚችል» ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተደምጧል። ተስፋው የተሟጠጠው ምሩቅ ናትናኤልም ይህን ዕድል ቢያገኝ ወደ ኋላ አይልም።«  በጣም ብዙ ጓደኞቼ ሄደዋል። ለማስተርስ ትምህርት ፕሮሰስ እያደረጉ ያሉም አሉ። ቢሳካ በምን እድላችን። አሁን ያለው ሁኔታ ወደዚህ መመለስ እንዳናስብ የሚያደርግ ነው። እንደው ቤተሰብ ልጄ ተመረቀ እንዲል ያህል ነው። ተማሪውን ያስጨንቀው የነበረው ሥራ አገኛለሁ ወይ የሚለው ሳይሆን ቤተሰቤን ተመርቄ እንዴት አስደስታለሁ የሚለው ነው። » ይላል ናትናኤል።

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW