የመገናኛ ብዙኀን ሁኔታና መጪው ምርጫ በኢትዮጵያ
እሑድ፣ ታኅሣሥ 12 2018
ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገሪቱ የታሠረ ጋዜጠኛ የሌለባት ሀገር መሆኗ በዜና ተዘግቦ ነበር። ለዓመታት ለጋዜጠኞች የሙያ መብትና ለሰብአዊ መብቶች የሚሟገቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት በጋዜጠኛ አያያዟ ሲወቅሷት የከረሙትን ሀገር አወድሰው የዓለም የፕረስ ነጻነትን ቀን አዲስ አበባ ላይ እንዲከበር ማድረጋቸውም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ብዙም ሳይቆይ ግን የጋዜጠኞች ወከባና እስራት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ መሆኑን የሚገልጹ ዘገባዎች መውጣት ጀመሩ።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎች በቅርቡ ባወጣው ዘገባ፤ ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር አንስቶ የኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች ገለልተኛ መገናኛ ብዙኀን ላይ የሚያደርጉትን ጫና እንደገና ማገርሸቱን ጠቁሟል። ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን በበኩሉ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ጋዜጠኞች መታሠራቸውን፤ ጠቅሶ አሁንም አምስት ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ አመልክቷል። ጋዜጠኞች በሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ምክንያት ለወከባ፤ እስራትና ስደት ብሎም የሥራ መታገድ መጋለጣቸውን ያወገዘው ሂውማን ራይትስ ዎች ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጫና መንግሥት ለገለልተኛ ምርመራና ለሂሳዊ ዘገባዎች ያለውን ጥላቻ ያሳያል ነው ያለው።
ጫና የበረታባቸው መገናኛ ብዙኀን ስጋት እንዳንዣበባቸው በሚነገርበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ 7ተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ ናት። «የመገናኛ ብዙኀን ሁኔታና መጪው ምርጫ በኢትዮጵያ» የዶቼ ቬለ የዚህ ሳምንት የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ነው። ጋዜጠኞችን እና የሰብአዊ መብቶች ባለሙያን በመጋበዝ ውይይቱን አካሂደናል።
ሙሉውን ውይይት ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ
ሸዋዬ ለገሠ