የመጀመርያዉ ነጭ ደቡብ አፍሪቃ ቡድን በትራምፕ የስደተኞች እቅድ መሰረት ወደ አሜሪካ ተጓዙ
ሰኞ፣ ግንቦት 4 2017
በትራምፕ የስደተኞች እቅድ መሰረት የመጀመርያዉ ነጭ ደቡብ አፍሪቃዉያን ቡድን ወደ አሜሪካ ተጓዘ
የትራምፕ አስተዳደር ይፋ ባደረገዉ ፕሮግራም አማካኝነት አሜሪካ ዉስጥ የጥገኝነት መብት የተሰጣቸው ነጭ ደቡብ አፍሪቃውያን የመጀመሪያ ቡድን ደቡብ አፍሪቃን መልቀቁ ተሰማ። የደቡብ አፍሪቃ የትራንስፖርት ክፍል ቃል አቀባይን ጠቅሶ አሶሽየትድ ፕሬስ እንደዘገበዉ፤ 49 የደቡብ አፍሪቃ መንገደኞች የይለፍ ፈቃድ ተሰቷቸዉ እሁድ ምሽት ተሳፍረዋል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አብዛኞች አፍሪቃዉያን ለሆኑት ለነጮች ደቡብ አፍሪቃውያን የጥገኝነት እድል መስጠታቸዉ ይታወቃል። ትራምፕ ለደቡብ አፍሪቃዉያን ነጮች ይህን እድል የሰጡበት ምክንያት፤ በአብዛኛዉ ጥቁሮች በሚገኙባት ደቡብ አፍሪቃ፤ ነጭ ደቡብ አፍሪቃዉያን «የዘር መድልዎ» ይደርስባቸዋል ሲሉ ነዉ። ያም ሆኖ አፓርታይድ ከተገረሰሰ ከ30 ዓመታት በኋላ ዛሬም በደቡብ አፍሪቃ የተደላደለ ኑሮ ያላቸዉ ነጭ ደቡብ አፍሪቃዉያን ተወላጆች ናቸው። ደቡብ አፍሪቃ ከሚገኙት ዜጎች መካከል ሰባት በመቶ ገደማ የሚሆኑት ነጭ ደቡብ አፍሪቃዉያን ሲሆኑ እነዚህ ነጭ ደቡብ አፍሪቃዉያን ዛሬም በአገሪቱ ወደ ሰማንያ በመቶ ያህሉን የእርሻ መሬት በግላቸው የያዙም ናቸዉ። ከዚህ በተጨማሪ ነጭ ደቡብ አፍሪቃዉያን ከጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን ጋር ሲወዳደሩ በ20 እጥፍ ሀብት ያላቸዉ ናቸዉ።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ