የደሞዝ ጭማሪው «ሳይመጣ የሄደ ተስፋ» ወይስ ደጓሚ ?
እሑድ፣ መስከረም 19 2017የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጎኑ የሚገለጽ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ባደረገ ማግስት ለመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ሊያደርግ መሆኑ ተሰምቷል።
የደሞዝ ጭማሪው በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ መምህራን እና የጤና ባለሞያዎችን ጨምሮ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ የመንግስት ሰራተኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።
ገና በሂደት ላይ ያለው እና የመጨረሻ ውሳኔ ያላገኘው የደሞዝ ጭማሪ በዝቅተኛ የደሞዝ እርከን ላይ ያሉትን ሰራተኞች ከሶስት መቶ ሰላሳ በመቶ በላይ ጭማሪ እንደሚያስገኝ ሲጠበቅ እስከ ከፍተኛው የደሞዝ እርከን ያሉ ሰራተኞችም እንደደረጃቸው የደሞዝ ጭማሪ እንደሚደረግላቸው ይጠበቃል።
የደሞዝ ማስተካከያና የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ መጨመር
ነገር ግን በሀገሪቱ የዋጋ ግሽበቱ በአንድ ቀን ውስጥ ልዩነት በሚያሳይበት በአሁኑ ወቅት መንግስት ተግባራዊ ሊያደርገው የተቃረበው የደሞዝ ጭማሪ ምን ያህል የሰራተኛውን ኑሮ ይደጉማል የሚለው ጥያቄ ጎልቶ ይሰማል።
በሌላ በኩል በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያሉ እና የኑሮ ውድነቱ ፈተና የሆነባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና የግል ድርጅት ሰራተኞች ጉዳይን በተመለከተ መፍትሄ ስለመቀመጡ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም።
የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም የገንዘብ ድርጅት በቀረበ ብድር ተግባራዊ ያደረገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ በያዝነው ዓመት የጥር ገደማ «የዋጋ ግሽበቱ ከ30 እስከ 35 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል » ተተንብይዋል።
በተጨማሪ ገና ለገና የደሞዝ ጭማሪ ሊደረግ ነው በሚል በተለይ በመሰረታዊ የፍጆታ ቁሳቁሶች ላይ ተከታታይነት ያለው ጭማሪ እየታየ መሆኑን ሸማቾች ይናገራሉ ። ይህ ደግሞ የሰራተኛውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ይደግፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የደሞዝ ጭማሪ ተስፋ እንዳያመነምን ያሰጋል ።
መንግስት በተለይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰራተኞቹን ኑሮ ለመደጎም የደሞዝ ጭማሪ ሲያደርግ የጎንዮሽ ተግዳሮቶችን እንዴት ይቆጣጠራል የሚለው ጥያቄ መነሳቱም አይቀርም ።
«የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ሳይመጣ የሄደ ተስፋ ወይስ ደጓሚ ?» የእንወያይ ዝግጅታችን የዉይይት ርዕስ ነው ።
ታምራት ዲንሳ