1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመጋቢት 15 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 15 2017

በቻይና ናንጂንግ የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ ዩናይትድ በ3ተኛ ደረጃ አጠናቃለች ። በግብጽ የ2 ለ0 ሽንፈት ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከጅቡቲ ጋር ዛሬ ማታ ይጋጠማል ። በአውሮጳ የኔሽንስ ሊግ ጀርመን ከፖርቹጋል ሙይንሽን አሬና ውስጥ፤ ስፔን ከፈረንሳይ ጋር ደግሞ ሽቱትጋርት አሬና ውስጥ ይጋጠማሉ ።

በ1500 ሜትር ርቀት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ በ(3:54.86)ሮጣ ስታጠናቅቅ ክብረወሰን ጭምር በመስበር  ነበር ።  አትሌት ድርቤ ወልተጂ ጉዳፍን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች
በ1500 ሜትር ርቀትም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ በ(3:54.86)ሮጣ ስታጠናቅቅ ክብረወሰን ጭምር በመስበር  ነበር ። የአገሯ ልጅ አትሌት ድርቤ ወልተጂ ጉዳፍን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች ምስል፦ Dar Yasin/AP/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በቻይና ናንጂንግ ከተማ የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክር  ኢትዮጵያ  ዩናይትድ ስቴትስ እና ኖርዌይን ተከትላ በሦስተኛ ደረጃ አጠናቃለች ። Ethiopiaበግብጽ የ2 ለ0 ሽንፈት ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከጅቡቲ ጋር ዛሬ ማታ ሞሮኮ ውስጥ ይጋጠማል ። በአውሮጳ የኔሽንስ ሊግ እግር ኳስ በግማሽ ፍጻሜው ጀርመን ከፖርቹጋል ሙይንሽን አሬና ውስጥ፤ ስፔን ከፈረንሳይ ጋር ደግሞ ሽቱትጋርት አሬና ውስጥ ይጋጠማሉ ። 

አትሌቲክስ

ቻይና ናንጂንግ ከተማ ውስጥ ትናንት (መጋቢት 14 ቀን፣2017 ዓ.ም) በተጠናቀቀው የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ ብሪታንያ እና ጣሊያንን አስከትላ ከዓለም በ3ኛ ደረጃ አጠናቃለች ። ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሠንጠረዥ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ኖርዌይ ቀጥላ በሁለት የወርቅ እና ሦስት የብር ሜዳሊያዎች የሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ።  ለኢትዮጵያ ከተገኘው አምስት ሜዳሊያዎች ውስጥ በአትሌት በሪሁ ኃይሉ ከተገኘው የብር ሜዳሊያ በስተቀር የተቀሩት በአጠቃላይ በሴት አትሌቶቻችን የተገኙ ናቸው ። ሁለቱን የወርቅ ሜዳሊያዎች ያስገኙት ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ፍሬወይኒ ኃይሉ እና ጉዳፍ ጸጋዬ ናቸው ። 

በሴቶች የ3000 ሜትር ርቀት ፍጻሜ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ድል ተጎናጽፋ የወርቅ ሜዳሊያ ለማጥለቅ የፈጀባት ጊዜ (8:37.21)ነው ። ብርቱ ፉክክር በታየበት የ3000 የፍጻሜ ሩጫ፦ ሜትር አሜሪካዊቷ ሼልቢ ሁሊሃን ፍሬወይኒ ኃይሉን በአንድ ነጥብ አምስት ሰከንድ ተከትላ ሁለተኛ ወጥታለች ። የአውስትራሊያዋ ሯጭ ጄሲካ ሁል ከሼልቢ በሁለት ማይክሮ ሰከንድ ተበልጣ ነው ሦስተኛ የወጣችው ። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ብርቄ ኃየሎም አሜሪካዊቷ ዊትኒ ሞርጋንን ተከትላ የአምስተኛ ደረጃ አግኝታለች ።

በ1500 ሜትር ርቀትም ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ  በ(3:54.86) ሮጣ ስታጠናቅቅ ክብረወሰን ጭምር በመስበር  ነበር ። የአገሯ ልጅ አትሌት ድርቤ ወልተጂ ጉዳፍን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች ። አትሌት ድርቤ ወልተጂ ከጉዳፍ በአራት ነጥብ ዐርባ አራት ሰከንድ ተከትላ በመግባት (3:59.30) የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች ። ብሪታንያዊቷ አትሌት ጆርጂያ ሁንተር ቤል ሦስተኛ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሁናለች ።

በቻይና ናንጂንግ ከተማ የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክር በ1500 ሜትር ርቀት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ውድድሩን ስትመራምስል፦ Dar Yasin/AP/picture alliance

የኢትዮጵያ አመርቂ ድል

በወንዶች የ3000 ሜትር የፍጻሜ ሩጫ ደግሞ ኢትዮጵያዊው አትሌት በሪሁ አረጋዊ (7:46.25)በመሮጥ የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል ።  ኖርዌያዊው አትሌት ጄኮብ ኢንገርብሪግስተን በሪሁን ቀድሞ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው ከአንድ ሰከንድ ባነሰ 16 ማይክሮ ሰከንድ ለጥቂት ቀድሞ ነው ። የአውስትራሊያው ኪይ ሮቢንሰን ሦስተኛ ደረጃ ሲያገን፥ አንደኛ ከወጣው ኖርዊያዊ አትሌት የተቀደመው በአንድ ሰከንድ ብቻ ነበር ። ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ቢንያም መሐሪ እና ጌትነት ዋለ ኤርትራዊው ዳዊት ሠዓረን ከመሀል አድርገው 9ኛ እና 11ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቅቀዋል ። የጀርመኑ ሣም ፓርሶናስ 12ኛ ደረጃ አግኝቷል ።

በትናንትናው የ800 ሜትር የሴቶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት ንግሥት ጌታቸው ሁለተኛ በመሆን ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች ። የገባችበት (1:59.63) የግሏ ምርጥ ሰአት ሁኖ ተመዝግቧል ።  በውድድሩ ከፍተኛ ቅድመ ግምት አግኝታ የነበረው የአምና ሻምፒዮና ጽጌ ዱጉማ (2:04.76) ስድስተኛ በመሆን አጠናቃለች ። የ800 ሜትር ርቀት የፍጻሜ ውድድሩን አሸንፋ (1:58.40) የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው የደቡብ አፍሪቃዋ ሯጭ ፕሩደንስ ሴክጎዲሶ አሸንፋለች ። የፖርቹጋሏ ፓትሪሺያ ሲልቫ (1:59.80) በሦስተኛ ደረጃ የነሐስ ተሸላሚ ሁናለች ።

በአጠቃላይ የሜዳሊያ ሠንጠረዥ በአንደኛነት ያጠናቀቀችው  ዩናይትድ ስቴትስ  ናት ። 6 የወርቅ 4 የብር እና 6 የነሐስ ሜዳሊያዎች በድምሩ 16 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች ። ተከታዩዋ ኖርዌይ በ 3 የወርቅ እና 1 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 4 ሜዳሊያዎች ነው የሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው ። ከአፍሪቃ የሜዳሊያ ሠንጠረዥ ውስጥ መግባት የቻሉት፦ ደቡብ አፍሪቃ እና ቡርኪና ፋሶ ብቻ ናቸው ። ደቡብ አፍሪቃ በአንድ የወርቅ እና በአንድ የነሐስ በድምሩ ሁለት ሜዳሊያዎች 11ኛ ደረጃ አግኝታ አጠናቃለች ። ቡርኪናፋሶ በአንድ ብቸኛ የነሐስ ሜዳሊያ እንደ ጀርመን ሁሉ የ27ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች ። ሉክዘምበርግ፤ ፖርቹጋል እና ዩክሬንም በአንድ የነሐስ ሜዳሊያ ደረጃቸው እንደ ቡርኪናፋሶ እና ጀርመን 27ኛ ነው ። ኬንያ ከሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውጪ ናት ።

እግር ኳስ

ጀርመን በኔሽንስ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ጣሊያንን በሩብ ፍጻሜው አሰናብታለችምስል፦ Marc Schueler/Sportpics/picture alliance

ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሞሮኮ ውስጥ ከግብጽ ጋር ተጋጥመው 2 ለ0 የተሸነፉት ዋሊያዎቹ ዛሬ ማታ እዛው ሞሮኮ ውስጥ ከጅቡቲ ጋር ይጋጠማሉ ። ግብፅ  በ13 ነጥብ  ለዓለም ዋንጫ ማለፏን ከወዲሁ አረጋግጣለች ። በዐርቡ ግጥሚያ ሁለቱን ግቦች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ ያስቆጠሩት የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሣለህ እና አህመድ ሣይድ ናቸው ። እስካሁን በምጀርመንድቡ እያንዳንዱ ቡድን አምስት ጨዋታዎችን አከናውኗል ። ኢትዮጵያ በ3 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ናት ። ዛሬ የምትገጥማት ጅቡቲ በአንድ ብቸኛ ነጥብ የመጨረሻ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ።  ሴራሊዮን በ8 ነጥብ ሦስተኛ፤ እንዲሁም ጊኒ ቢሳዎ በስድስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ።

በአውሮጳ የኔሽንስ ሊግ እግር ኳስ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ የጀርመን ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜ አለፈ ። ትናንት ማታ በሁለተኛው አጋማሽ በጣሊያኖች ጫና የተፈጠረበት የጀርመን ቡድን ተጨዋቾች በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከል፥ አስጨንቆ በመጫወት እና ኳስ ሲነጠቁ በእልህ ኳሷን አስጥሎ መልሶ በመቆጣጠር ተሳክቶላቸው ነበር ። የመጀመሪያው አጋማሽ በጀርመን ቡድን 3 ለ0 መሪነት መጠናቀቁ በእርግጥም ለጀርመን ተጨዋቾች የሚገባቸው ነበር ማለት ይቻላል ።  ዶርትሙንድ ውስጥ የትናንት በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከልም ሆነ በማጥቃት የጀርመን ቡድን ከረዥም ዘመን በኋላ የተሳካ እንቅስቃሴ ያሳየበት ነበር ።  የመጋቢት 8 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በሁለተኛው አጋማሽ ግን አሰልጣኝ ዩሊያን ናገልስማንም አምነው እንደተቀበሉት ቡድናቸው በመከላከል ላይ ማተኮሩ ለጥቃት ዳርጎታል ። ጣሊያኖች በአንፃሩ ተጠናክረው በማጥቃት ላይ አተኩረው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት ። ያም ወደ ውጤት ተቀይሮ ጨዋታው ሦስት እኩል ተጠናቋል ። በደርሶ መልስ የ5 ለ4 ውጤት የጀርመን ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፍ ችሏል ።

በመጀመሪያው አጋማሽ ጣሊያኖች ላይ ሁለተኛው ግብ የተቆጠረው በተጨዋቾቹ አሳፋሪ ድርጊት ነበር ። የ15 ዐመቱ ኳስ አቀባይ ኖኤል ዑርባኒያክ ለዮሹዋ ኪሚሽ የማእዘን ምቱን ቶሎ እንዲመታ በፍጥነት ኳስ በማቀበል ሁለተኛዋ ግብ እንድትቆጠር አስተዋፅኦ አድርጓል ።  ኳስ አቀባዩ ኳሷን ከማቀበሉ ጥቂት ቀደም ሲል የጀርመን ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲገር ያሻማትን ኳስ አጥቂው ቲም ክላይንዲንስት በጭንቅላት ገጭቶ ግብ ጠባቂው ጂያንሉጂ ዶማ ሩማ በድንቅ ሁኔታ አጨናግፎ ከግቡ ጀርባ ኳሷን ይልካል ። ከዚያም ጂያንሉጂ ዶማሩማ የማእዘን ምት መሰጠቱን ዘንግቶ እንዴት ኳሱን አስመታችሁ በሚል ከተከላካዮች ጋር ለመጨቃጨቅ የግብ ክልሉን ጥሎ ወደፊት ይሄዳል ።  ከኋላው ያሉትን ዮሹዋ ኪሚሽ እና ጃማል ሙሳይላን አላስተዋለም ።

የጀርመን ቡድን ንቃት

በዐይን እይታ ብቻ የተግባባው ኳስ አቀባዩ ቶሎ ኳሷን ለዮሹዋ ኪሚሽ ይወረውርለታል፥ ዮሹዋ ኪሚሽ ለጃማል፥ ግብ ጠባቂውም ተከላካዮችም ከጭቅጭቃቸው ሳይወጡ እና ሳይነቁ ጃማልም ኳሷን ከመረብ ያሳርፋል ። እን ዶማሩማ ዞር ሲሉ ግቡ ተቆጥሯል ። የጃማል ሙሳይላ፤ ዮሹዋ ኪሚሽ እና የኳስ አቀባዩ ኑኤል የጋራ ጥረት የታከለባት ግብ ልትባል ትችላለች ። ለቅፅበት ተዘናግተው ጭቅጭቅ ላይ ማተኮራቸው ጣሊያኖችን ጉድ አድርጓቸዋል ። የጀርመን ተጨዋቾች በተለይ ከረፍት በፊት በተገኘው አጋጣሚ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣታቸውን ያስመሰከሩበት ግጥሚያ ነበር ። ዮሹዋ ኪሚሽ ከጣልያን ጋር በነበረው የደርሶ መልስ ግጥሚያ በተቆጠሩት እምስት ግቦች በአጠቃላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል ። አንዷን በመልሱ ግጥሚያ ትናንት በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል ።

የጀርመን የኋላ መስመር ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲገር አጥቂው ቲም ክላይንዲንስትን ዘሎ ሲያቅፈው ። አንቶኒዮ ሩዲገር ድንቅ ብቃቱን ዐሳይቷል ምስል፦ Christof Koepsel/Getty Images

ከእረፍት መልስ፦ የጣሊያን ቡድን ወደ ማጥቃቱ አጨዋወቱን ቀይሮ ማስጨነቁም ተሳክቶለት ነበር ። የሌሮይ ሳኔ ስህተት ሰበቡም ይኸው አስጨንቆ የመጫወት ስልት ውጤት ነው ። ሌሮይ ሳኔ በቀኝ ክንፈ ጫና ሲበዛበት ኳሷን ባልተመጠነ ሁኔታ ወደ መሀል ለዮሹዋ ኪሚሽ ይልካል፥ ሆኖም ኳሷ የጣሊያን አጥቂ ሞይሴ ኪን እግር ላይ ታርፋለች ። ። በዚያም ሞይሴ ለጣሊያን አስቆጥሮ ቡድኑ ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጓል ።  ሁለተኛውንም ይኸው ፀጉረ ጉዱሩው ሞይሴ ኪን አስቆጥሯል ።

ጀርመን ላይ ሁለተኛው ግብ ሲቆጠርም የመጨረሻው ተከላካይ ታህ ወደፊት ከመውጣት ይልቅ ወደኋላ እያፈገፈገ ለመከላከል መሞከሩ ግቡ እንዲቆጠር አድርጓል ። የማታ ማታ የጣሊያን ቡድን ሦስት እኩል ቢወጣም በደርሶ መልስ ግን ጀርመን ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፏል ። በሩብ ፍፃሜው የዶርትሙንዱ ኤዱና ፓርክ ስታዲየም በደጋፊዎች ደምቃ አምሽታለች ። ሽቱትጋርት እና ሙይንሽን የግማሽ ፍፃሜ ጨወታዎችን ያስተናግዳሉ ።

የጣሊያን ልፋት እና ሽንፈት

የጣሊያን አቻውን በሩብ ፍጻሜው ያሸነፈው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሙይንሽን እና ሽቱትጋርት ከተሞች ውስጥ በሚካሄዱ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ተሳታፊ ይሆናል ።  ሁለቱ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ለረቡዕ፤ ግንቦት 27 እና በነጋታው ቀጠሮ ተይዞላቸዋል ። የፍጻሜ ግጥሚያው እሁድ ሰኔ 1 ቀን፤ 2017 ዓ.ም ቱሪን ጣሊያን ውስጥ ይካሄዳል ። 

ትናንት በነበሩ የኤሽንስ ሊግ ግጥሚያዎች ፖርቹጋል ከዴንማርክ ጋር ተጫውታለች ። የ40 ዐመቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ለግብ ጠባቂው አስታቅፎታል ።  ሆኖም 38ኛው ደቂቃ ለይ ብሩኖ ፈርናንዴሽ በግራ በኩል ያሻማትን ኳስ ክርስቲያኖ በጭንቅላት ሊገጭ ሲዘል የዴንማርኩ ተከላካይ ዮአኺም አንደርሰን ኳሷን አጨናግፋለሁ ብሎ በገዛ መረቡ ላይ በጭንቅላት ገጭቶ አሳርፏል ። 72ኛው ደቃ ላይ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ፖርቹጋል 2 ለ1 እንድትመራ ያደረገውን ግብ ከማእዘኑ በቀኝ በኩል ሰውነቱ አጠማዝዞ በድንቅ ሁኔታ አስቆጥሯል ። 76ኛ ደቂቃ ላይ ክርስቲያን ኤሪክሰን ዴንማርክን ሁለት እኩል ያደረገችውን ግብ አስቆጠረ ።

መደበኛ 90 ደቂቃው 3 ለ2 ቢጠናቀቅም በደርሶ ምልስ ውጤት ሦስት እኩል በመሆኑ ጨዋታው እንዲራዘም ደቂቃ ተጨምሯል ። በተራዘመው ጨዋታ ፖርቹጋል ዴንማርክን 5 ለ2 ድል አድርጋ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፋለች ። በግማሽ ፍፃሜው ከጀርመን ጋር ትጋጠማለች ።

በአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ የጀርመን እና ጣሊያን ግጥሚያ፦ ጀርመን አሸንፋ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፋለች። ጂያንሉጂ ዱማሩማ የዮሹዋ ኪሚሽን ፍጹም ቅጣት ምት ማጨናገፍ አልቻለም ምስል፦ Alex Grimm/Getty Images

ስፔን ከኔዘርላንድ በደርሶ መልስ ግጥሚያው 3:3 ተጠናቆ በመለያ ምት ስፔን ኔዘርላንድን 5 ለ4 በአጠቃላይ 8 ለ7 ድል አድርጓል ። የ16 ዐመቱ ላሚን ጃማል ለስፔን ሦስተኛዋን ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል ። ፈረንሣይ ክሮሺያን በመልሱ ጨዋታ በኦሊሴ እና ዖስማን ዴምቤሌ ግቦች 2 ለ0 ብታሸንፍም በደርሶ መልስ 2 ለ2 በመጠናቀቁ ጨዋታው እንዲራዘም ተደርጓል ። በተራዘመው ጨዋታ አሸናፊውን መለየት ባለመቻሉም በመለያ ምት ፈረንሣይ ክሮሺያን 5 ለ4 አሸንፋለች ። የመጋቢት 01 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የፎርሙላ አንድ

በሻንጋይ የቻይና ግራንድ ፕሪ የፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም፦ የማክለረን አሽከርካሪዎች አንደኛ እና ሁለተኛ ወጡ ።  በትናንቱ ሽቅድምድም ዖስካር ፒያስትሪ አንደኛ በመውጣት 25 ነጥብ ሲያገኝ፤ የቡድን አጋሩ ላንዶ ኖሪስ ሁለተኛ በመውጣት 18 ነጥብ አግኝቷል ።  የመርሴዲሱ ጆርጅ ሩሴል በትናንቱም ውድድር እንዳለፈው ሽቅድምድም ሦስተኛ ደረጃ አግኝቶ 15 ነጥብ አግኝቷል ። በ4ኛነት ያጠናቀቀው የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን 12 ነጥብ አግኝቷል ። ሌዊስ ሐሚልተን በፌራሪ ተሽከርካሪው ሳያጠናቅቅ በመቅረቱ የ19ኛ ደረጃ ይዟል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ

   

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW