1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመገጣጠሚያ ህመም መንስኤዎችና መፍትሄ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ማክሰኞ፣ መስከረም 13 2018

መገጣጠሚያ አካል ላይ የሚከሰት ህመም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ቁርጥማት ተብሎ የሚታወቀው ማለት ነው መነሻው ምን እንደሆነ የሚጠይቁ ጥቂት አይደሉም። ስለዚህ የጤና ችግር የህክምና ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

የመገጣጠሚያ አካላት ህመም
የመገጣጠሚያ አካላት ህመም መንስኤዎቹ በርካታ እንደሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዚህ የጤና ችግር በርካቶች እየተሰቃዩ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አመልክቷል። ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Christin Klose/dpa-tmn/picture alliance

የመገጣጠሚያ ህመም መንስኤዎችና መፍትሄ

This browser does not support the audio element.

 

የመገጣጠሚያ አካላት ህመም ዕድሜ ይወስነዋል?

የመገጣጠሚያ ላይ ህመም የተለያዩ መንስኤዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። አብዛኛውን ጊዜ ግን በዋና ምክንያትነት ከሚነሱት ውስጥ በአጥንቶች መካከል የሚገኘው ከአጥንት የለሰለሰ ከሥጋ የጠጠረ ክፍል ካርቲሌጅ የሚባለው አጥንት እንዳይፋተግ የሚረዳ የተፈጥሮ መጠበቂያ ማለቅ የሚያስከትለው ህመም አንዱ ነው። ይህ ችግር ቀስ በቀስ በዕድሜ ሂደት የሚከሰት ሲሆን በተለይ ከ45 ዓመት በኋላ ሊባባስ እንደሚችል የሚመለክቱ መረጃዎች አሉ። ይህ በሚከሰትበት ጊዜም የመገጣጠሚያ አካላት ላይ ጠንካራ የህመም ስሜት ይፈጠራል። በአጥንትና መገጣጠሚያ አካል ላይ የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮችን ለረዥም ዓመታት ሲያክሙ የኖሩት ዶክተር ውብታዬ ግን የመገጣጠሚያ አካላት ህመም እንደውም የዕድሜ ገደብ የለውም ነው የሚሉት።

የመገጣጠሚያ አካል ህመም መንስኤውዎቹ ብዙ ናቸው

ለመሆኑ የመገጣጠሚያ አካል ህመም መንስኤው ምን ይሆን? ያልናቸው ዶክተር ውብታዬ እንደነገሩን እንደየሰው እና አጋጣሚው መንስኤዎቹ የተለያዩ ናቸው። ዕድሜን ተከትሎ የሚከሰት እንዳለ ሁሉ፤ በልጆችና በወጣቶች ላይ ሳይቀር የመገጣጠሚያ ህመም ሊያጋጥምም ይችላል። ከአደጋና ከሌላ ህመም ጋር በተገናኘ የመገጣጠሚ ህመም የሚመጣበት ጊዜ አለ ያሉት ባለሙያው በተለይ ለሴቶች ከወር አበባ ዑደት መቆም ጋ በተያያዘም ህመሙ ሊከተል እንደሚችልም አስረድተዋል።

የሰውነት ክብደት መጨመር፤ የአካል እንቅስቃሴ አለማዘውተር፤ የሥራ ጫና እና ጉልበት የሚጠይቁ ከባድ እንቅስቃሴዎች፤ ያልተመጨ ጫማ፤ ወለምታ፤ መጋጨት፤ ከስፖርት እንቅስቃሴ ጋ የተገናኘ አደጋም ሆነ አጉል እንቅስቃሴ የመገጣጠሚያ አካላትን ህመም ሊያስከትሉ እንደሚችሉም ዘርዝረዋል። 

በእጅ ጣቶች መገጣጠሚያ ላይ ሳይቀር ህመም የሚኖርበት አጋጣሚ እንዳለ ያመለከቱት ባለሙያው በአብዛኛው ከሥራ ብዛት ጫና ጋር እንደሚገናኝም ነው ያስረዱት። ህመሙ አንዳንዴም የጣቶችን ቅርጽ እስከመቀየር ሊደርስ ይችላልም ባይ ናቸው። ከዚህም ሌላ የአመጋገብ ጉድለት እና አልክሆል ማዘውተርም ሌላው የችግሩ አባባሽ ምክንያቶች መሆናቸውንም ሳይገልጹ አላለፉም።

የመገጣጠሚያ አካላትን ከሚጎዳው ህመም አንዱ የጣቶች ቅርጽ እንዲቀየር ሁሉ ያደርጋል። ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ David Herraez Calzada/Zoonar/picture alliance

የአመጋገብ ጉድለትን ለማካካስ በሚል የሚወሰዱ ተጨማሪ ቫይታሚኖችና ማዕድናትን መውሰድን ባይነቅፉም በጥናት የተረጋገጠ ነገር ግን አንዳላገኙ ተናግረዋል። እንዲህ ያሉትን ተጨማሪ ቫይታሚን እና ማዕድናትን የሚያዘጋጁ ኩባንያዎች በበኩላቸው ጠቀሜታቸውን ደጋግመው በመዘርዘር ማስታወቂያዎችን በስፋት ያሰራጫሉ። ጥቂት የማይባሉ ደንበኞችም አሏቸው።

መፍትሄ ይኖረው ይሆን?

መነሻ ምክንያቱ በርካታ መሆኑ የተገለጸለት የመገጣጠሚያ አካል ህመም መፍትሄው ምን ይሆን የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ወደሀኪም መሄድ ግድ የሚለው የተባባሰና ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ከሆነ መሆኑን ያሳሰቡት ዶክተር ውብታዬ እንደሚሉት በአብዛኛው ዋነኛው መፍትሄው መንቀሳቀስ ነው። ክብደት መቀነስ፤ የስፖርት እንቅስቃሴዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ፤ ምቹ ጫማ ማድር,ግና አመጋገብን በጥንቃቄ መከታተልንም መክረዋል።  

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በመላው ዓለም በርካታ ሰዎች በመገጣጠሚያ ህመም ይሰቃያሉ። መነሻ ምክንያቱ የተለያየ እንደመሆኑም ህክምናውም እየደየሰው ህመምና የመንቀሳቀስ አቅም ጋ ይገናኛል። የዓለም የጤና ድርጅትም ሆነ እዚህ ጀርመን ሀገር በአጥንት እና መገጣጠሚያ ላይ የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮችን ለረዥም ዓመታት ሲያክሙ ከቆዩት ዶክተር ውብታየ ዱሬሳ ተክሌ የጋራ ምክራቸው ለዚህ ችግር የተሻለ መፍትሄ ህመም እየተሰማም ቢሆን እንቅስቃሴ ማዘውተር የሚል ነው። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ እና ምክር የዘወትር ተባባሪያችን የሆኑትን በአጥንትና መገጣጠሚያ አካል ላይ የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮችን ለረዥም ዓመታት ሲያክሙ የኖሩት ዶክተር ውብታዬ ዱሬሳ ተክሌን ከልብ እናመሰግናለን። 

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW