የመንግስት የትኩረት አቅጣጫና የህዝቡ ቀዳሚ ፍላጎት
ማክሰኞ፣ መስከረም 27 2018
በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባኤ ላይ ትናንት ንግግር ያደረጉት ርዕሰ-ብሔር ታዬ አጽቀስላሴ የዓመቱን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች አመልክተዋል፡፡በዚሁ ላይ ከተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ዜጎች ሰላምና ጸጥታ ብሎም ያለቅጥ እያሻቀበ ያለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ከቀዳሚዎቹ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲገቡ እንደሚሹ አስረድተዋል፡፡
“ከስርዓት መለዋወት ጋር የማይናዱ ገለልተኛ እና ህዝባዊ ብሔራዊ ተቋማት ለመፍጠር መንግስት ጽኑ መሰረት በመጣል ላይ ይገኛል” ሲሉ በትናንት እለቱ የመንግስት የ2018 ዓ.ም. የስራ ትኩረት ላይ ትናንት አጽእኖት ሰጥተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ በተያዘው በጀት ዓመት መንግስት የተቋማት ግንባታው በማይናወጥ ደረጃ ላይ ለማድረስ እንደሚሰራ ነው ያስታወቁት፡፡
የሰላምና ጸጥታው ትኩረት
በዚሁ በትናንቱ የሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ መርሃግብር ላይ ባደረጉት ንግግር የበጀት ዓመቱን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ጠቋሚ ንግግራቸው ወቅት በአገሪቱ ተንሰራፍተው የሚስተዋሉ የሰላምና ፀጥታው ጉዳይ የመንግስት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ “በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን በኃል ማረቅ ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው ግን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ መንግስት ጽኑ እምነት አለው” በማለት የእርቅና የሰላም አማራጮችን በመከተል መንግስት የአገሪቱ ሰላም ለማረቅ እየሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የህብረተሰቡ ቀዳሚው ፍላጎት “ሰላም”
በዚህ ላይ ዶቼ ቬለ ከተለያዩ የአገሪቱአከባቢዎች ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች የሰላምና ጸትታው ጉዳይ ጊዜ የማይሰጠውና በተፋላሚ አካላት ሁሉ ለህዝብ ያደላ ውሳኔ የሚተላለፍበትና ስራዎች የሚሰሩበት ዓመት እንዲሆን ተማጽነዋል፡፡
የምዕረብ ኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦጋምቤል ወረዳ ተፈናቃዩ አስተያየት ሰጪ ይህ ዓመት ከንብረት ቀዬያቸው ያፈናቀላቸው ግጭት ፍፃሜውን አግኝቶ ወደ መደበኛ ህወታቸው የሚመለሱበት እንዲሆን መንግስት በዚሁ ላይ አተኩሮ ብሰራ ይላሉ፡፡ “በተጠና መልኩ ሰላምን አውርዶ ወደ ቀዬያችን ብንመለስ ደስ ይለኛል” ሲሉም ከመንግስት የሚጠብቁትን ቀዳሚ ፍላጎት አስረድተዋል፡፡
እንደ የምዕራብ ኦሮሚያው ተፈናቃይ ሁሉየሰላምና ጸጥታው ይዞታ በትልቁ የሚያሳስብና እንዲሰራበት የምንፈልገው ቀዳሚው ጉዳይ ነው ያሉት የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረጽጌ ከተማ እና የአማራ ክልል ደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎችም በአስተያየታቸው እንዲህ ብለዋል፡፡ “ባሁን ወቅት አባይ ተመርቆ ብዙ ፕሮጀክት ስራዎች መታቀዳቸው ለኛ መልካም ነው፤ የጸጥታው ጉዳይ ግን የሁሉም አካላት ፍላጎትን የሚሻ እንዲ በአንድ አካል ፍላጎት ብቻ እንደሚሳካ ስለምናውቅ ሁሉም ተፋላሚዎች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በመምጣት ቢፈቱ” ያሉት የሰሜን ሸዋ ዞን ደብረጽጌ ነዋሪ ናቸው፡፡ የአማራ ክልል ደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ በፊናቸው፤ “ሰላም ሆኖ በሰላም ወጥቶ መግባት ከስጋት ነጻ መውጣት የምንፈልገው የመጀመሪያው ጉዳይ ነው” በማለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢኮኖሚው አንገብጋቢ መፍትሄ
መንግሥት ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ፣ እና የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሠራ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በትናንቱ የመንግስት አቅጣጫ ካነሷቸው ሃሳቦች አንዱ ነው፡፡
አስተያየት ሰጪ ነዋሪዎቹም ከኢኮኖሚው አከሷያ በብርቱ ፈትኖናል ያሉት የዋጋ ንረትና ግሽበቱ አንገብጋቢው የመንግስት የስራ አቅጣጫ ቢሆን የሚል አስተያየትንም ሰጥተዋል፡፡ “ለመኖርም በጣም እየፈተነን ያለው ሁለተኛ ጉዳይ ደግሞ የኑሮ ውድነት ነው” የሚሉት የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪው፤ የኑሮ ሁኔታውን ማረጋጋት ብቻል የዜጎች ሌላኛው ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡ ሰሜን ሸዋ ደብረጽጌ ከተማ ነዋሪዋም፤ “የሰላም እና ጸጥታው ጉዳይ እልባት ካገኘ ሌላውን የህዝብ ጥያቄ መመለስ ካባድ አይሆንም” ባይ ናቸው፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫኔ