1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የመከላከያ ሠራዊትን እንቅስቃሴ ማስተጓጎል ተገቢ አይደለም» ዶክተር ደብረ ጽዮን

ረቡዕ፣ ጥር 1 2011

በትግራይ ክልል አመራሮችና በኤርትራ ባለስልጣናት መካከል የመነጋገር ፍላጎት እንዳለ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ተናገሩ፡፡ በቅርቡ በትግራይ ክልል በተደጋጋሚ የታየው የመከላከያ ሠራዊትን እንቅስቃሴ የማስተጓጎል ሁኔታ ተገቢነት እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡

Äthiopien - Tigray Regionalregierung Vizepräsident Dr. Debretsion Gebremikail PK
ምስል DW/M. Haileselassie

በኤርትራና በትግራይ ክልል ባለስልጣናት መካከል የመነጋገር ፍላጎት አለ ብለዋል

This browser does not support the audio element.

በትግራይ ክልል አመራሮች እና በኤርትራ ባለስልጣናት መካከል የመነጋገር ፍላጎት እንዳለ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ፡፡ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ይህን የተናገሩት ትላንት ማምሻውን ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። 
“በትግራይ እና ኤርትራ መሪዎች መካከል የቆዩ ችግሮች ነበሩ” ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ “እነዚህ ችግሮች ለመፍታት በሁለቱም ወገን ለውይይት ዝግጁነት አለ” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።ቀደም ሲል ከኤርትራ መንግስት ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የጠቆሙት ምክትል ዶ/ር ደብረፅዮን ከኤርትራው መሪ ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋርም ከአንድም ሁለት ጊዜ አጫጭር ውይይቶችን ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ከትላንት በስቲያ ሰኞ በተካሄደው የሑመራ - ኦምሓጀር ድንበር መክፈት ስነ ስርዓት ላይ ከፕሬዝዳንት ኢስሳያስ ጋር ተገናኝተው መምከራቸው የጠቆሙት ዶክተር ደብረፅዮን “የቆዩ ችግሮች መፈታት እንደሚገባቸው ፕሬዝደንት ኢሳያስ ገልፀውልናል፡፡ ይህ እኛም የምንፈልገው ነው” ብለዋል፡፡ 
በሰኞው ስነስርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ኢስሳያስ እና ዶ/ር ደብረፅዮን ከሌሎች ባለስልጣናት ነጠል ብለው እና እጅ ለእጅ ተጨባብጠው በቅርበት ሲነጋገሩ ታይተዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ ወገን ዶ/ር ደብረፅዮንን ጨምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ተገኝተዋል።     
በኤርትራ በኩል ከፕሬዝደንት ኢሳይያስ በተጨማሪ የፕሬዝዳንቱ አማካሪ የማነ ገብረአብ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦስማን ሳሌሕ፣ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ኤታማዦር ሹም ፊሊጶስ ወልደዩሃንስ እና ሌሎች ከፍተኛ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ታድመዋል። ዶ/ር ደብረፅዮን በትላንቱ መግለጫቸው “በሁለቱም ወገን፤ ያለፉ ጥፋቶችን ልንማርባቸው እንጂ ሒሳብ ልናወራርድ አይገባም” ሲሉ ስለ መጪው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ተናግረዋል። 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከጋዜጣዊ መግለጫቸው ከኢትዮ- ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታ በተጨማሪ  ሌሎች ጉዳዮችም አንስተዋል፡፡ በዛላምበሳና ራማ በኩል ወደ ኤርትራ ይደረግ የነበረው የየብስ ጉዞ በቅርቡ ስርዓት ተበጅቶለት ወደ ስራ ይገባል ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡ በቅርቡ በትግራይ ክልል በተደጋጋሚ የታየው የመከላከያ ሰራዊትን እንቅስቃሴ የማስተጓጎል ሁኔታ ተገቢነት እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW