1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመንገዶች መዘጋትና መከፈት በጎጃም ቀጠና

ዓለምነው መኮንን
ሰኞ፣ ነሐሴ 5 2017

የምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ከተማ ነዋሪ ባለፈው አርብ በእጀብ ሲጓዙ የተወሰኑ መኪናዎችን ሲያልፉ ማየታቸውን ተናግረዋል።በከተማው ውስጥ የባጃጆች እንቅስቃሴ እንደነበር ጠቁመው፣ ከዚያ ውጪ ወደየትኛውም አቅጣጫ የሚጓዝ የህዝብ ትራንስፖርት እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡የአማራ ፋኖ በጎጃም ባሰራጨው አዲስ መረጃ፣ እገዳው ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አመልክቷል፣

Äthiopien | Straßen von Bahir Dar – Debre Markos – Addis Abeba und Straßen von Bahir Dar – Motta – Addis Abeba
ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የመንገዶች መዘጋትና መከፈት በጎጃም ቀጠና

This browser does not support the audio element.

ካለፈው ሐሙስ ነሐሴ 1/2017 ዓም ጀምሮ በጎጃም ቀጠናየህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትየሚሰጡ ዋና ዋና ጎዳናዎች ዝግ ሆነው መቆየታቸውን ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአንዳንድ ሸቅጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደታየ ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡን የምስራቅ ጎጃም ዞን የቢቸና ከተማ ነዋሪ መካከል አንዱ እንዲህ ብለዋል፡፡
“... ወቅቱ የግብርና ወቅት በመሆኑ የመንገዱ መዘጋት ማዳበሪያ ከሩቅ ቦታ መጥተው ወደ ገጠር የሚወስዱ አርሶ አደሮች ላይ ጫና ፈጥሯል፣ 80 እና 90 ብር የነበር የአንድ ሽንኩርት ዋጋ ወደ 140 ብር ከፍ ብሏል በመንገዱ መዘጋት ምክንያት” ብለዋል፡፡

“የትራንስፖርት አገልገሎት ተቋርጦ ሰንብቷል” ነዋሪዎች

ከከምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ከተማ  ትናንት አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ በበኩላቸው ባለፈው አርብ በእጀባ ሲጓዙ የተወሰኑ መኪናዎችን ሲያልፉ ማየታቸውን ተናግረዋል፣ በከተማው ውስጥ የባጃጆች እንቅስቃሴ እንደነበር ጠቁመው፣ ከዚያ ውጪ ወደየትኛውም አቅጣጫ የሚጓዝ የህዝብ ትራንስፖርት እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን መንገዶች የተዘጉት የአማራ ፋኖ በጎጃም የሰጠውን ማሳሰቢያ ተከትሎ ነው ያሉን አንድ አስተያየት ሰጪ ምክንያት ነው ያሉትን እንዲህ አብራርተዋል፡፡
“...  ከዚያ በፊት ከሞጣ አዴት (ሞጣ ባሕር ዳር አቅጣጫ) በረሀው ክፍል በመንግሥት ተዘግቶ ነበር፣ ጎጃምን ከወሎ የሚያገናኘው የመካነ ሠላም መርጡለማሪያም መስመርም በመንግሥት ዝግ ነበር፣ ሰሞኑን ደግሞ የአማራ ፋኖ በጎጃም “እኚህ መስመሮች ካልተከፈቱ” በሚል የባህር ዳር ማርቆስ አዲስ አበባን መንገድ ዘጋው” ነው ያሉት፡፡

“ከመካነ ሠላም መርጡለማሪያም መንገድ ከተዘጋ 6 ወራት አልፎታል” ነዋሪዎች

ከባህርዳር ወደ በደብረ ማርቆስ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

በደቡብ ወሎ ዞን የመካነ ሠላም ከተማ ነዋሪ ጎጃምን ከወሎ የሚያገናኘው መንገድ ከተዘጋ ከ6 ወራት በላይ በማስቆጠሩ በሁለቱ አዋሳኝ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ለመስራት አልተቻለም የሸቀጦች ዝውውርም ተዳክሟል ነው ያሉት፡፡ የመንግዱ መዘጋት ለወሎ ነዋሪዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደሆነ ነው ያብራሩት፡፡ ከዚህ ቀደም  ከወሎ ወደ ጎጃምና  ከጎጃም ወደ ወሎ ብዙ ሸቀጦች ይገቡ እንደነበር አስታውሰው፣ መንገዱ ባለመከፈቱ አንድ ኪሎ በርበሬ መካነ ሠላም ላይ ከ1400 እሰከ 1500 ብር እየተሸጠ መሆኑን ነው ነዋሪው የተናገሩት፡፡
“ስልመካነ ሠላም መርጡለማሪያም መንገድ መዘጋት “የማውቀው ነገር የልም”” የቦረና ወረዳ መንገድ ጽ/ቤት ጉዳዩን በተመለከተ ማረጋገጫ ወይም ማስተባበያ እንዲሰጡን ለደቡብ ወሎ ዞን ትራንስፖርትመምሪያ ኃላፊ አቶ ከድር ይመር ብንደውልም ጉዳዩ እርሳቸውን ሳይሆን የወረዳውን ትራንስፖርት ጽ/ቤት እንደሚመለከት ነግረውናል፡፡ በዞኑ የቦረና ወረዳ የትራንስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ አራጌ “ሰለጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የመንገድ ክልከላው ስለመነሳቱ

ዘግይቶ በደረሰን መርጃ ደግሞ የሰሞኑን የመንገድ መዘጋት ተመልክቶ የአማራ ፋኖ በጎጃም በሕዝብ ግንኙነቱ በኩል ባሰራጨው አዲስ መረጃ፣ ደብረ ማርቆስን ከባሕር ዳር የሚያገናኘው የጊደብ ድልድይ ተሰበሮ በወንዝ በመወሰዱ በህብረተሰቡ እንቅስቃሴ ላይ ተጨማሪ ጫና በመፍጠሩ ቀደም ሲል ባወጣው የእንቅስቃሴ እገዳ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አመልክቷል፣ “በመሆኑም ህዝቡ አማራጭ ያገኝ ዘንድ በእኛ በኩል በሁሉም አቅጣጫ ያስቀመጥነውን የመንገድ ክልከላ መመሪያ ያነሳን መሆኑን እናሳውቃለን” ብሏል፡፡
ያም ሆኖ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት የተወሰኑ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ቢኖሩም የትራንስፖርት አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ወደ እንቅስቃሴ ገብቷል ለማለት እንደማይቻል ገልጠዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
 ሸዋዬ ለገሠ 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW