1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመንግሥት ተቋማት የኢትዮጵያን ምርቶች እንዲገዙ የሚደረግ ግፊት ለአምራቾች ምን ይፈይዳል?

ረቡዕ፣ መጋቢት 4 2016

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የመንግሥት ተቋማት ከውጭ ከሚገቡ ሸቀጦች ይልቅ ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ እንዲሰጡ ግፊት እያደረጉ ነው። የማምረቻ ኢንዱስትሪው የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ፋይናንስ እና የውጭ ምንዛሪ እጦትን የመሳሰሉ ችግሮች ይፈታተኑታል። ባለፈው አንድ ዓመት 450 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች ሥራ አቁመዋል። የባለሥልጣናቱ ግፊት ምን ይፈይዳል?

Äthiopien Der Industriepark Adama
ምስል፦ Eshete Bekele Tekle/DW

የመንግሥት ተቋማት የኢትዮጵያን ምርቶች እንዲገዙ የሚደረግ ግፊት ለአምራቾች ምን ይፈይዳል?

This browser does not support the audio element.

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ባለፈው ሣምንት የመንግሥትን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ከገመገመ በኋላ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በሰጡት ማብራሪያ የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በተለያዩ ምክንያቶች የተዳከመ እንደሆነ ተናግረዋል። በተያዘው አመት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 56.4 በመቶ ከፍ እንዳለ የጠቀሱት ሚኒስትሩ ባለፉት ስድስት ወራት 994 ሚሊዮን ዶላር ከዘርፉ እንደተገኘ ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 1500 ገደማ አዳዲስ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን፤ በዘርፉ 120 ሺሕ ገደማ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። መንግሥት የሚከተለው “ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” አቶ መላኩ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት “ትልልቅ ውጤቶች” አምጥቷል።

የንቅናቄውን ውጤቶች የዘረዘሩት ሚኒስትሩ የማምረቻ ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን “ይኸ ነው የሚባል መሠረታዊ ለውጥ” እንዳላመጣ አልሸሸጉም። “በሀገር ውስጥ ያሉ ምርቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ግን በውድድር ለመንግሥት ግዢ” እንዲቀርቡ “አቅጣጫ” እንደተሰጠ አቶ መላኩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አምራቾች ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ያላቸው ድርሻ 38 በመቶ ብቻ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ባለፈው ወር በአዲስ አበባ ይፋ ያደረገው ሠነድ ያሳያል። የተቀረው 68 በመቶ ሀገሪቱ ከውጭ በምትሸምተው ሸቀጥ የሚሸፈን ነው።

አቶ መላኩ አለበል የማምረቻ ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን “ይኸ ነው የሚባል መሠረታዊ ለውጥ” እንዳላመጣ ተናግረዋልምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ “የሀገር ውስጥ ምርትን በሀገር ውስጥ የመጠቀም ዝንባሌው እና ተነሳሽነቱ ይቀራል” የሚል ዕምነት መንግሥታቸው እንዳለው ተናግረዋል። “የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ሕግ አሻሽለንም ቢሆን በቅድሚያ የሀገር ውስጥ ምርት እንዲገዙ እንዲጠቀሙ” እንደሚደረግም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

“የትኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ኢትዮጵያ ያመረተችውን ቀድሞ መግዛት አለበት” የሚል ውሳኔ እንደተላለፈ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። አቶ ተመስገን እንዳሉት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከዓለም ገበያ ሸቀጥ የሚሸምቱት በሀገር ውስጥ የተመረተ ካላገኙ ብቻ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የመረጠው መንገድ በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ “ብዙም የሚያረካ ውጤት” እንዳልተገኘበት በካናዳ ማክማስተር ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አዲሱ ላሽተው ይተቻሉ። “ሲጀመር የሀገር ውስጥ ፍጆታ በሀገር ውስጥ ምርት ያለመተካቱ ዋናው ምክንያት የሀገር ውስጥ አምራቾች ጠንካራ አለመሆናቸው ነው” የሚሉት የኤኮኖሚ እና ልማት ባለሙያው “ተሞክሮ የታየ፤ የማያዋጣ ፖሊሲ ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አምራቾች ተጠናክረው ምርቶቻቸውን በዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ፤ ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር እንዲፎካከሩ፤ ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ግፊት ማድረግ፤ ማበረታቻ መስጠት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።

ከኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑት ወይም 2.2 በመቶው በእንግሊዘኛ ኮንግሎሜሬት የሚባሉ ግዙፍ ኩባንያዎች መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ባለፈው ሣምንት በአዲስ አበባ ይፋ ያደረገው ሠነድ ያሳያል። በሠነዱ መሠረት 7.5 በመቶ መካከለኛ፣ 18.9 በመቶ አነስተኛ 71.4 በመቶ ደግሞ ጥቃቅን (ማይክሮ) ተቋማት ናቸው።

በኢትዮጵያ የሚገኙ 18 የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሺሕዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች በተለይም ለሴቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ምስል፦ DW/Tesfalem Waldyes

ከጎርጎሮሳዊው 1995 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ከሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የሚልኩት 5 በመቶ ብቻ እንደሆኑ ይኸው የጥናት ውጤት ያሳያል። በሀገሪቱ አምስት የግል እና 13 የመንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አሉ። በሠነዱ መሠረት የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ከ60 የተለያዩ የውጭ ባለወረቶች 740 ሚሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ-ንዋይ የሳቡ ሲሆን ለ150 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ከአዲስ አበባ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር ባካሔደው የዳሰሳ ጥናት የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ፋይናንስ፣ የውጭ ምንዛሪ እና ቢሮክራሲ ቀዳሚ ፈተናዎች እንደሆኑ ደርሶበታል። የኤኮኖሚ እና ልማት ጥናት ባለሙያው ዶክተር አዲሱ “ፋይናንስ እንደ ልብ ሊገኝ ያልቻለበት አንደኛው ምክንያት መንግሥት ራሱ በተለይ ከንግድ ባንክ ብዙ ስለሚበደር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የመንግሥት ወጪ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት እንደነበረው በመሠረተ-ልማት ግንባታ ላይ ከማተኮር ይልቅ “ለኤኮኖሚ ያላቸው አስተዋጽዖ ግልጽ ያልሆነ አይነት ፕሮጀክቶች ላይ” እንደሆነ ዶክተር አዲሱ ይተቻሉ። በዚህም ምክንያት “የግል ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አይችሉም። የፋይናንስ አቅርቦታቸው ይስተጓጎላል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ስድስት ወራት ባንኮች ካቀረቡት ከ170 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ውስጥ 83 በመቶው ለግል ዘርፍ የተሰጠ እንደሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተያዘው ዓመት ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድር መጠን ካለፈው ዓመት ከ1/3ኛ እንዳይበልጥ የመገደብ ዕቅድ አለው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2016 የመጀመሪያ ስድስት ወራት ባንኮች ካቀረቡት 170 ቢሊዮን ብር ገደማ ብድር 83 በመቶው ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ እንደሆነ ተናግረዋልምስል፦ Fana Broadcasting Corporate S.C.

በታኅሳስ 2016 በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ “ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት እና መዋቅራዊ ሽግግር” ላቅ ያለ ሚና እንዲጫወት የታቀደ ነው። መንግሥት ፖሊሲውን ሥራ ላይ ሲያውል የግል ባለ ሐብቱን ተሳትፎ ለማሳደግ እና ለማበረታታት ተስፋ ቢያደርግም እርግጠኝነት ማጣት ግን ኹነኛ ፈተና ነው።

የብር የምንዛሪ ተመን በባንኮች እና በጎንዮሽ ገበያው ያለው ከፍተኛ ልዩነት ለኢትዮጵያ አምራቾች የመወዳደር አቅም ትልቅ ፈተና ነው። የግሉ ዘርፍ መንግሥት በሚከተላቸው ፖሊሲዎች ረገድ የሚሰማው የእርግጠኝነት ማጣት ሌላው ተጠቃሽ ችግር ነው። ዶክተር አዲሱ “የግል ዘርፍ መር የሆነ ፖሊሲ በንድፈ-ሐሳብ አለ፤ በአፈጻጸም ስታየው ግን በመላው የመንግሥት ተቋማት የተደገፈ አይነት አካሔድ የለውም” ሲሉ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ማምረቻዎች በ30 በመቶ አቅማቸው ብቻ ሥራቸውን ያከናውናሉ። ተቋማቱ ከሚያመርቷቸው ሸቀጦች ምግብ፣ መጠጦች፣ ብረት ያልሆኑ ማዕድናት እና አልባሳት እስከ 50 በመቶ ድርሻ አላቸው። በኢትዮጵያ ግብዓቶች እና ሸቀጦች ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ የሚጠይቀው ወጪ አምራቾች ከሌሎች ሀገራት አቻዎቻቸው እንዲወዳደሩ የሚፈቅድ አይደለም።

በክልሎች መካከል ያለው የተዘበራረቀ አሠራር እና ሙስና ሌሎች የማምረቻ ኢንዱስትሪውን የሚገዳደሩ ችግሮች ናቸው። የመሬት አቅርቦት፣ ግብር እና ሙስና አምራቾች ሥራቸውን እንዳያስፋፉ ጋሬጣ ይፈጥራሉ። ፈቃድ ለማውጣት የሚወስደው ጊዜ፣ የሚጠየቀው ጉቦ፣ በክልሎች ያለው ውስብስብ ሒደት እና ውጤታማ ያልሆነ አሠራር መፍትሔ የሚሹ ችግሮች ናቸው።

ዶክተር አዲሱ የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ “በብዙ እጥፍ የማደግ አቅም” እንዳለው ቢያምኑም ቢሮክራሲ፣ ሙስና እና የመሠረተ-ልማት አለመሟላት እየተገዳደሩት እንደሚገኝ ይናገራሉ። የመንግሥት የገንዘብ አመዳደብ እና የውጭ ምንዛሪ ድልድል ለትልልቅ የመንግሥት ተቋማት ትኩረት መስጠቱን የሚተቹት ዶክተር አዲሱ ለግሉ ዘርፍ አቅም ማጣት “ዋናው ተጠያቂው መንግሥት ነው” የሚል ዕምነት አላቸው።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተለይ በትግራይ ክልል ፋብሪካዎች እና ማምረቻዎች ብርቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ምስል፦ Biniam Gebrezgi/Zenith Gebs Eshet Ethiopia Ltd

የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በደቡብ አፍሪካ በተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት ቢቆምም ሀገሪቱ የባለወረቶች ቀልብ መግዛት ወደምትችልበት መረጋጋት አልተመለሰችም። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ከመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ጋር የገቡበት ግጭት ከደም አፋሳሽነቱ ባሻገር ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን በኃይል ጎድቶታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የሁለቱን ክልሎች ቀውስ በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ እንደሆነ ቢገልጽም እስካሁን በተጨባጭ መፍትሔ አልተበጀም። ዶክተር አዲሱ “ፖለቲካዊ ችግሩ ቢፈታ ኤኮኖሚያዊ መስተካከል ይችላል” የሚል አቋም አላቸው።

“የፖለቲካው ችግር ከሥሩ መስተካከል አለበት” የሚሉት ዶክተር አዲሱ “ሀገሪቱ ውስጥ ቅቡልነት ያለው፤ ሕዝብ የሚያከብረው እና ሕዝብን የሚያከብር መንግሥት መመሥረት” እንደሚያስፈልግ በአጽንዖት ገልጸዋል።  

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ሠነድ 5000 ገደማ ከሚደርሱ የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች 450 የሚሆኑት ባለፈው አንድ ዓመት ሥራ ማቆማቸውን ያሳያል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራቸውን ያከናውኑ የነበሩ የውጭ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ከአጎዋ በመሠረዟ እና ሀገሪቱን በሚፈታተነው የጸጥታ ችግር ምክንያት ጥለው ወጥተዋል።

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW