1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳሬሰላም ድርድርና የሕዝብ አስተያየት

ዓርብ፣ ጥቅምት 30 2016

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሌላ ነዋሪም 2ኛ ዙር ድርድር ተጀምሯል መባሉን በድንገት መስማታቸውን ገልጸው ድርድሩ በስምምነት እንዲጠናቀቅና በክልሉ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ሁሉም ግፊት ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡

ወለጋ ዉስጥ የሚደረገዉ ግጭትና ጥቃት ካፈናቀላቸዉ ጥቂቱ
ወለጋ ዉስጥ የሚደረገዉን ግጭት የሸሼ ተፈናቃዮች በከፊልምስል Alemnew Mekonnen/DW

የዳሬ ኤስ ሰላም ድርድርና የወለጋ ህዝብ አስተያየት

This browser does not support the audio element.


የኢትዮጵያ መንግስትና መንግስት ኦነግ ሸኔ በሚል ስያሜ በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ሠራዊት (ኦነሠ) ዳሬሰላም ታንዚያ ዉስጥ በሚያደርጉት ድርድር እንዲስማሙ ሁሉም ወገን ግፊት ያደርግ ዘንድ የምዕራብ ኦሮሚያ ነዋሪዎች ጠየቁ።የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎችና የኦነሰ ታጣቂዎች ከአምስት ዓመት በላይ በገጠሙት ዉጊያ በተለይ የአራቱ የወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች ክፉኛ ተጎድተዋል። የአሶሳዉ ወኪላችን ነጋሳ ደሳለኝ ያነጋገራቸዉ ነዋሪዎች እንደሚሉት ሁሉም ወገኖችን የሕዝብን ደሕንነትና ጥቅም ማስቀደም አለባቸዉ።

ታጣቂዎችበብዛት ከሚንቀሳቀሱባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ የአራቱም የወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች ሰሞኑን በመንግስት እና መንግስት ሸኔ ብሎ በሚጠራቸውና ራሳቸውን ኦሮሞ ነጻነት ስራዊት ብሎ በሚጠሩ ታጣቂዎች መካከል በታንዛኒያ ተጀምሯል  የተባለው ሁለተኛው ዙር ድርድር በስምምነት እንዲጠናቀቅ ያላቸውም ምኞት ገልጸዋል፡፡ በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ነዋሪ እና በመምህርነት ስራ ላይ የሚገኙ ነዋሪ በሰጡን አስተያየት በአካባቢው ለረጅም ጊዜ በዘለቀው የሰላም እጦት ምክንያት በንግድ፣የጤና እና የትምህርት ስርዓት ላይ ከፍተኛ ተጽህኖ ደርሷል፡፡ በታንዛኒያ ተጀመረ የተባለው 2ኛ ዙር ድርድርም ለበርካቶች አሁንም ተስፋን የጫረ እና ውጤቱን በጉጉት እየጠበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች የህዝብን ጥቅም በማስቀደም አለመግባባቶችን በስምምነት ማጠናቀቅ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሌላ ነዋሪም 2ኛ ዙር ድርድር ተጀምሯል መባሉን በድንገት መስማታቸውን ገልጸው ድርድሩ በስምምነት እንዲጠናቀቅና በክልሉ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ሁሉም ግፊት ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ለዓመታት የቆየው ግጭት በሰላም ቢጠናቀቅ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱና ለ3 ዓመታት የተዘጉ መንገዶችም ተከፍተው ለዜጎች አገልግሎት ይሰጣሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
የቄሌም ወለጋዞን ዳንቢዶሎ ከተማው ነዋሪው አቶ ቀልበሳ የተባሉ ነዋሪ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበረው ድርድር አንጻር ይሳካል የሚል እምነት እንደለላቸው ገልጸዋል፡፡ 
‹‹ ድርድሩ ቢሳካ መልካምና ብዙ ችግሮችን ይፈታል ብለን እናስባለን፡፡ ሰው በሰላም ወጥቶ የመግባት፣የመንቀሳቀስ ዕድል ይኖረዋል፡፡ እንዲውም ለዓመታት ያላረሱ አርሶ አደሮችም ወደ መደበኛ ስራቸው ይመለሳሉ፡፡ ነገር ግን ይሳካል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ‹‹  

ከወለጋ ሸሽተዉ አዲስ አበባ የተጠለሉ ተፈናቃዮችምስል Solomon Muchie/DW

በምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ በህክምና ስራ ተሰማርቶ የሚገኙ ሌላው ነዋሪም በዞኑ ውስጥ በነበረው ግጭት በርካታ ጤና ተቋማት መጎዳታቸውንና ከአገልግሎት ውጪ የሆኑም እንዳሉ ገልጸው በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው ድርድሩ በስምምነት ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ 
የዛሬ ዓመት ገደማ ከምስራቅ ወለጋ ዞንኪረሙ ወረዳ ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰከላ የሚባል ቦታ እንዳሉ የነገሩን ነዋሪም የታጣቂዎችና መንግስት ድርድር ቀያአቸውን ጥለው ለሸሹ ነዋሪዎችም ወደ ቤታቸው ተመልሰው መደበኛ ህይወታቸውን ይመራሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው በስልክ ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን መመለስ እንደማፈልጉ አመልክተዋል፡፡ በርካታ የተፈናቀሉ ዜጎች በአካባቢው ለተራዘመ ጊዜ በግጭት ውስጥ ከመቆየቱ አንጻር አለመግባባቱ በድርድር እንዲፈታ ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል፡፡ 

ነጋሳ ደሳለኝ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW