1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመውሊድ በዓል ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴት

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 29 2017

ዛሬ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ የዋለው 1 ሺህ 500ኛው የነብዩ መሃመድ ልደት (መውሊድ) ትልቅ መንፈሳዊ ትርጉም የሚሰጠው ነው ። በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዓሉ ሲከበር ከሃይማኖታዊ ይዘቱም ባሻገር ባሕላዊ እሴቱም ጎልቶ እንደሚጠቀስ የሃይማኖቱ ልሒቃን ያስረዳሉ ።

የመውሊድ በዓል አከባበር በኢትዮጵያ
በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ የዋለው 1 ሺህ 500ኛው የነብዩ መሃመድ ልደት (መውሊድ) ትልቅ መንፈሳዊ ትርጉም የሚሰጠው ነው ። የመውሊድ በዓል አከባበር በኢትዮጵያ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Mesay Tekelu/DW

የመውሊድ በዓል ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴት

This browser does not support the audio element.

ዛሬ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ የዋለው 1 ሺህ 500ኛው የነብዩ መሃመድ ልደት (መውሊድ) ትልቅ መንፈሳዊ ትርጉም የሚሰጠው ነው ። በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዓሉ ሲከበር ከሃይማኖታዊ ይዘቱም ባሻገር ባሕላዊ እሴቱም ጎልቶ እንደሚጠቀስ የሃይማኖቱ ልሒቃን ያስረዳሉ ። የመውሊድ ሃማኖታዊ እና ባህላዊ ትሩፋቱ በኢትዮጵያውን ሙስሊሞች ዘንድ እንዴት ይዘከራል?

የመውሊድ ሃይማኖታዊ አንድምታ

ሼክ አብዱልሃሚድ አህመድ በኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት የብሔራዊ መውሊድ አስተባባሪ ናቸው፡፡ ነብዩ መሃመድ የተወለዱበት እለት የሚታወስበትና የሚከበርበት የዛሬው እለት መውሊድ በእስልምና ሃይማኖት ዘንድ ያለውን ስፍራ ሲያስረዱ፤ "መውሊድ ነብዩ መሃመድ የተወለዱባት ልዩ ቀን ናት፡፡ ይህችን ቀን እሳቸው በጸሎት ያከብሯት ያስታውሷትም ነበር” በማለት መውሊድን ሙስሊሞች  ከጭለማ ወደ ብርሃን የወጡበት ቀን አድረገው እንደሚያስታውሱም አስረድተዋል፡፡

"አሏህ ፍርድ በሚሰጥበት እለት ነብዩ መሓመድ ለኛ አማላጅ ሆነው እዝነት ስለሚሰጡ፤ ትልቅ እዝነት ነብይ ስለሆነ መውሊድን እናከብራለን” ሲሉም እለቱ ከሃይማኖቱ አኳያ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

መውሊድ በኢትዮጵያውን ሙስሊሞች

ኢትዮጵያ ሙስሊሞች መውሊድን የሚያከብሩበት ባሕል እሴቱ ከሌላው ዓለም ይለይ ይሆን የሚል ጥያቄም የቀረበላቸው ሼኽ አብዱልሃሚድ፤ "መውሊድ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ነው፤ ከሌላው ዓለም እንለያለንም” በማለት ንጉሥ ነጃሺ ሙስሊሞችን ከነብዩ መሀመድ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት የተቀበሉበትን ታሪካዊ ቁርኝትም አንስተው የነብዩ መሀመድ ልደት መውሊድ ስከበር እነዚህ ሁሉ የሚታወሱ ይሆናልም ብለዋል፡፡

"መውሊድ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ነው፤ ከሌላው ዓለም እንለያለንም” ሼኽ አብዱልሃሚድ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Mesay Tekelu/DW

የመውሊድ ባሕላዊ በረከቶች

እንደ የሃይማኖት አዋቂው ማብራሪያ መውሊድ  በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዘንድ  ሲከበር ከሃይማኖታዊ ይዘቱና መልእክቱም ባለፈ በባሕላዊ የማኅበረሰብ ትስስሩም አይነተኛ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል፡፡ "ሀገር ላይ ችግር ስመጣ በመውሊድ ተሰባስበው ነው ዱዓ የሚደርጉት፡፡ የተነፋፈቁ የተራራቁም ሰዎች የሚገናኙት በመውሊድ ላይ ነው” ሲሉ ስለመሰል ሃይማኖታዊ በዓል አከባበርና እሴቶች ዘርዝረው ተናግረዋል፡፡

"በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዘንድ የተለመደው በዚህ እለት እርድ ተከናውኖ፤ ምግብም ተዘጋጅቶ የሃይማኖቱ ልቃዎንት ደረሳዎችም ጭምር ተሰባስበው ይዘያየራሉም” ብለዋል፡፡ "ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ሙስሊም ያልሆነውም እንኳን አደረሳችሁ በሚል ይዘያየራሉ” ብለዋል፡፡ እናም ሰው እንዲገናኝና አብሮነትን እንዲያጠነክር መውሊድ ትልቁን ስፍራ ከሚይዙ የኢትዮጵያውያን ዓመታዊ በዓል አከባበሮች ተጠቃሽም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW