1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመገናኛ ዘዴዎች ሚና በብሔራዊ ምክክር

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 29 2015

የመገናኛ ብዙኃን በአንድ በኩል ከግጭት ቀስቃሽ እና ልዩነት ሰባኪነት ገጽታቸው ካልወጡ እና በሌላ በኩል በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ዐውድ ካልተፈጠረ በስተቀር ለሀገራዊ ምክክሩ እዚህ ግባ የሚባል እገዛ ሊያደርጉ እንደማይችሉ በውይይቱ ተጠቅሷል።

Äthiopien l Rolle der Medien für den Erfolg des nationalen Dialogs in Äthiopien
ምስል Solomon Muchie/DW

በብሔራዊ ምክክሩ ሒደት መገናኛ ዘዴዎች ሚና ምንድነዉ?

This browser does not support the audio element.

                           
ኢትዮጵያ ዉስጥ ሊደረግ የታቀደዉ ብሔራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን መገናኛ ብዙኃን  ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ አተኩረዉ እንዲዘግቡ የሲቪክ ማሕበራት፣የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግስት ጠየቁ። የኢትዮጵያ ሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑን  ተግባርን ለማገዝ ባደረጉት ስምምነት መሰረት ዛሬ ዛሬ መገናኛ ብዙኃን ስለሚኖራቸው ኃላፊነት ተወያይተዋል።

የመገናኛ ብዙኃን በአንድ በኩል ከግጭት ቀስቃሽ እና ልዩነት ሰባኪነት ገጽታቸው ካልወጡ እና በሌላ በኩል በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ዐውድ ካልተፈጠረ በስተቀር ለሀገራዊ ምክክሩ እዚህ ግባ የሚባል እገዛ ሊያደርጉ እንደማይችሉ በውይይቱ ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙት መገናኛ ብዙኃን እውነትን በመሸሸግና የመንግሥ እና የፓርቲ ጉዳዮችን በስፋት በማጉላት ሲሰሩ ይስተዋላሉ።
ከፍተኛ ተጽእኖ እየፈጠሩ የሚገኙት የማሕበራዊ መገናኛ ዐውታቶች በአንፃሩ ጥላቻ ፣ ግጭት እና እርስ በርስ መጠፋፋትን የሚያጎሉ ሥራዎችን ሲያስተጋቡ በብዛት ይታያል። መገናኛ ብዙኃን የጎሳ ፖለቲካው ነፀብራቅ ናቸውና ከዚያ ማእቀፍ ወጥተው በገለልተኝነትና በሙያ ሥነ ምግባር ሊሰሩ ስለማይችሉ ተወቃሽ ሊሆን ከተገባው ሥርዓቱ ነው የሚሉ ብዙ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ የዛሬ ውይይታቸውን ዓላማ ባጭሩ ገልፀዋል።የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ ጀመረ
የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ተወካይ አቶ ታምራት ኃይሉ  መገናኛ ብዙኃን በዚህ የምክክር ሥራ ሂደት ውስጥ ምን እንዲያደርጉ እንደታሰበ እስካሁን ግልጽ አለመሆኑን ነው የሚናገሩት።
"እስካሁን ድረስ ግልጽ ነገር የለም። የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶችም በዚህ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አላቸው። ያንን ማየትም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት የለም ያሉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ይህ ጉዳይ የብሔራዊ ምክክሩ አንዱ አጀንዳ እንዲሆን የጋራ ምክር ቤታቸው ፍላጎቱ መሆኑን ተናግረዋል።
"የሚዲያ ነፃነት ራሱ አንዱ የብሔራዊ ምክክር አጀንዳ ይሆናል የሚል እምነት አለን። የሚዲያን ሚና ማሳነስ አንፈልግም" ብለዋል
የሰላም ሚኒስትር ድኤታ ታዬ ደንደዓ መንግሥታቸው ከሕወሓት ጋር ዘላቂ የተኩስ ማቆም ስምምነት ማድረጉ የብሔራዊ ምክክር ሥራውን እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች በምክክሩ ውስጥ ትጥቅ አንግበው የሚንቀሳቀሱትም ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባል በሚል ውትወታ ሲያደርጉ ይስተዋላል።
ሰሞኑን ነቀምት ከተማ ውስጥ ድረስ በመዝለቅ ጥቃት የከፈተውና በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ግድያ፣ ውድመት እና ዘረፋ የሚፈጽመው መንግሥት ሸኔ የሚለው ታጣቂ ሰራዊት ጋር ብሔራዊ ምክክሩን በተመለከተ የመንግሥትን ምልከታ የተጠየቁት አቶ ታዬ "ከማንኛውም ኃይል ጋር መንግሥት ረጅም ርቀት ሄዶ ወደ መድረክ ማምጣት ይፈልጋል" ብለዋል።የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ትኩረት ምን ሊሆን ይገባል? 

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ተግባርን ለማገዝ ባደረጉት ስምምነት መሰረት መገናኛ ብዙኃን ስለሚኖራቸው ኃላፊነት ተወያይተዋል።ምስል Solomon Muchie/DW

ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነውና 11 ኮሚሽነሮችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ምክንያቶችን ይለያል፣ ብቃት ባለውና በገለልተኛ አካል ውይይት እንዲካሄድባቸው ያደርጋል በዚህም መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ይሰራልም ተብሏል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW