1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግሥት ሠራተኞች የ3 ወራት ደሞዝ አልተከፈለም አሉ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 19 2015

ደቡብ ክልል ሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳና የሾኔ ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ላለፉት ሦስት ወራት የደሞዝ ክፍያ «ባለመግኘታችን ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል» አሉ ። ደሞዝ ባለማግኘታቸውም አንዳንዶቹ የሚበሉት በማጣት የቤት እቃዎቻቸውን እየሸጡ ፤ ከፊሎቹም ቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻላቸው ገጠር ቤተሰቦቻቸው ጋር ለመጠጋት መገደዳቸውን ገልጸዋል ።

Karte Sodo Ethiopia ENG

«ማዳበሪያ ከደሞዝ ጋር ምን አገናኘው?»

This browser does not support the audio element.

ደቡብ ክልል ሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ እና የሾኔ ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ላለፉት ሦስት ወራት የደሞዝ ክፍያ «ባለመግኘታችን ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል» ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናገሩ ። ሠራተኞቹ በደሞዝ አጦት ተነሳ አንዳንዶቹ የሚበሉት በማጣት የቤት እቃዎቻቸውን እየሸጡ ፤ ከፊሎቹም ቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻላቸው ወደ ገጠር ቤተሰቦቻቸው ለመጠጋት መገደዳቸውን ገልጸዋል ። ክፍያው ሊፈጸም ያልቻለው የቀድሞው የወረዳው አመራር የመንግሥት ሠራተኞችን የደሞዝ በጀት በዋስትና በማስያዝ የወሰዱሱት የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ባለመከፈሉ እና በዋስትና የተያዘው የደሞዝ በጀት ለአበዳሪው አካል ገቢ በመደረጉ ነው ተብሏል ። ሠራተኞቹ ማስተባበያውን የማይገናኝ ብለውታል ። 

በሠራተኝነት ሲቀጠሩ ወር በገባ በ30 መንግሥት የደሞዝ ክፍያ እንደሚፈጽም የቅጥር ውል ግዴታ የሚጥል ቢሆንም «ይህ ግን በምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ እና በሾኔ ከተማ አስተዳደር ላይ ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም» ብለዋል ። በወረዳው እና በከተማ አስተዳደሩ ከሁለት ሺህ በላይ ሠራተኞች በማገልገል ላይ እንደሚገኙ የሚናገሩት ሠራተኞቹ በአሁኑ ወቅት የደሞዝ ክፍያ በመቋረጡ ለችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል ። 

መምህርት ሥመኝ ኦልበሞ እና የግብርና ባለሙያው አሸናፊ ሙሉጌታ በምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ መንግሥት ሠራተኝነት በማገልገል ላይ ከሚገኙት መካከል ናቸው ፡፡ እነሱ የሚሰሩበትን ጨምሮ በሁሉም የወረዳው ጽህፈት ቤቶች በማገልገል ላይ ለሚገኙ ሠራተኞች ደሞዝ አለመከፈሉን ሥመኝ እና አሸናፊ ይናገራሉ ፡፡ የደሞዝ አለመከፈል ከነቤተቦቻቸው ለከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እየዳረጋቸው እንደሚገኝ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ «አንዳንዶቻችን የምንበላው በማጣት የቤት እቃዎቻችንን በርካሽ እየሸጥን እንገኛለን ፡፡ ከፊሎቻችን ደግሞ ቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻላችን ወደ ቤተሰቦቻችን ለመጠጋት ተገደናል» ብለዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ (DW) ያነጋገራቸው በሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ፋይናንስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብረሃም ሌራሞ የደሞዝ ክፍያው ሊፈጸም ያልቻለው የቀድሞው የወረዳው አመራሮች የመንግሥት ሠራተኞችን የደሞዝ በጀት በዋስትና በማስያዝ የወሰዱትን የአፈር ማዳበሪያ ብድር በወቅቱ ባለመመለሳቸው የተነሳ ነው ብለዋል ፡፡ አሁን ላይ ወረዳው ያለበት ዕዳ ባለመከፈሉ በዋስትና የተያዘው የሠራተኞች የደሞዝ በጀት ለአበዳሪው አካል ገቢ በመደረጉ የደሞዝ ክፍያ ለመፈፀም አለመቻሉን ነው ኃላፊው የተናገሩት  ፡፡

የወረዳው ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው የአፈር ማዳበሪያ ዋስትና በሚል ያሰጡትን ምላሽ እንደማይቀበሉት ሠራተኞቹ ይናገራሉ ፡፡ የመንግስት ሠራተኛ ደሞዝን እና የማዳበሪያ ዕዳን ምን አገናኘው በማለት የሚጠይቁት ሠራተኞቹ “ እኛ የመንግሥት ሠራተኛ እንጂ አርሶአደር አይደለንም ፡፡ ጉዳዩ በምንም መንገድ ከእኛ ደሞዝ ጋር ሊገናኝ የሚችልበት አግባብ አይኖርም ፤ ምላሹም አሳማኝ አይደለም “ ብለዋል ፡፡

የሠራተኞቹን የደሞዝ ችግር ለመፍታት አሁን ላይ በወረዳው የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ አብረሃም “ ምንም እንኳን ሁኔታው ከአቅማችን በላይ ቢሆንም የሠራተኞቹን ችግር በጊዜያዊነት ለማቃለል ከወረዳው ባለሀብቶችና ነጋዴዎች በብድር መልክ ገንዘብ ለማሰባሰብ እየሞከርን ነው ፡፡ በዘላቂነት ደግሞ ወረዳው ያለበት የማዳበሪያ ዕዳ በረጅም ጊዜ እንዲከፈል ሀሳብ እያቀረብን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ በሠራተኞቹ ቅሬታ ዙሪያ ተጨማሪ ምላሽ ለማግኘት የደቡብ ክልል የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ እና የፍይናንስ ቢሮ ሃላፊዎችን በአካል ለማነጋገር ቢሞከርም ሃላፊዎቹን በቢሯቸው ማግኘት ባለመቻሉና ስልክም ሲደወልላቸው ባለመመለሳቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡

ባለፈው ወር መጨረሻ  በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ አንድ ምከር ቤቱ አባል የደቡብ ክልል ለሠራተኞ ደሞዝ መክፍል እየተቸገረ መምጣቱን በመጥቀስ የፌደራሉ መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው  ፡፡ ያምሆኖ የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ እና የሾኔ ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች አሁንም የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ይገኛሉ ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW