1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 12 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ መጋቢት 12 2014

የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ በነገሰበት የኤል ክላሲኮ ምሽት ባርሴሎና ሪያል ማድሪድን በሜዳው ጉድ አድርጎታል። በድል ላይ ድል እየተቀዳጀ ያለው ወጣቱ የባርሴሎና አሰልጣኝ ዣቪ ኼርናንዴዝ፦ የፓሪ ሳንጃርሞ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ወደ ባርሴሎና ቢመለስ እጃችን ዘርግተን እንቀበለዋለን ብሏል። ኢትዮጵያ በቤልግሬድ የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ገናለች።

Fußball Real Madrid - FC Barcelona 0:4
ምስል Marca/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ በነገሰበት የኤል ክላሲኮ ምሽት ባርሴሎና ሪያል ማድሪድን በሜዳው ቤርናቤዮ ጉድ አድርጎታል። በድል ላይ ድል እየተቀዳጀ ያለው ወጣቱ የባርሴሎና አሰልጣኝ ዣቪ ኼርናንዴዝ፦ ከሻምፒዮንስ ሊግ በሪያል ማድሪድ የተሰናበተው ፓሪ ሳንጃርሞ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ በማንኛውም ሰአት ቢመጣ እጃችን ዘርግተን እንቀበለዋለን ብሏል። በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ሊቨርፑል ትናንት ኖቲንግሀም ፎረስትን በትግል አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፏል።  ዋነኛ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲ ይጠብቀዋል። ሲቲ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰው ተጋጣሚውን በሰፊ የግብ ልዩነት ድባቅ መትቶ ነው። አርሰናል በሚቀጥለው ዙር የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ የመሆን ዕድሉን አስፍቷል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታው ላይ የቅዳሜ ድሉን ከደገመ በፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ የሚከተለው ቶትንሀምን በስድስት ነጥብ ርቆ ቸልሲን በ2 ነጥብ ልዩነት ይጠጋል። በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በኮይልን ነጥብ ሲጥል፤ መሪው ባየርን ሙይንሽን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል። 

ኤል ክላሲኮ

በኤል ክላሲኮው የትናንት ምሽት ውብ ግጥሚያ ባርሳ ሪያል ማድሪድን በሜዳው ቤርናቤዮ 4 ለ0 ድባቅ መትቶታል። ጋቦናዊው አጥቂ ፒዬር-ኤመሪክ ኦባሜየያንግ በ29ኛው እና 51ኛው ደቂቃዎች ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ የምሽቱ ጨዋታ ንጉሥ ተሰኝቷል። ቀሪዎቹ ሁለት ግቦች የአራውዮ እና ቶሬዝ ናቸው። በላሊጋው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ባርሴሎና በመሪው ሪያል ማድሪድ በ12 ነጥብ ይበለጣል። ሴቪያ በ57 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ምስል Just Pictures/IMAGO

በትናንቱ ግጥሚያ ፒዬር-ኤመሪክ ኦባሜየያንግ ካስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ባሻገር ተቀይሮ እስኪወጣ ድረስ አንድ ለግብ የሚሆን ኳስም አመቻችቶ ነበር። የትናንቱ ብቃቱን የተመለከተው አርሰናል መቼም መቆጨቱ የማይቀር ነው። አርሰናል የ32 ዓመቱ አጥቂ ፒዬር-ኤመሪክ ኦባሜየያንግ ቡድኑን ጥሎ እንዲኼድለት 8 ሚሊዮን ዩሮ ከከፈለው ብዙም አልቆየ። 8 ሚሊዮኑን ይዞ ወደ ስፔን እብስ ያለው ጋቦናዊን ባርሴሎና ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ሲያስፈርመው 100 ሚሊዮን ዩሮ ከፍሎት ነው። ያም ብቻ አይደለም። በውሉ መሠረት የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ ከአንድ ዓመት በኋላ ቢፈልግ ወደ ሌላ ቡድንም መቀየር ይችላል። በእርግጥ አርሰናል በቆይታው ብዙም ላልፈየደለት አጥቂ በሳምንት 420.000 ዩሮ ከመክፈል በ8 ሚሊዮን መገላገሉ ይሻለኛል ብሎ ነበር ያሰናበተው። ፒዬር-ኤመሪክ ኦባሜየያንግ ባርሴሎና ውስጥ ዳግም እያበበ ነው። ለባርሴሎና የትናንት አመርቂ ድል ከፒዬር-ኤመሪክ ኦባሜየያንግ በተጨማሪ ሌላኛው የቀድሞ የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋቾች ዖስማኔ ዴምቤሌም አስተዋጽዖው ከፍተኛ ነበር። ግብ የሚሆኑ ኳሶችን እየመጠነ በማቀበል ብቃቱን ዐሳይቷል።

ውብ ጨዋታ እናሳያለን ላለው የባርሴሎናው ወጣቱ አሰልጣኝ ዣቪ ኼርናንዴዝ በእርግጥም የትናንቱ ድል ውብ ጨዋታ ያሳየበት ነበር። በኤል ክላሲኮው በሪያል ማድሪድ በተደጋጋሚ የመሸነፍ ታሪክንም ቀይሯል። ዣቪ ባርሴሎናን በአሰልጣኝነት ከያዘው ጀምሮ ድል በድል እየሆነ ነው። ዣቪ ከጨዋታው በፊት በሰጠው ቃለ መጠይቅ፦ የቀድሞው የክለቡ ፈርጥ ሊዮኔል ሜሲ በማንኛውም ጊዜ ተመልሶ ቢመጣ እጃችን ዘርግተን እንቀበለዋለን ብሏል። ሊዮኔል ሜሲ ቡድኑ ፓሪ ሳንጃርሞ ከሻምፒዮንስ ሊጉ ከተሰናበተ በኋላ የሱ በቡድኑ መቆየት አጠያያቂ ሆኗል። በጉዳት የተነሳ ያለ ዋና አጥቂያቸው ካሪም ቤንዜማ ተጨዋቾቻቸውን ወደ ሜዳ የላኩት የሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ለትናንቱ ሽንፈት ጥፋተኛ መሆናቸውን ገልጠዋል። ከ1 ለ 0 በኋላ ባርሴሎና ያገኘውን አጋጣሚ በሙሉ እንደተጠቀመ ቡድናቸው ጨዋታውን መቆጣጠር እንደተሳነው ተናግረዋል። ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት የተጨዋች ለውጥ ውጤት ባለማምጣቱም በሜዳቸው ለደረሰባቸው ከፍተኛ ሽንፈት ተጠያቂ ራሳቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። ሁሉንም ነገር ረስተው ወደፊት መገስገስ እንደሚሹም በቁርጠንነት ዐስታውቀዋል።

ምስል Marc Gonzalez Aloma/Action Plus/imago images

ኤፍ ኤ ካፕ

ትናንት ክሪስታል ፓላስ ኤቨርተንን በሰፊ የግብ ልዪነት 4 ለ0፤ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ሳውዝሀምፕተንን 4 ለ1 አንኮታተዋቷል። ሊቨርፑል በዲዬጎ ጆታ ብቸኛ ግብ ኖቲንግሀም ፎረስትን 1 ለ0 አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊቨርፑል ጎልቶ ቢታይም ያለ ግብ ነበር የተጠናቀቀው። ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፉን ለማረጋገጥ እስከ 78ኛው ደቂቃ ድረስም መጠበቅ ነበረበት። በግማሽ ፍጻሜው ዋነኛ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲን ከአንድ ወር በኋላ ሚያዝያ 8 አለያም 9 ዌምብሌ ስታዲየም ውስጥ ይገጥማል። ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ የትናንቱን የኤፍኤ ካፕ ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ የሻምፒዮንስ ሊግ አይነት ፍልሚያ ሲሉ ጠንካራ የነበረው ተጋጣሚያቸውን አወድሰዋል። ከትናንት ወዲያ ቸልሲ ሚድልስቦቶውን 2 ለ0 አሸንፏል። በግማሽ ፍጻሜው በዌምብሌ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ይፋለማል።

ምስል Andrew Couldridge/REUTERS

ፕሬሚየር ሊግ

ቶትንሀም ሆትስፐር ዌስትሀም ዩናይትድን ትናንት 3 ለ1 ድል አድርጓል። ላይስተር ሲቲ በበኩሉ ብሬንትፎርድን 2 ለ1 አሸንፏል። ቅዳሜ ዕለት አርሰናል አስቶንቪላን 1 ለ0 ድል ሲያደርግ፤ የዋትፎርድ እና ኤቨርተን ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።  በፕሬሚየር ሊጉ ማንቸስተር ዩናይትድ 50 ነጥብ ይዞ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቶትንሀም በ51 ነጥብ ከበላዩ ሰፍሯል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው አርሰናል 54 ነጥብ ይዞ ደረጃው አራተኛ ነው። ቸልሲም አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 59 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሊቨርፑል እና መሪው ማንቸስተር ሲቲ በአንድ ነጥብ ብቻ ይለያያሉ። 70 ነጥብ ይዞ ፕሬሚየር ሊጉን የሚመራው ሲቲ በግብ ክፍያ በሊቨርፑል በ5 ይበለጣል። ዋትፎርድ፣ በርንሌይ እና ኖርዊች ከ18ኛ እስከ 20 የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተደርድረዋል።

በቡንደስሊጋ

ምስል Meuter/nordphoto GmBH/picture alliance

ትናንት ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከኮይልን ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። በደረጃ ሰንጠረዡ ከመሪው ባየርን ሙይንሽን በ6 ነጥብ ይበለጣል። ባየርን ሙይንሽን ቅዳሜ እለት ኡኒዮን ቤርሊንን በሰፊ የግብ ልዩነት 4 ለ0 አሸንፎ ነጥቡን 63 አድርሷል። በእለቱ ማይንትስ በተመሳሳይ የግብ ልዩነት ቢሌፌልድን 4 ለ0 ሸኝቷል፤ ደረጃው 10ኛ ነው። ትናንት ባዬርን ሌቨርኩሰን ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 ሲያሸንፍ፤ ላይፕትሲሽ ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ባዬርን ሌቨርኩሰን 48 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ላይፕትሲሽ በ45 ነጥብ ይከተለዋል።

አትሌቲክስ

በቤልግሬድ 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ አራት ወርቅ፤ ሦስት የብር እና ሁለት የነሐስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በወርቅ ብዛት ዩናይትድ ስቴትስን እና ቤልጂየምን አስከትላ ከዓለም አንደኛ ወጥታለች። በአጠቃላይ የሜዳሊያ ብዛት ደግሞ ከአሜሪካ ቀጠላ በ2ኛነት አጠናቃለች። የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ኢትዮ ስፖርት አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ ጥቂት አትሌቶችን በተወሰኑ የርቀት ዘርፎች አሳትፈን አራት ወርቅ ማግኘታችን በጣም ትልቅ ውጤት ነው ብሏል። 

ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙት፦ በ1,500 ሜ. ወንዶች ፍፃሜ፦ ሳሙኤል ተፈራ፤ በ3000 ሜ. ወንዶች ፍፃሜ፦ ሰለሞን ባረጋ፤ በሴቶች 1,500 ሜ. ፍፃሜ፦ ጉዳፍ ጸጋይ፤ የሴቶች 3,000 ሜ. ለምለም ኃይሉ ናቸው። በውድድሩ ኢትዮጵያ 14 አትሌቶችን፣ 4 አሰልጣኞችን እና 6 የልዑካን ቡድን ይዛ መሳተፏን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጧል።

ኒውዮርክ በተካኼደው የግማሽ ማራቶን ሩጫ ፉክክር ደግሞ ሰንብሬ ተፈሪ ኬኒያዊቷ ሯጭ ኢሬኔ ቼፓቲን ጥሳ አንደኛ በመውጣት ለድል በቅታለች። ሰንበሬ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 1 ሰዓት ከ7 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ ነበር። በወንዶች ፉክክር ኬንያዊው አትሌት ሮኔክስ ኪፕሩቶ አንደኛ በመሆን አጠናቋል። የሀገሩ ልጅ ኤድዋርድ ቼሴሬክ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። በዚህ ውድድር በሦስተኛነት ያጠናቀቀው ኢትዮጵያዊው አትሌት ተሾመ መኮንን ነው። አትሌቱ በውድድሩ መጨረሻ እጆቹን ከፍ አድርጎ በማጣመር የትግራይ ክልልን በተመለከተ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ ላይ ፖለቲካዊ ተቃውሞውን አሰምቷል።

ፎርሙላ አንድ

ምስል Diederik Van Der Laan/DPPI/picture alliance

የጀርመኑ አውዲ የመኪና አምራች ኩባንያ በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ማመልከቱ ተሰምቷል። ከአውዲ በተጨማሪም ሌላኛው የአውዲ ንብረት የሆነው ፎልክስቫገንም በፎርሙላ አንድ ተሳታፊ ለመሆን ከፎርሙላ አንድ የውድድር አዘጋጆች ጋር ንግግር ጀምሯል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የጀርመኑ መርሴዲስ የረዥም ጊዜ የውድሩ ባለድል ነው። በፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም ተሳታፊ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች አዲስ በወጣው ሕግ መሠረት፦ ከሚቀጥሉት አራት ዓመታት በኋላ መቶ በመቶ የተፈጥሮ ነዳጅ ሳይሆን በዘላቂ ታዳሽ ኃይል የሚገኙ ነዳጆችን መጠቀም ይገባቸዋል።

በፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም ለ103 ጊዜ ባለድል የሆነው የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ትናንት በባሕሬን ውድድር ያገኘው ሦስተኛ ደረጃ እንዳስደሰተው ተናግሯል። ለሰባት ጊዜያት የፎርሙላ አንድ የዓለም ባለድል መሆን የቻለው ብሪታንያዊ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን፦ «ይህ ድንቁ ውጤት ነው» ብሏል በአስቸጋሪ ሁኔታ ከአምስተኛ ደረጃ ተነስቶ ባገኘው ውጤቱ። በምሽቱ ፉክክክር የፌራሪው አሽከርካሪ ሻርል ሌክሌር አንደኛ ደረጃን ይዞ 26 ነጥብ አግኝቷል። ሌላኛው የፌራሪ አሽከርካሪ ካርሎስ ሳይንስ ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ሲያጠናቅቅ 18 ነጥብ አግኝቷል። ሌዊስ ሐሚልተን ለሦስተኛ ደረጃ የሚሰጠውን 15 ነጥብ አግኝቷል።   

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW