1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ገደብ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 2017

ከአዲስ አበባ በጎጃም አድርጎ እስከ ጎንደር በተዘረጋው አገር አቋራጭ መንገድ ላይ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ መኖሩን አሽከርካሪዎች እና አንድ የጎጃም አካባቢ ነዋሪ ገለፁ።

የጭነት ተሽከርካሪዎች በባሕርዳር
ከአዲስ አበባ በጎጃም አድርጎ እስከ ጎንደር በተዘረጋው አገር አቋራጭ መንገድ ላይ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ መኖሩን አሽከርካሪዎች እና አንድ የጎጃም አካባቢ ነዋሪ ገለፁ። ፎቶ ከማኅደር ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ገደብ

This browser does not support the audio element.

 

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሁለት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ከመንግሥት ጋር በሚዋጋው ፋኖ ከትናንት ጀምሮ በጎጃም መስመር የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲደረግ መገለፁን ተከትሎ መኪናዎቻቸውን ይዘው መቆማቸውን አስረድተዋል። ጎጃም ፈረስ ቤት ውስጥ የሚኖሩ አንድ ግለሰብ እንዳሉት ከሆነ ደግሞ በዚህ መስመር የጭነትን ጨምሮ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴያቸው የተገታ ሲሆን የንግድ ተቋማትም እየተዘጉ ነው።

የጎጃም አካባቢ ነዋሪ አስተያየት

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች እየተደረገ ያለውውጊያ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ቀጥሏል። ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች ቢደመጡም በተፋላሚዎች መካከል ግድያዎች፣ አፈናዎች፣ የተማረኩ እና ተደመሰሱ ዘገባዎች መውጣት አላቆሙም። በዚህ መሀል ንፁሐን ዜጎች መደበኛ ሕይወታቸው ክፉኛ እየተጎዳ መሆኑ በየጊዜው ይነገራል። ለዚህ አንዱ ማሳያዉ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ገደቦች ይጠቀሳሉ። ከትናንት ጀምሮ በተለይ በጎጃም መስመር የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በሚል በፋኖ ተሰጠ የተባለው ማሳሰቢያ የእንቅስቃሴ ገደብ መፍጠሩን አንድ የፈረስ ቤት ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

«በዚህ ሰሞን ገደብ ተጥሏል። መኪና እንዳይንቀሳቀስ፣ ሱቅ እንዳይከፈት፣ ባንክ እንዳይከፈት የሚል ማዕቀብ ተጥሏል። አሁን የመኪና እንቅስቃሴ ነው እንጂ ሱቆች በግድም ሆነ በውድ ሱቁን እየከፈቱ ነው ያሉት መከላከያዎች።» 

አሽከርካሪዎች ምን ይላሉ?  

በዛሬው ዕለት ሰሜን ጎንደር አካባቢ እንደሚገኝ የሚገልፅ አንድ የከባድ መኪና አሽከርካሪ በዚሁ ተጣለ በተባለው ገደብ ምክንያት ለመቆም መገደዱን ለዶቼ ቬለ ተናግሯል። «ከ 30 ጀምሮ ላልተወሰነ ቀን ነው ተዘግቷል የተባለው። እኔ አሁን በአጋጣሚ ሰሜን ጎንደር ነኝ። እና እዛ ነው የቆምነው»። ብለዋል።

ይሄዉ የእንቅስቃሴ ገደብ ከጅቡቲ በሚወጡ እና ወደዚያው በሚያቀኑት ላይም ሥጋትን ፈጥሮ እክል መሆኑን ሌላኛው አሽከርካሪ ይገልፃሉ።

«እኔም አሁን ገና ከጅቡቲ እየወጣሁ ነው። መንገድ ዝግ ነው ተብሎ መንገድ ላይ ቆሜያለሁ»። ነው ያሉት።

ከትናንት ጀምሮ በተለይ በጎጃም መስመር የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በሚል በፋኖ የተሰጠ ማሳሰቢያ መኖሩን ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።ፎቶ ከማኅደር ምስል Seyoum Getu/DW

የአማራ ክልል የሰላም ምክር ቤት ጥረት

ይህ የእርስ በእርስ ውጊያ እንዲያበቃ በሚል መንግሥትን እና የፋኖ ታጣቂዎችን ወደ ሰላም ለማምጣት የተቋቋመው ስብስብ እስካሁን የተጨበጠ ውጤት ያመጣ አይመስልም። የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያም አቶ እያቸውም ይህንኑ ነው የሚጠቅሱት። 

«በሁለቱም ወገን ያለው አለመተመመን የከፋ ነው አሁንም« ሲሉ ባለፈው ሳምንት ለዶቼ ቬለ ሁኔታውን ተናግረው ነበር። 

የአሽከርካሪዎች ማሕበር ምላሽ ?

አሽከርካሪዎች «ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች መንገድ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠየቃሉ» የሚሉት የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር የሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ሰለሞን ዘውዴ ለሾፌሮች አሁን አንፃራዊ ሰላም ያለው በአፋር ክልል ላይ ብቻ ነው ይላሉ። በኦሮሚያ ክልል የኮቴ በሚል ታጣቂዎች ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጥሩ፣ በአማራ ክልል ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት መባባሱን ጠቅሰው ትናንት ሰኞ ዕለት አንድ አሽከርካሪ ደቡብ ጎንደር ደብረታቦር አካባቢ በእንቅስቃሴ ላይ እያለ ተመትቶ ቆስሎ በህክምና ላይ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

እንዲህ ያለው ችግር ከፀጥታ ችግሮች ጋር ሲደመር የከፋ ውጤት ያለው በመሆኑ አሽከርካሪዎች ከጥዋቱ 12 እስከ ምሽት 11 ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ እንዲንቀሳቀሱም ጠይቀዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW