1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመንገድ ልማት ጥያቄ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሐሙስ፣ የካቲት 6 2017

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከተጀመሩ የመንገድ ግንባታዎች መካከል አብዛኞቹ በበጀት እጥረት ምክንያት መቋረጣቸውን የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ ። የወከሉት ማኅበረሰብ በመንገድ ችግር እየተሰቃየ እንደሚገኝ ለጉባዔው የገለጹ አንድ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ያልተሰሩ መንገዶች ተሠርቷል በሚል እንዴት የሪፖርቱ አካል ሊሆን ቻለ ሲሉ ጠይቀዋል ።

South West Ethiopia People Region Emblem
ምስል፦ South West Ethiopia People Region government Communication Affairs Bureau

የመንገድ ልማት ጥያቄ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቀደምሲል ከተጀመሩ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች መካከል አብዛኞቹ በበጀት እጥረት ምክንያት መቋረጣቸውን የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ ፡፡  ፕሮጀክቶቹን በቀጣይ ዓመታትም ገቢራዊ ለማድረግ አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ኃላፊዎቹ እየተካሄደ በሚገኘው የክልሉ 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል ፡፡ የወከሉት ማኅበረሰብ በመንገድ ችግር እየተሰቃየ እንደሚገኝ ለጉባዔው የገለጹ አንድ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ያልተሰሩ መንገዶች ተሠርቷል በሚል እንዴት የሪፖርቱ አካል ሊሆን ቻለ ሲሉ ጠይቀዋል ፡፡     

የመንገድ ልማት ጥያቄ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል

በዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ 7ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ የሚገኘው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት በርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ የቀረበለትን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በግብርና ፣ በጤና ፣ በትምህርት ፣ በሥራ ዕድለ ፈጠራ ፣ በሰላም እና ፀጥታ ዙሪያ ተከናውነዋል ያሏቸውን ተግባራት በአሃዝ በመስደገፍ ጠቅሰዋል ፡፡ የርዕሰ መስተዳድሩን ሪፖርት ተከትሎ በምክር ቤት አባላት የተነሱ የማብራሪያ ጥያቄዎች በአብዛኛው አንገብጋቢ ባሉት  የመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ያተኮረ ነው ፡፡

የእንደራሴዎቹ የማብራሪያ ጥያቄዎች

በጉባዔው ላይ የምክር ቤቱ እንደራሴዎች በክልሉ ዋነኛ ችግር ነው ያሉትን የመንገድ ልማት ጥያቄ አንስተዋል ፡፡ የወከሉት ማህበረሰብ በመንገድ እጦት እየተሰቃየ እንደሚገኝ ለጉባዔው የገለጹት አንድ የምክር ቤት አባል "በጭራሽ ያልሰሩ ሥራዎች የርፖርቱ አካል ሆነው ቀርበዋል ፡፡ ለአብነት የቦንጋ አዲያ ካካ መንገድ እነኳን ሊጠገን የግንባታ ተሸከርካሪዎች ወደ አካባቢው መጥተው አያውቁም ፡፡ ተሠራ የተባለው የ12 ኪሎ ሜትር መንገድ የት ጋር የተጠገነው " በማለት ጠይቀዋል ፡፡  

መልክአ ምድር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልምስል፦ Mahlet Fasil Desalegn/DW

በመንገድ መሠረተ ልማት ዙሪያ ሌሎች ምክር ቤት አባላትም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አንስተዋል ፡፡ አንዳንዶቹ በየአካባቢያቸው ይጀመራሉ የተባሉ ሥራዎች ለምን አልተጀመሩም ሲሉ ሌሎች ደግሞ በግንባታ ላይ ያሉት ለምን ተቋረጡ በማለት ጠይቀዋል ፡፡

 የኃላፊዎቹ ምላሽ

ከምክር ቤት እንደራሴዎቹ ለቀረበው ጥያቄ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡ የመንገድ መሠረት ልማት በባህሪው ሰፊ ሀብት የሚፈልግ መሆኑን የጠቀሱት የቢሮው ሃላፊ በሪፖርቱ የቀረቡት  በሀምሌ እና በነሀሴ ወራት የተከናወኑ ሥራዎች ናቸው  ብለዋል ፡፡ 

ሳይሰራ የውሸት ሪፖርት ቀርቧል የተባለው ትክክል እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ፋጂዮ "የተጠቀሰው የቦንጋ አዲያ ካካ  መንገድብ በተመለከተ በሪፖርቱ የተቀመጠው አምስት ኪሎ ሜትር ጠግነናል በሚል እንጂ አጠናቀናል አይልም  ፡፡ ዋነው ችግር ግን የበጀት እጥረት ነው ፡፡ ሱርማ ወረዳ ብቻ የተጀመሩ አራት  ድልድዮችን ላለፉት ሦስት ዓመታት ግንባታቸውን ማስቀጠል አልቻልንም ፡፡ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም አንጨርሳለን ብዬ አላስብም  ፡፡ በቀጣይ በራስ አቅም መሥራት የመጀመሪያው  አማራጭ ሊሆን ይገባል ፡፡ ከአቅም በላይ የሆኑትን ደግሞ ከክልል እና ከፌዴራል አካለት ጋር በመቀናጀት ሊሠራ ይገባል " ብለዋል ፡፡ 

የመንገድ ልማት ጥያቄ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ወጪ ይቀነስ

ዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸውና ጉባዔውን በቅርብ እየተከታተሉ የሚገኙት የካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት ሰብሳቢ አቶ ቦጋለ ሀይሌ በክልሉ በበርካታ አካባቢዎች የመሠረት ድንጋይ የተጣለባቸው ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ደረጃ እየተተገበሩ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መስተጓጎል ዋናው ምክንያት የበጀት እጥረት ነው በሚል በክልል የጠቀሰው ምክንያት በከፊል ተቀባይነት ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቦጋለ "ክልሉ ወጪን ለመቀነስ ለተለያዩ አላሥፈላጊ ክብረበዓላትን ለማክበር  የሚወጡ የሚዘገንኑ ወጪዎችን ማጤን ይኖርበታል ፡፡ ያንን ቀንሶ ወደ መሠረት ልማት ማዞር ይገባል " ብለዋል ፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል  መስከረም 20 ቀን 2014 ዓም ባካሄደው ህዝበ ውሳኔ ከቀድሞው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በመነጠል ራሱና በቻለ ክልል መደራጀቱ የሚታወስ ነው  ።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW