1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 10 ቀን 2016 የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ነሐሴ 10 2016

ምርጫቦርድ ዕውቅና በነፈገውና 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በርካታ ጉባኤተኞች ባልተሳተፉበት ሁኔታ እየተካሄደ ስላለው የህወሓት 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ፤ የዶላር ዋጋን ተንተርሶ የብር የመግዛት አቅም መዳከም በኑሮ ላይ ያሳደረው ጫና የሚሉ ርዕሶች ይገኙበታል።

Social Media App Symbolbild
ምስል Jonathan Raa/NurPhoto/picture alliance

የነሐሴ 10 ቀን 2016 የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

የዛሬ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት በ3 ርእሰጉዳዮች ላይ ያተኩራል። ምርጫቦርድ ዕውቅና በነፈገውና 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በርካታ ጉባኤተኞች ባልተሳተፉበት ሁኔታ እየተካሄደ ስላለው የህወሓት 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ፤ የዶላር ዋጋን ተንተርሶ የብር የመግዛት አቅም መዳከም በኑሮ ላይ ያሳደረው ጫና እንዲሁም በፓሪስ ኦሎምፒክ የኢትዮያ ተሳትፎና ውጤት ላይ ተንተርሰው በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተንሸራሸሩ ሐሳቦች እናቀርባለን።

ማክሰኞ የተጀመረው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ በዝግ ስብሰባውን ቀጥቷል። ስብሰባው ከመጀመሩ በፊትም  የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ራሳቸውን ከጉባኤው ማግለላቸውን በይፋ አስታውቀዋል። ከእነሱ በተጨማሪ  ከተለያዩ አካባቢዎች በጉባኤው ሊሳተፉ ይጠበቁ የነበሩ የፓርቲው አባላት በጉባኤው ሳይሳተፉ ቀርተዋል። እነዚህ ራሳቸውን ከጉባኤው ያገለሉ የህወሓት አባላት እና አመራሮች፥ ጉባኤው የተወሰነ አመራርን ለማጥቃት በችኮላ የተጠራ መድረክ  ነው ሲሉ አውግዘዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫቦርድ በበኩሉ ሕገወጥ ያለውን ጉባኤ የሚያስተላልፈቸውን ውሳኔዎች እውቅና እንዳማይሰጣቸው አስታውቋል። ይህ ጉባኤ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ትኩረት አግኝቷል። ይህን ተንተርሰው ከተሰነዘሩ አስተያየቶች የተወሰኑትን እናከትላለን።
አማኑኤል መኮንን
"በኣለም በውሰጠ ድርጅት መሰብሰብ ሃጥያት በህውሃት ሊሆን ነው ። ጉባኤ ማድረግ ውስጠ ድርጅት ሆኖ ሳለ በትግራይ ሲሆን ቀንዱን እንደተመታ በሬ የምትሆኑ ለምንድነው? ፖለቲካዊ ችግር ቢኖርም በፖለቲካ መፍታት ነው የሚገባው።" ብለዋል። "ይመቻቸው" በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ ምስጋናው አዳነ ናቸው።
"ይመቻቸው...ለማንም የማያሽቃብጡ የራሳቸውንና የራሳቸውን የሚያዳምጡ...አሉ የኛዎቹ አባሎቻቸውን እስርቤት አስገብተው የሚያጨበጭቡ" ።
 ሰሎሞን ሃይሉ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፣
"የሚያሳዝነው አፋርና አማራ ክልል ነው ሁሌም ወላፈኑ የሚለበልበው። የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ግን የተነጠቁትን የክልል ፕሬዚደንትነት ስልጣን በስብሰባው ላይ አንገኝም ያሉትን እነ ጌታቸው ረዳን አባረው ስልጣኑን በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ነው?" በማለት ጥያቄን ያዘለ አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል።

ምስል Annegret Hilse/REUTERS

ዮሃሐንስ ዳዊት ደግሞ እንዲህ ይላሉ፤
"ክቡር ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ሆይ!
በሁሉም ወገን ውድ የህይወት ዋጋ የተከፈለበት ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ህዝባችን አንጻራዊ ሰላም አግኝቷል፤ እንኳንም አገኘ። ይህ አንጻራዊ ሰላም ግን አንድ ክስተት በተፈጠረ ቁጥር እንደ "ማስፈራሪያ ካርድ" ሆኖ የሚቀርበው ለምንድነው? እስከመቼስ ነው ሰላምን የመሰለ ውድ እሴት ለወረደ ፖለቲካችን መቆመሪያ የምንጠቀምበት? ኧረ ነውር ነው!" የሚል አስተያየት ያሰፈሩት ደግሞ ዮሐንስ ዳዊት ናቸው።
ሰው መሆን ይቀድማል በሚል መጠሪያ በፌስቡክ "ከተፃፈ ውጭ ማንበብ ማለት ይሄ ነው። ቆይ ግን ህወሓት ፈረሷል ብሎ ምርጫ ቦርድ መቼ ውሳኔ የሰጠው? እንደ ማንኛውም ፓርቲ በተሻሻለው አዋጅ እንደ አዲስ ተመዝገቡ ተባለ እንጂ ፈርሷል የሚል ተፅፏል ወይ? ምን ነው በግድ ባሩድ ካላሸተትኩኝ አልክሳ ደፂ" 
ደረጀ አየለ ደግሞ፣ "እንዴት ከስህቶቻችን መማር አቃትን ለህዝቡ ማዘን አይሻልም?" የሚል አጭር ጥያቄ አዘል አስተያየት ሰንዝሯል።
ለሁሉም ሰላም የተባሉ አስተያየት ሰጪ፤ "ጉባኤው ጊዜና ገንዘብ ከማቃጠል ያለፈ ምንም ተቀባይነት የለውም በመሆኑም በጥቂት ቀናት ውድቅ ሆኖ ህወሓት ህግን በመተላለፋ ቅጣት ይጠብቀዎል።"
ብሮከር ያሲኖ በሚል መጠሪያ የጻፉት አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይላል፤ "የህወሓት ፖለቲከኞች ከእሩብ ምተዓመት ላቅ ላለ ግዜ የፌዴራል መንበሩን በሃገራዊ ሃላፊነት ሲመሩ የኖሩ ጉምቱ እንደመሆናቸው መጠን አልፎም በተመሳሳይ የህልህ መንገድ የተለኮሰው እሳት ቁስል ገና ጠገግ እንኳ ባላለበት በዚህ የላቀ የሃላፊነት ስሜትን በሚጠይቅ ወቅት በዚህ መንገድ መጓዝ መምረጣቸው በእውነት አጃኢብ ነው። በግሌ የፌዴራል መንግስት ከተመሳሳይ የእልህ መንገድ በመቆጠብ ሃገርና ህዝብን ለዳግም እልቂት የሚዳርጉ በሮችን በመጠርቀም እንደሚሻገር ነው ተስፋዬን የምጥለው።"

ምስል Michael M. Santiago/Getty Images


መንግስት የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ በሸቀጦችና አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ ይገኛል። አለቅጥ እየናረ ያለው ዋጋ ነዋሪዎች መሸከም ከሚችሉት በላይ ነው በማለት ምሬታቸውን ሲገልጹ እየተደመጡ ነው። መንግስት በበኩሉ የዶላር ዋጋ መጨመርን ተንተርሰው ዋጋ ጨምሯል ባላቸው ነጋዴዎች ላይ ስቆቻቸውን የማሸግ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ገልጿል። በአንጻሩ መንግስታዊ ተቋማት የሆኑት እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዳደረጉ ሲነገር፤ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎትም ጭማሪ ለማድረግ እያኮበከበ ነው ተብሏል። በዚህ ላይ ከተሰነዘሁ አስተያየቶች የተወሰኑትን እናቀርባለን።
የሪያድ ማሕበረሰብ ድምጽ በሚል መጠሪያ የሚጠሩ አስተያየት ሰጪ
"በዶላር ዋጋ መጨመር ምክንያት በማህበረሰቡ የተለያዩ ፍጆታዎች ላይ የተጋነነ ዋጋ በሚቆልሉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚደነቅ ቢሆንም በስሩ ያሉ ህዝባዊ ተቋማት በተለያየ አገልግሎቶቻቸው ላይ በማን አለብኝነት ያስቀመጡት ተመን ከስግብግብ ነጋዴዎቹ የከፋ በመሆኑ ድሮ ተማሪ እያለን "መንግስት ማለት የመበዝበዣ መሳሪያ ነው" የሚለውን ሀረግ ያስተማሩንን የፖለቲካ መምህራችንን እንድናስታውስ አድርጎናል።" ብለዋል።
ዑመር ሙሄ ደግሞ "ሁለት አምፑል ተጠቅሜ የሐምሌን ወር 680 ብር ከፍያለሁ። በዚህ ስንማረር ደግሞ ሌላ በየሶስት ወር 10% ጭማሪ ብሎት አረፈው? ህዝብ መምራት ካልቀረ እንዲህ ነው። ዕዳን ለመክፈል ህዝብን መግፈፍ ምን ማለት ነው? የህዝቡን ስነልቦና በደንብ ተረድታችኋል።ምንም ብናደርገው እያለቀሰ ይኖራል እንጂ እንደሌላ ሀገር መብቱን ለማስከበር መቼም አይነሳም ብላችሁ ነው?" በማለት ይጠይቃሉ። ወደ ሌላ አስተያየት አለፍን፤
"የኢት/ያ ኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ለሕዝብ የማያስብ ድርጅት ከደሐው ሕዝብ የሚሰበስብ ገንዘብ በመተማመን ደመወዛቸውን በየዓመቱ ከመጨመራቸው ባለፈ ውድ ሕንጻዎችን በተጋነነ ዋጋ እየተከራዩ ላልተገባ ወጭ ራሳቸውን ዳርገው በሕዛባችን ላይ ዕዳቸውን ለማራገፍ ሲሞክሩ መንግሥት የሌለበት ሀገር ያስመስላል" የሚል አስተያየት የጻፉት ሲዝን ደበላ የተባሉ ናቸው። 
በጎሰው ስሜነት ደግሞ "አባይን የገደብነው ታሪፍ እንዲጨመር ነው እንዴ?" በማለት ይጠይቃሉ።
"የብር አቅም እንዲዳከም ከመደረጉ በፊት ራሱ የኑሮ ውድነት አላፈናፍን ብሎ ነበር። ይህ አልበቃ ብሎ ደግሞ የብር አቅም በግማሽ ሲቀንስ ሁሉም ነገር በጣም መጨመሩ አይቀሬ ነው። በፊት ያመጣኸውን ዕቃ ለምን ትጨምራለህ ስትለው አሁን ዕቃ ለማምጣት ስለሚከብደኝ ነው ይላል። ነገሩ በአጭሩ እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል።" የሚል አስተያየት የጻፉት ደግሞ ገዛኸኝ ገብሬ ናቸው።
የሺዋስ ጌታሁን ደግሞ በአጭር ግጥም እንዲህ ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል
"እንዴት ይገለፃል ምንስ ቃል ተገኝቶ
በኑሮ ውድነት መኖራችን ሙቶ"

ምስል Sebastian Kahnert/dpa/picture alliance

መብራቱ ከበደ ደግሞ ተከታዩን አስተያየት አስፍሯል።
"እኛ መንግስት መንግስት መሆኑን የማናቅበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ። በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ ሆነና ነገሩ ቀደም ሲል የነበረውን የኑሮ ውድነት ያልቀለበሰው መንግሰት ተብዬ በአሁኑ ሰዓት የበለጠ ቤንዚን መጨመሩን አረጋግጦልናል ።ቀደም ሲል 600 ብር ይሸጥ የነበረ 3 ሊትር ዘይት አሁን 1,200 ብር ገብቷል ።
ነጋዴው ቀደም ሲል በርካታ ዘይትን ከውጭ አጓጉዞ አስገብቶ በተለያዩ ቦታዎች ከዝኖ በማስቀመጥ በ600 ብር ሺያጭ የለም ሲል የነበረውን አሁን 1,200 ብር ሺያጭ በሚስጥር ቦታዎች መቸብቸብ ጀምሯል ።
ታሸጓል የሚባለው ቦታ ሌላ፤ ዘይት ያለው ሌላ ቦታ።  የማይሆን ስራ ከመሰራቱም ውጭ እንዳማራጭ መታሸግ በራሱ ሌላ ተጨማሪ የዋጋ ንረት እንጂ ለውጥ እንደማያመጣ ቀደም ሲል ሲሰራበት ስለነበረ ግልጽም ነበር ።
ነገር ግን በነጋዴው እንዳይፈረድ መንግሰት በራሱ እጅ በያዛቸው የንግድ አውታሮች ላይ ማቆሚያ የሌለው ጭማሪ ማሳየቱ ለህዝብ ማሰብ ከሆነ የአለም ማህበረሰብ ይፍረደው ከማለት ውጭ ለጊዜው የምንለው የለንም ።
በትቂቱ ዘይትን ለምሳሌ ጠቅሰን እንጂ የምግብ እህል ሸቀጣሸቀጥ በሙሉ እጥፍ ጨምረዋል ።
አሁን ህዝባችን ያለው ተስፋ የፈጠረውን ፈጣሪውን ብቻ በማመን እሱ የከፈተውን ጉሮሮ እሱው ሳይዘጋው አያድርም የሚለውን መርህ ብቻ በመያዝ ጾሎቱን በማድረግና በማልቀስ ላይ ብቻ ይገኛል። በመጨረሻም ህዝባችን የሚለው የነጋዴውን ድርጀት ማሸጉ በፍጹም መፍትሄ አይሆንም ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ቤንዚን የጨመረው እራሱ መንግሰት ነው እንላለን ።"

ምስል Jaap Arriens/NurPhoto/picture alliance


በፓሪስ ኦሎምፒክ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ማራቶን ቡድን አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ ከኢትዮጵያ መንግስት የተበረከተላቸውን የሁለት ሚሊዮን ብር ሽልማት አልቀበልም ብሏል ። አሰልጣኙ ይህን ያሉት ማክሰኞ ምሽት በብሔራዊ ቤተመንግስት ዉጤት ላመጡ የኦሎምፒክ የልዑካን ቡድን አባላት በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሽልማት በተበረከተበት ወቅት ነው ።
አሰልጣኙ በፕሬዚዳንቷ የቀረበላቸውን የሁለት ሚሊዮን ብር ሽልማት ከተቀበሉ በኋላ ባደረጉት ንግግር «በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ እኔ  ሁለት ወርቅ እና ብር እንዲሁም ዲፕሎማ ተጋድዬ ለዚህ ሀገር አስመጥቼ  ለእኔ ሁለት ሚሊዮን የስድብ ያህል ስለሆነ እርስዎን ካላስከፋዎት ይህንን ሽልማቴን መመለስ እፈልጋለሁ ፤ ለሚመጣው ሁሉ እቀበላለሁ ።» ብለዋል።
አሰልጣኙ የሽልማት ገንዘቡን አልቀበልም ማለታቸው እና ያደረጉት ንግግር በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ በአንድ በኩል የወቀሳ እና ትችት አስተያየቶችን ሲያስተናግዱ ሽልማቱ አንሶባቸዋል የሚሉ አስተያየቶችንም በስፋት አስተናግዷል። የተወሰኑትን እናቀርባለን።
"እኔ እኮ የመሠለኝ ለሀገሬ ማድረግ የሚገባኝን ነው ያርኩት፤ ሸልማቴ ሀገሬ ሰታሸንፍ ማየት ነው፤ ያለ መሰሎኝ ነበር አነሰኝ ብሎ ነው እንዴት? ልቦና ይሰጥህ ወደ ቀልብህ ተመለስ" የሚል አስተያየት የጻፉት ይዘንጋል እስከመቼ ናቸው።
ዘነበ መልካ "በአሰልጣኙ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ታምራት ባልተሳተፈ ነበር፡፡ሰለሞን እንዲወዳደር እድሉን ባይሰጠው ኖሮ ወርቁም አይገኝም ነበር፡፡ ስለዚህ ጥሩ ነገር እንደ ሰራ ሰው ሽልማትም አይገበውም ባይ ነኝ፡፡በአትሌቱ ጥረትና ድካም የተገኘ ውጤት ነው፡፡" ብለዋል።
አንዋር አወል ደግሞ
"ያንስብኛል ማለቱ ትክክል ነው። እነሱ የቤተዘመድ መዝናኛ  ያደረጉትን የሃገሪቱን በጀት በስራ ለደከመ አሰልጣኝ ከሰራው በታች መክፈል ፍጹም ተገቢ አይደለም። ሁላችንም እንደምናውቀው ለተሳትፎ ማያበቃ አንድ እንኳን ለውጥ ለማያሳዩ የብሔራዊ ብድናችን አሰልጣኞች የሚከፈለውን እናውቃለን። የአንድ የጥበብ ባለተሰጦ የሙዚቃ ውድድር አሸንፎ ሲመጣ እንኳን በወረዳ ደረጃ ወረዳችንን አስጠራህ ተብሎ የሚበረከትለት ሽልማት ከዚህ የተሻለ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። አዎ ትክክል ነው አይገባውም አይመጥነውም!"

 ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 
ኂሩት መለሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW