የቅድስት ክፍሌ መታሰቢያ የመንገድ ደሕንነት ትምሕርት
ማክሰኞ፣ መጋቢት 22 2018
የቅድስት ክፍሌ መታሰቢያ
ቅድስት ክፍሌ፣ እንደ ጎርጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2019 ከካናዳ ወደኢትዮጵያየተጓዘችው፣የዕረፍት ጊዜዋን ለማሳለፍ ነበር፤ይሁንና ጊዜዋን በሚገባ ሳታጣጥም፣አዲስ አበባ ውስጥ በደረሰባት ድንገተኛ የመኪና አደጋ ሕይወቷን አጣች።
ቅድስት ክፍሌን ለማስታወስ የተቋቋመው ኪዲ ፋውንደሽን፣በጎ ተልዕኮን ለማነሳሳት መብቃቱን፣ የድርጅቱ መስራችና ፕሬዚዳንት ኤልሳቤጥ ወልደ ማርያም ለዶቼ ቨለ ገልጸዋል።
''ቅድስት ታናሽ እህቴ ናት።እና እሷ ኢትዮጵያ ውስጥ በመኪና አደጋ ህይወቷ አልፎ የአንድ ልጅ ናት፣ ባለትዳር እና በእሷ ምክንያት ነው እኛም ወደዚህ ነገር የገባነው።አደጋው እንዳለ እናውቃለን፤ የመኪና አደጋ ብዙ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገድል እናውቃለን፤ እና አንዳንድ ጊዜ በራስህ ሲመጣ በጣም ህመሙን መቋቋም አትችልም። እና አደጋ አንደኛ ነገር መከላከል የሚቻል ነገር ነው፣ መከላከል የምንችላቸው አደጋዎች ናቸው።''
የመኪና አደጋ ተጎጂዎች
በኢትዮጵያ 65 በመቶ የሚሆነው የመኪና አደጋ የሚደርሰው፣ በአውቶቡሶች እና የንግድ ተሽከርካሪዎችን እንደሆነ፣የኪዲ ፋውንዴሽን የቦርድ አባል አቶ ሊበን ገብረሚካኤል ይናገራሉ።
''65 በመቶ የመኪና እደጋ የሚደርሰው፣ በአውቶቡሶች እና በንግድ ሽከርካሪዎችን እንደሆነ፤ በመኪና አደጋ ደረጃ በዓለም 19ኛ ናት ኢትዮጵያ በአፍሪቃ የተወሰኑ ሃገሮች ናቸው ከእኛ የሚበልጡት እና ከፍተኛ ጉዳይ ነው።''
አቶ ሊበን ጨምረው እንዳስረዱት፣በመኪና አደጋ ብዙ ጊዜ ሕይወታቸውን የሚያጡት እና የአካል ጉዳት የሚደርስባቸው፣ዕድሜያቸው ከ 18 እሰከ 30 ዓመት የሚሆናቸው ወጣት እና አምራች ዜጎች ናቸው።
''በብዛት የሚጠቁት ከ18 እስከ 30 ዓመት ያሉት፣በአማካይ፣በእዛ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ናቸው ብዙ ጊዜ የሚጠቁት፣ወጣት ትውልዶች ናቸው። 33 በመቶ የሞት አደጋ በአዲስ አበባ ውስጥ ነው የሚደርሰው ሌሎቹ በገጠር ነው። በአዲስ አበባ 78 በመቶ በአደጋ የሚጠቁት፣እግረኞች ናቸው። ''
የትራፊክ ደህንነት ግንዛቤ
ይህንን አሳዛኝ እውነት ለመቀየር እናበትራፊክ ደህንነት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ኪዲ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ቢሮ ከፍቶ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሆነ ፣የድርጅቱ መስራችና ፕሬዝደንቷ አስረድተዋል።
"አዲስ አበባ ላይ ቢሮ አለን፣ ወደ ሳርቤት አካባቢ፣ ካናዳ ኤምባሲ አካባቢ፤እዚህም ቢሮ አለን። የምንሰራው መጀመሪያ ሰውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ለማሳወቅ፣ አደጋው ምን ያህል በጣም ክፉ እንደሆነ፣ሰው በደንብ እንዲያውቅ እና ይህን ነገር ለመከላከል ዘመቻዎች እናዘጋጃለን።ትምህርት ቤት ውስጥ አሁን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ስድስተኛ ትምህርት ቤቶች ላይ ደርሰናል። አንደኛው ቢሸፍቱ ውስጥ፣ለሎቹ አምስቱ አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ህፃናቶችን አምስተኛ ክፍል፣አሁን ደግሞ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል እንሰጣለን።''
ኪዲ ፋውንዴሽን፣ የመኪና አደጋ ተጎጂዎን እና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት በማኅበረስብ ላይ የተመሰረተ ድጋፍና እንክብካቤ እንደሚያደርግም ከፕሬዝዳንቷ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
''ለሕይወት ቅድሚያ እንስጥ፣አንድም ሕይወት ማዳንትልቅ ተግባር ነው ።'' በሚል መርዕ የሚንቀሳቀሰው ግብረ ሰናይ ድርጅቱ፣ኢትዮጵያ ውስጥ፣እንደ ቅድስት ዓይነት ልብ ሰባሪ የመኪና እደጋዎች፣ በከፍተኛ ደረጃ ተወግደው ማየትን ያልማል።
ታሪኩ ኃይሉ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ነጋሽ መሐመድ