1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት በማድረስ የተጠረጠሩ መታሰር

ረቡዕ፣ መጋቢት 27 2015

በአዲስ አበባ ፣ በባሕርዳር ፣ በአዳማና በድሬዳዋ ከተሞች ከፍተኛ «የመንግሥት አመራሮችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን በመፈጸም አገራዊ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ ነበር» በሚል በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ ከተደረጉት መካከል ሄኖክ አዲሱ የተባሉት የወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የራያ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባል አንዱ መሆናቸው ተገልጿል።

Justitia-Statue mit Waage
ምስል Arne Dedert/dpa/picture alliance

«ኅቡዕ መዋቅር በምስጢር የተንቀሳቀሰ ቡድን»

This browser does not support the audio element.

የጋራ ግብረ ኃይሉ በአዲስ አበባ ፣ በአማራ እና በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ያላቸው ምኁራን፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶችና ንቁ የፖለቲካ ተሳታፊዎች ወይም አክቲቪስቶችን ያካተተ «ኅቡዕ መዋቅር በምስጢር ሲንቀሳቀስ» ተደርሶበታል ብሏል። «ኅቡዕ» በተባለው አደረጃጀት ውስጥ ሲሳተፉ እና ሲያስተባብሩ የነበሩ የተባሉ ስምና ምስላቸው ይፋ ተደርጓል። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ አመሃ ዳኘውም ፍርድ ቤት ቀርበው «ወጣቶችን ማነሳሳት» በሚል ክስ እንደቀረበባቸው የገለፀው ፓርቲው ሁኔታው «ፓርቲውን የማዳከም እርምጃ ነው» ብሏል። ትናንት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ከተገለፀው ተጠርጣሪዎች መካከል የአንደኛው ጠበቃ ደንበኛቸው ቅዳሜ እለት ተይዘው ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው እንደተፈቀደ ገልፀዋል። ጠበቃው ብሔራዊ የፀጥታ እና ደህንነት ግብረ ኃይሉ ጥቃት ለመሰንዘር ትናንት በቂ ማስረጃ እንዳገኘባቸው ጠቅሶ ያወጣው መግለጫ የደንበኛቸውን «ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን የሚነፍግ» ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ፣ በባሕርዳር ፣ በአዳማ እና በድሬዳዋ ከተሞች ከፍተኛ «የመንግሥት አመራሮችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን በመፈጸም አገራዊ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ ነበር» በሚል በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ ከተደረጉት መካከል ሄኖክ አዲሱ የተባሉት የወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የራያ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባል አንዱ መሆናቸውን ጠበቃቸው የሆኑት በፌዴራል ማንኛውም ደረጃ ፍርድ ቤት ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ አዲሱ ጌታነህ «ለጥርጣሬ የሚያበቃ ነገር አልነበረም» የሚል መከራከሪያ ሰኞ ዕለት በአራዳ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ቀርበው መከራከራቸውን ገልፀዋል።
ከሳምንታት በፊት ታስረው የተለቀቁት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኛው «ወጣቶችን በማነሳሳት» ተጠርጥረው ቅዳሜ ዕለት በፖሊስ መያዛቸውን የገለፀት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር በቃሉ አጥናፊ ድርጊቱን «ፓርቲውን የማዳከም ሥራ ነው» ብለውታል።

«የአመጽ እንቅስቃሴ ለማካሄድ ሲደራጁና ሀገሪቱን ወደ ቀውስ ለመመለስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር» ተጠርጥረዋል ተብለው የተያዙት ሰዎች «ኅቡዕ ወታደራዊ ክንፍ በማደራጀት በጦር መሣሪያ የታገዘ የከተማ ላይ ጥቃት የመፈፀም እቅድ እንደነበራቸውና በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት በመፈፀም ሕዝቡን የማሸበር ተልዕኮ ይዘው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን»  የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው ገልጿል።

ከተጠርጣሪዎች የአንደኛው ጠበቃ አቶ አዲሱ ጌታነህ ትናንት የጋራ ግብረ ኃይሉ ካወጣው መግለጫ በፊት ሰኞ እለት ስድስት ተጠርጣሪዎች በአንድ መዝገብ ፍርድ ቤት ቀርበው እንደነበር ገልፀዋል።
የመንግሥት አመራሮችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን ለመፈጸም በኅቡዕ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል ተብለው ተጠርጥረው ከተያዙት ከ13 በላይ ሰዎች አንዱ የሆኑት የረዳት ፕሮፌሰር ማዕረጉ ቢያበይን ባለቤት ወይዘሮ መሠረት ትኩዬ በአጭር ተከታዩን ብለዋል። «በጎ አድራጎት ይሠራል እንጂ ሌላ ነገር የሚያደርገው ነገር ግን የለም።» በጉዳዩ ዙሪያ ከብሔራዊ የጋራ ግብረ ኃይሉ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW