1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 19 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ መጋቢት 19 2014

በዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ ተሰላፊ ለመሆን ፉክክሩ ቀጥሏል። ጣሊያንን በአለቀ ሰአት ጉድ የሠራችው ሰሜን መቄዶንያ ነገ ማታ ለፍጻሜው ትጋጠማለች። አፍሪቃን የሚወክሉ ቡድኖች 2ኛ ዙር ግጥሚያቸውን ነገ ማታ ያከናውናሉ። ቤልጂየም በተደረገው የብስክሌት ግልቢያ የኤርትራው ጋላቢ ብንያም ግርማይ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ አሸናፊ በመሆን ታሪክ ሠራ።

 FIFA World Cup Fußball Weltmeisterschaft 2022 Logo Symbolbild
ምስል Darko Bandic/AP Photo/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ተሰላፊ ለመሆን ፉክክሩ ቀጥሏል። ጣሊያንን በአለቀ ሰአት ጉድ የሠራችው ሰሜን መቄዶንያ ነገ ማታ ለፍጻሜው ትጋጠማለች። ለዓለም ዋንጫ ያለፉት ዐሥሩ የአውሮጳ ቡድኖች ከወዲሁ ታውቀዋል። ሰሜን መቄዶንያ፣ ፖላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ስኮትላንድ፣ ስዊድን ፣ ዩክሬን እና ዌልስ በሚያደርጉት ፍልሚያ በፍጻሜ አላፊ ሦስት ቡድኖች ዐስሩን ይቀላቀላሉ። አፍሪቃን የሚወክሉ ቡድኖች ሁለተኛ ዙር ግጥሚያቸውን ነገ ማታ ያከናውናሉ። በሰሜን፤ መካከለኛው አሜሪካ እና ካሪቢክ የእግር ኳስ ማኅበር ኮንፌዴሬሽን የማጣሪያ ግጥሚያ ዩናይትድ ስቴትስ ድል ቀንቷታል። ኤርትራዊው የብስክሌት ጋላቢ በብስክሌት ውድድር ብቸኛው አፍሪቃዊ አሸናፊ በመሆን ቤልጂየም ውስጥ ታሪክ ሠርቷል።

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ

በዓለም ዋንጫ እግር ኳስ አውሮጳን የሚወክሉ ቡድኖች የሚታወቁበት ግጥሚያ በነገው ዕለት ይቀጥላል። ባለቀ ሰአት ጠንካራውን የጣሊያን ቡድን ባልተጠበቀ መልኩ 1 ለ0 ድል ያደረገችው ሰሜን መቄዶንያ ነገ ማታ ለፍጻሜው ከፖርቹጋል ጋር ትጋጠማለች። እስካሁን ሁለቱ ቡድኖች ሁለት ጊዜ ለወዳጅነት ተጋጥመው ፖርቹጋል 1 ለ0 ሲያሸንፍ ሌላኛውን ግጥሚያ አቻ ተለያይተዋል። ፖርቹጋል በሜዳዋ ኤስታዲዮ ዶ ድራጋዶ ውስጥ ካደረጋቸው 11 ግጥሚያዎች ሽንፈት ያስተናገደችው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው። የነገው ግጥሚያ በዚሁ ስታዲየም ነው የሚከናወነው።

ምስል Michael Probst/AP/picture alliance

ለሰሜን መቄዶኒያ ታሪካዊ ድል ብቸኛዋን ግብ ጣሊያን ላይ ያስቆጠረው አሌክሳንደር ታራያኮቭስኪ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው አምስተኛ ግብ ኾኖ ተመዝግቦለታል። ለሰሜን መቄዶንያ ይህን ያህል ግብ ያስቆጠረ ሌላ ተጨዋች የለም። እናስ በነገው ምሽት ግጥሚያ ማን ለዓለም ዋንጫ ያልፍ ይሆን? ላለፉት 20 ዓመታት ከዓለም ዋንጫ መድረክ ጠፍታ የማታውቀው ቤተኛዋ ፖርቹጋል ወይንስ አዲስ ገቢዋ ሰሜን መቄዶንያ? የሁለቱ ግጥሚያ ከወዲሁ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል።  ጣሊያን ጉድ የሠራችው ሰሜን መቄዶንያ ነገ ማታ ምን ልትፈጥር እንደምትችል ዐይታወቅም። ነገ ማታ በተመሳሳይ ሰአት ፖላንድ እና ስዊድን የፍጻሜ ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ።  ሩስያ እና ፖላንድ የሚያደርጉት ግጥሚያ የተሰረዘ ሲሆን፤ ዩክሬን ከስኮትላንድ ጋር የምታደርገው የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። ዌልስ ከስኮትላንድ አለያም ከዩክሬን አላፊ ጋር ለፍጻሜ የምትጋጠምበት ቀንም ዐልታወቀም። በቀጥታ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ከዐስሩም ምድብ በነጥብ አንደኛ የወጡ ቡድኖች ናቸው። እነሱም፦ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ክሮሺያ፣ ዴንማርክ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድ፣ ስፔን፣ ስዊዘርላንድ እና ሠርቢያ ናቸው።

አፍሪቃን ወክለው ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረገው ሁለተኛ ዙር ግጥሚያ በነገው ዕለት ይቀጥላል። በቅድሚያ ናይጀሪያ እና ጋና እንዲሁም ሴኔጋል እና ግብጽ በተመሳሳይ ሰአት ግጥሚያቸውን ማታ ያከናውናሉ። ከእነሱ ጨዋታ በመቀጠል ካሜሩን ከአልጄሪያ፤ ሞሮኮ ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እንዲሁም ማሊ እና ቱኒዝያም ይጋጠማሉ። በመጀመሪያው ዙር ግጥሚያ ሞሮኮ እና ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አንድ እኩል ሲወጡ፤ ጋና እና ናይጄሪያ ያለምንም ግብ ነው የተለያዩት። አልጄሪያ ካሜሩን፤ ቱኒዝያ ማሊን እንዲሁም ግብጽ ሴኔጋልን ያሸነፉት በተመሳሳይ እና በጠባቡ 1 ለ0 ነው። የነገ የነገ አሸናፊ አምስት ቡድኖች ለኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ አፍሪቃን ይወክላሉ።

ምስል Ulmer/imago images

በሰሜን፤ መካከለኛው አሜሪካ እና ካሪቢክ የእግር ኳስ ማኅበር ኮንፌዴሬሽን (CONCACAF) የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያ፦ ክሩስቲያን ፑሊሲክ በዓለም አቀፍ ግጥሚያ የመጀመሪያውን ሔትትሪክ ባስቆጠረበት ጨዋታ ዩናይትድ ስቴትስ ፓናማን በሰፊ የግብ ልዩነት 5 ለ1 አሸንፋለች። ትናንት የትኬት ሽያጩ ሙሉ ለሙሉ በተጠናቀቀበትና 25,022 ተመልካቾችን ባስተናገደው ኤክስፕሎሪያ ስታዲዬም የመጀመሪያውን ግብ በ17ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ከመረብ ያሳረፈው የቸልሲው አጥቂ ክሩስቲያን ፑሊሲክ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው የባከነ ሰአት 49ኛ ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግቡንም ያስቆጠረው በፍፁም ቅጣት ምት ነው። ሦስተኛውን ደግሞ በ65ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል። ቀሪዎቹ ግቦች የፖል አሪዮላ እና ጄሰስ ፌሬራ ናቸው። ለፓናማ ብቸኛዋን ግብ አኒባል ጎዲ 86ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።

ምድቡን አሜሪካ በ25 ነጥብ ከካናዳ ቀጥላ በሁለተኛነት ትከተላለች። ሜክሲኮን በግብ ልዩነት ብቻ ትበልጣለች። ቅዳሜ እለት ጄሜይካን 4 ለ0 የሸኘችው ካናዳ ምድቡን በ28 ነጥብ ትመራለች። ሆንዱራስ ከሜክሲኮ ጋር ገጥማ በጠበበ የግብ ልዩነት 1:0 ተሸንፋለች። ኤልሳልቫዶር ኮስታሪካን አስተናግዳ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሟታል።

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ከጣሊያን ቡድን ጋር ለሚኖረው የኔሽን ሊግ ግጥሚያ መለኪያ ነገ ማታ ከኔዘርላንድ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያከናውናል። ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተጋጠሙት የዛሬ ሁለት ዓመት ነበር፤ ለአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ። ሐምቡርግ ከተማ ውስጥ በተደረገው የያኔው የወዳጅነት ጨዋታ የጀርመን ቡድን በሠርጌ ግናብሬ ቀዳሚ ግብ ቢመራው የማታ ማታ ግን በኔዘርላንድ የ4 ለ2 ሽንፈትን አስተናግዷል።  የወዳጅነቱን ጨዋታ ጨምሮ ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች እስካሁን በአጠቃላይ ለ44 ጊዜያት ተጋጥመው ጀርመን ለ16 ጊዜያት አሸንፏል፤ ኔዘርላንድ ደግሞ ለ12 ጊዜያት። 16 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።

ኮስታሪካ በምታዘጋጀው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን ጫፍ ደርሶ የነበረው እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ሴቶች የእግር ኳስ ቡድን የዓለም ዋንጫ ሕልሙ በጋና አቻው ተጨናግፏል። ቀደም ሲል በሜዳው የ3 ለ0 ሽንፈትን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት አክራ ውስጥ በነበረው የመልስ ግጥሚያ 2 ለ1 ተሸንፏል። ትናንት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አቻ ሊሆን የሚችል ሁለተኛ ግብ 40ኛው ደቂቃ ላይ ቢቆጠርም፤ ግቡ ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ተሰርዟል።

ምስል Ahmed Gomaa/Xinhua News Agency/picture alliance

በአጠቃላይ የደርሶ መልስ 5 ለ1 ድምር ውጤትም የጋና ጥቋቁር ልዕልታት አፍሪቃን ወክለው ለኮስታሪካ 2022 የዓለም ዋንጫ ተሰላፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ለዓለም ዋንጫ አፍሪቃን ወክለው የሚቀርቡት ሁለት ሃገራት ናቸው።  ሴኔጋልን በደርሶ መልስ ግጥሚያ 7 ለ2 ድባቅ የመታችው ናይጀሪያም አፍሪቃን ወክላ ለዓለም ዋንጫ የምትሳተፍ ሁለተኛዋ ሀገር መሆኗን ከትናንት በስትያ ቤኒን ከተማ ውስጥ አረጋግጣለች።   

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዋሊያዎቹም ለወዳጅነት ግጥሚያ ወደ ኮሞሮስ አቅንቶ ባደረገው ግጥሚያ ዐርብ ዕለት 2 ለ1 ተሸንፏል። ሁለቱ ቡድኖች የወዳጅነት ግጥሚያውን ያደረጉት ለቀጣዩ የአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያ ዝግጅት አቋማቸውን ለመፈተሽ በሚል ነው። ባለፈው የአፍሪቃ ዋንጫ ኮሞሮስ 16 ቡድን ውስጥ ብትገባም በአዘጋጇ ካሜሩን የተሰናበተችው 2 ለ1 ተሸንፋ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ በምድቡ አንድም ጨዋታ ሳያሸንፍ ነበር የተሰናበተው።

አትሌቲክስ

51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሰኞ፤ መጋቢት 19 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ከማለዳው 2:30 በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስቴድዮም ተጀመሯል። በውድድሩ፦ የአሎሎ ውርወራ፣ ስሉስ ዝላይ፣ የ100 እና 400 ሜትር ርቀት የሩጫ ፉክክሮች፤ የ800 ሜትር መካከለኛ ርቀት እና የ10,000 ሜትር ረዥም ርቀት የሩጫ ፉክክሮችም ይከናወናሉ።

ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፀሀይ ገመቹ ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ውስጥ ትናንት በተደረገ የግማሽ ማራቶን ውድድር 1:05:52 ሮጣ በማጠናቀቅ 2ኛ ሆናለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት በቀለች ጉደታ ደግሞ ርቀቱን 1:06:35 በሆነ ጊዜ በመሮጥ የ3ኛ ደረጃን አግኝታለች።

የብስክሌት ግልቢያ

ቤልጂየም ኸንት-ቬቩልኼም ውስጥ ትናንት በተደረገው የብስክሌት ግልቢያ የኤርትራው ጋላቢ ብንያም ግርማይ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ አሸናፊ በመሆን ታሪክ ሠራ። የ21 ዓመቱ ብስክሌት ጋላቢ 248,8 ኪሎ ሜርትር የሚሸፍነውን ውድድር ከሦስተኛነት ተስፈንጥሮ በመውጣት ማሸነፉን « የማይታመን» ብሎታል። በውድድሩ መገባደጃ ዝነኛው ፈረንሳዊ ጋላቢ ክሪስቶፍ ላፖርቴን ጨምሮ የቤልጂጉ ጋላቢ ድሪስ ፋን ጌስቴልን ቀድሞ ነው ብንያም ለድል የበቃው።  ብንያም ባለፈው የውድድር ዘመንም ከ23 ዓመት በታች የዓለም ፉክክር ላይ እንደ አንድ አፍሪቃዊ ተወዳዳሪ የሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ታሪክ ሠርቶ ነበር። በዚህ የውድድር ዘመን ስፔን ማዮካ ውስጥም አንደኛ በመውጣት ብርቱ ብስክሌት ጋላቢነቱን ያስመሰከረ የስፖርት ሰው ነው።

የመኪና ሽቅድምድም

ምስል Hassan Ammar/AP Photo/picture alliance

በፎርሙላ አንድ የሳውዲ ዓረቢያ ጅዳ የመኪና ሽቅድምድም የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን ዳግም ድል ርቆታል።  የፎርሙላ አንድ አጠቃላይ ውድድር የ7 ጊዜያት ዋንጫ ባለቤቱ ሌዊስ ሐሚልተን በዘንድሮው የሁለተኛ ዙር ውድድርም ሽንፈት ገጥሞታል። የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን የፌራሪውን አሽከርካሪ ሻርል ሌክሌርን አስከትሎ አንደኛ በወጣበት ፉክክር ዝነኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪው የ10ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በባለፉት ሁለት ግጥሚያዎች መሠረት፦ ሻርል ሌክሌር በ45 ነጥብ ይመራል። የፌራሪ ቡድን አጋሩ ካርሎስ ሳይንስ በ33 ነጥብ ይከተለዋል። የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን በትናንት ድሉ ያገኘው 25 ነጥብን ይዞ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የመርሴዲሱ ሌዊስ ሐሚልተን ትናንት 10ኛ በመውጣቱ ከተሰጠው አንዲት ነጥብ ጋር እስካሁን 16 ነጥብ በማግኘት የ5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም የነጥብ አሰጣጥ ደንብ መሠረት፦ 1ኛ ለወጣ አሽከርካሪ 25 ነጥብ ይሰጣል። በእያንዳንዱ ውድድር ሁለተኛ ለሚወጣ 19 ነጥብ፤ ለሦስተኛ 15፤ ለአራተኛ 12 ነጥብ፤ አምስተኛ ሆኖ ላጠናቀቀ ደግሞ 10 ነጥብ ይሰጣል። ነጥቡ 8፣ 6፣ 4፣ 2፣ 1 እያለ እስከ ዐሥረኛ ደረጃ ድረስ ይወርዳል። ከዐሥራ አንደኛ ጀምሮ ወደታች ያሉት ምንም ነጥብ አይሰጣቸው። በየሃገራቱ የሚደረጉ ውድድሮች ውጤት በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ላይ ተደምረው ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበ የውድድር ዘመኑ አሸናፊ ይሰኛል። በዚህ መልኩ የመርሴዲስ አሽከርካሪው፤ ብሪታንያዊው ሌዊስ ሐሚልተን ለሰባት ጊዜያት ባለድል ሆኗል።

ምስል Juergen Hasenkopf/imageBROKER/picture alliance

የሜዳ ቴኒስ

የኦሎምፒክ ባለድሉ አሌክሰአንደር ዜቬሬቭ ሚያሚ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የቴኒስ ባለሞያዎች ማኅበር (ATP) ግጥሚያ ያለብዙ ልፋት ማለፍ ችሏል። በትናንቱ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ በተደረገ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ፦ የሐምቡርግ ከተማ ተወላጁ አሌክሰአንደር ዜቬሬቭ አሜሪካዊው ማኬንዚ ሜክዶናልድን ያሸነፈው በተደጋጋሚ 6:2 እና 6:2 ነው።  ቀጣይ ተፎካካሪውም ዴኒስ ኩድላን 7:5 እና 7:4 በድምር ውጤት 2 ለ1 ያሸነፈው አውስትራሊያዊው ታናሲ ኮኪናኪስ ነው።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW