1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመከላከያ አባል በጉጂ የአምስት ዓመት ሕጻን ወንድ በአሰቃቂ ሁኔታ ደፈረ መባሉ

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 2 2017

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ዋደራ ከተማ የአምስት ዓመት ሕጻን ወንድ ልጃቸው የመከላከያ ሠራዊት አባል ነው በተባለ ግለሰብ እንደተደፈረባቸው ተጎጂ ቤተሰብ እና የአከባቢው ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል ።

Symbolbild | Justiz
ምስል፦ fikmik/YAY Images/IMAGO

የተደፈረው ሕጻን ልጅ ከባድ አካላዊ ጉዳት ደርበታል

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ዋደራ ከተማ የአምስት ዓመት ሕጻን ወንድ ልጃቸው የመከላከያ ሠራዊት አባል ነው በተባለ ግለሰብ እንደተደፈረባቸው ተጎጂ ቤተሰብ እና የአከባቢው ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል ። ፖሊስ ጉዳዩ ምርመራ ላይ በመሆኑ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ቢቆጠብም ታዳጊው ላይ አስነዋሪ በሆነ መልኩ ጉዳት አድርሷል የተባለው ግለሰብ ግን በሕግ ቁጥጥር ስር መዋሉ እየተነገረ ነው ።

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ዋደራ ከተማ የአምስት ዓመት ሕጻን ልጅ የመከላከያ ሠራዊት አባል ነው በተባለ ሰው መደፈሩን የተጎጂው አጎት ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ። ተፈጸመ ባሉት የአስገድዶ መድፈር ድርጊትም ሕጻኑ ክፉኛ መጎዳቱንና በአዶላ እና ሀዋሳ ሆስፒታሎች ህክምናውን በመከታተል ላይ እንደሆነ አስረድተዋል። ኅዳር 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም. ዓርብ በአዶላ ወረዳ አዶላ ከተማ ሸዋ በር በምትባል ልዩ ስፍራ ተፈጸመ የተባለው ድርጊቱ በአከባቢው ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ በመሆኑ ክፉኛ ድንጋጤ መፍጠሩም ተገልጿል።

ድርጊቱ የተፈጸመበት አሰቃቂ ሒደት

«ድርጊቱ ጫፍ የወጣ ከባድ ድርጊት ነው» ሲሉ ስሜታቸውን የገለጹት የሕጻኑ እናት ወንድም በሰሰጡን አስተያየት፦ ድርጊቱ ኅዳር 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም. መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ ይህ አሰቃቂ የተባለው ድርጊት የተፈጸመበት ዋደራ ከተማ ሸዋበር አከባቢ የመከላከያ ጣቢያ መኖሩን የገለጹት የተጎጂው ቤተሰብ አባል ጉዳቱን ያደረሰው ግለሰብ የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆኑ ይበልጥ ድንጋጤን የፈጠረው የማይጠበቅ ተግባር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ በእለቱ ህጻኑን ይዞ እንደነበርና ቤተሰብ ለሥራ ቤት አለመዋላቸውን ገልጸውም እናት ለምሳ ከሚሠሩበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሲመለሱ ልጃቸውን በማጣታቸው ለፖሊስ እስከማመልከት ያደረሳቸው እልህ አስጨራሽ ፍለጋ ማድረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡ «በመጨረሻ ግን ህጻኑ መቀመጥ መነሳት የማይችልበትና ሽንቱን መቆጣጠር እንደተሳነው ቤተሰብ ሲረዳ መደናገጥ ተፈጥሯል» ነው ያሉት፡፡

ሕጻናት እና ሴቶች ላይ የሚደርስ አስገድዶ መድፈር አሳሳቢነቱ እያነጋገረ ነውምስል፦ Colourbox

የሕክምና ውጣ ውረድ

ህጻኑ ላይ የተፈጸመውን  የአስገድዶ መድፈር ድርጊት የተገነዘበች እናት ወንድማቸውን ጠርተው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲያመሩ ወደ ህክምና ተቋም እንዲወስዱት በተነገረው መሰረት አከባቢ ላይ ወዳለው የህክምና ተቀቋም ቢያመሩም ከአቅማቸው በላይ ይሆናል ። የተሻለ የህክምና መሣሪያ ወዳለበት አዶላ ሆስፒታል ሪፈር ቢባሉም በዚያም ህክምናው ከሆስፒታሉ አቅም በላይ ይሆናል፡፡ «ትንሽ ጉዳቱ ከፍ ስለሚል ኢንደስኮፒ በሚባል መሣሪያ መታየት አለበት ተባልን፡፡ ልጁ ሽንቱንም መቆጣጠር የማይችልበት ደረጃ ላይ ስለነበር ወደ ሀዋሳ ሆስፒታል ሪፈር ጻፉልን» ያሉን የተጎጂው ቤተሰብ በሃዋሳ ልጁን ለአራት ቀናት ካስተኙ በኋላ ህክምና ባለሞያዎች ለጊዜው መድኃኒት ሰጥተው በዚያም ካልተሻለው ካሳምንት በኋላ መልሰው እንዲወስዱት እንደተነገራቸውም አስረድተዋል፡፡

የሀዋሳ ሆስፒታል የህጻኑ የጤና ሁኔታ የማይሻሻል እና የቀዶ-ጥገና ህክምና የሚስፈልገው ከሆነ ወደ ጥቁር አንበሳ እንዲወስዱ ሪፈር እንደሚጽፍላቸውም ነግሯቸዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው የቤተሰብ አባል፤ ጉዳቱን አድርሷል የተባለው ግለሰብ በአሁኑ ወቅት በመከላከያ ካምፑ በቁጥጥር ስር ውሎ ድርጊቱን በማመኑ አስፈላጊው የሕግ ሂደቶች በሰራዊቱ አመራሮችና አቃቤ ሕግ እንዲሁም በአከባቢው ፖሊስ እየተጣራ ነው፡፡

የወላጅ እናት ሰቆቃ

የአስገድዶ መድፈሩ ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ በእለቱ ህጻኑን ይዞ እንደነበርና ቤተሰብ ለሥራ ቤት አለመዋላቸው ተገልጿልምስል፦ Seyoum Getu/DW

ወደ ሚሠሩበት መሥሪያ ቤት እንደወትሮው በጠዋት ከቤት መውጣታቸውን ገልጸው አስተያየታቸው የሰጡን የተጎጂ ህጻኑ እናት ወደቤት ሲመለሱ ህጻኑን የአምስት ዓመት ታዳጊ ልጃቸውን ከቤት በማጣታቸው ፍላጋ ከወጡ በኋላ «ልጄ እንዳልሆነ ሆኖ አገኘሁት» ይላሉ፡፡ እናም ከሕግ ፍትህን እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ «ሌላ ቦታ የሰሚ ሰሚ ካልሆነ እንዲህ ያለ ነገር በፍጹም በአከባቢያችን ሰምተንም አይተንም ዐናውቅም፡፡ ሰው ሁሉ ቅዠት እንጂ እውነት ለማለት እየተቸገረ ነው፡፡ እንኳን እኔ ሁሉም ማኅበረሰብ ነው የደነገጠው፡፡ የሰራዊቱ አባላትም ግለሰቡ ስማችንን አጠፋ በእሱ የተነሳ ወጥተን  ለመግባት እንኳ እየተሳቀቅን ነው እያሉ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡ አሁን የምንጠብቀው ህግ የሚለውን ነው” ብለዋል፡፡

ጉዳዩን አረጋግጠው በሕግ ሂደት ላይ መሆኑን ያስረዱን የወረዳው ሴቶች እና ህጻናት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ዱሬ ዱቤ፤ «ጉዳዩ አሁን በሂደት ላይ ነው፡፡ አጥፊውም በቁጥጥር ስር ውሎ ማስረጃዎች እየተጠናከሩ ይገኛሉ፡፡ እኛም በቅርበት እየተከታተልነው ነው» ብለዋል፡፡

በጉጂ ዞን በተራዘመው የሸማቂዎች እና የመንግስት ሰራዊት ውጊያ በተለያዩ ጊዜያት በታጣቁ አካላት የመብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙ ከዚህ በፊት ተደጋግሞ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW