የመጋቢት 26 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ መጋቢት 26 2014ለነገው የሩብ ፍጻሜ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ሊቨርፑል ወደ ፖርቹጋል ሙሉ ቡድኑን ይዞ እንደሚያቀና የተጎዱ ተጨዋቾች ማገገማቸውንም ጀርመናዊው አሰልጣኝ ይፋ አድርገዋል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ድል የቀናቸው መሪው ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ ተናንቀዋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ተጋጣሚውን በሰፋ የግብ ልዩነት ድል አድርጎ ደረጃውን እንዳስጠበቀ ነው። በአንጻሩ ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በገዛ ሜዳው ሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም በሰፊ የግብ ልዩነት አስደንጋጭ ሽንፈት አስተናግዷል። ለአውሮጳ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ሐሙስ ማታ አታላንታን የሚገጥመው ላይፕትሲሽ ነው በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድን ጉድ የሠራው። ሐሙስ ማታ የአውሮጳ ሊግ አራት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
አትሌቲክስ
ጣሊያን ሚላኖ ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነ የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። ኬኒያዊቷ አትሌት ቪቪያን ጄሮኖ ኪፕላጋት አንደኛ በወጣችበት ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ስንታዬሁ ጥላሁን የ2ኛ ደረጃን አግኝታለች። ከኬኒያዊቷ በ1 ደቂቃ ከ1 ሰከንድ በመቀደም የገባችው 2 ሰአት ከ22 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ በመሮጥ ነው። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አታለል አንሙት ከስንታየሁ ሁለት ሰከንድ ብቻ በመቀደም እግር በእግር ተከትላ 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ያለውን ተርታ በመያዝ የሚላኖን ማራቶን ተቆጣጥረውት ነበር። መሰለች ፀጋዬ፣ ራህማ ቱሳ፣ እና ዝናሽ መኮንን እስከ ስድስተኛ ደረጃ ተከታትሎ በመግባት አመርቂ ድል አስመዝግበዋል።
በፈረንሳይ የፓሪሱ ኢንተርናሽናል ማራቶን የሩጫ ፉክክር በወንዶችም በሴቶችም ኢትዮጵያውያኑ ለድል በቅተዋል። በወንዶች ደሱ ገልሚሳ 2:05:07 በመሮጥ የ1ኛ ደረጃን አግኝቶ አሸንፏል። ደሱ በቀዝቃዛው የፓሪስ አየር ውድድሩን ያሸነፈው በመጨረሻው ዙር ፍጥነት በመጨመር ሲሆን፤ ወድድሩን ለማጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜም የራሱን የግል ሰዓት በ14 ሰከንድ ያሻሻለበት ነው። ሠይፉ ቱራ ከደሱ ሦስት ሰከንድ ብቻ ዘግይቶ የሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ዓባይነህ ደጉ፣ ኦሊካ አዱኛ፣ ልመንህ ጌታቸው እና አዐይቼው ባንቲ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 8ኛ እና 9ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
በሴቶች የፓሪስ ማራቶን ፋንቱ ጅማ 2:22:52 በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። ከ24 ሰከንድ በኋላ ተከትላ የገባችው በሱ ሳዶ የሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በዚህ ውድድር ኬኒያዊቷ ጁዲዝ ኮሪስ ጄፕቱም 2:19:48 በመሮጥ በፈረንሳይ ምድር ከ2 ሰአት ከ20 በታች በማስመዝገብ ክብረወሰን ሰብራለች።
በ31ኛው የባርሴሎና ግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክርም ኢትዮጵያውያኑ በወንዶችም በሴቶችም ድል ቀንቷቸዋል። በወንዶች ፉክክር ኃፍቱ ተክሉ 59 ደቂቃ ከ04 ሰከንድ በመሮጥ 1ኛ፣ ሲወጣ የቦታውን ርቀት ክብረወሰን በመስበር ነው። 40 ሰከንድ ያሻሻለው ክብረወሰን ከ5 ዓመት በፊት በሙሌ ዋሲሁን የተያዘ ነበር። ጫላ ረጋሳ 4 ሰከንድ ተከትሎት የ2ኛ ደረጃን በማግኘት ለድል በቅቷል። ኬኒያዊው ኤልቪስ ቹቦይን ተከትለው ኢትዮጵያውያኑ አንተንዐየሁ ዳኛቸው እና ክንዴ ደርሴህ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃን ይዘዋል። በዚሁ የሴቶች ፉክክር ደግሞ ጌጤ ዓለማየሁ (1:06:37)እና አስናቀች እርዋጭቴ (1:09:34)2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘው ለድል በቅተዋል። ኬኒያዊቷ ማርጋሬት ኪፕኬምቦይ የ1ኛ ደረጃን በማግኘት አሸንፋለች። በዚህ ውድድር አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በውድድሩ እንደማትሳተፍ በመጨረሻዎቹ ጊዜያት ማሳወቋን አዘጋጆቹ ተናግረዋል።
በኮቪድ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ሩጫ ውድድር ዳግም ሊጀምር ነው። ውድድሩ ለ14ተኛ ጊዜ እሁድ፤ ሚያዚያ 30 ቀን፣ 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ይከናወናል። በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያንና በሃገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የውጪ ማኅበሰብ ልጆች በውድድሩ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጧል። ውድድሩ በአራት የተለያዩ የእድሜ ክልሎች ማለትም (ከ5፣ ከ8፣ ከ11 እና ከ14 በታች) በወንድና በሴት ተከፋፍሎ እንደሚካሄድም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዛሬ በኢሜል በላከልን መግለጫ ጠቅሷል። እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ግንቦት 9 ቀን ተከብሮ የሚውለውን የአውሮጳ ኅብረት የተቋቋመበትን የሮም ስምምነትን በዓል ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ የሩጫ ውድድር ይከናወናል። ውድድሩ ላለፉት 2 ዓመታት በኮቪድ ምክንያት ተቋርጦ ነበር፡፡ 2000 ተሳታፊዎች ይኖሩታል ተብሎ የሚገመተው ይህ የሩጫ ፉክክር ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት ማዕከል የተለያዩ የህፃናት መዝናኛዎችን እንደሚያካትት ተጠቅሷል።
የሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ
የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ዛሬ ከሰአት በሰጡት መግለጫ፦ በፕሬሚየር ሊግ የቅዳሜ ግጥሚያ በጉዳት ያልተሰለፈው አማካዩ ናቢ ኪዬታ ከጉዳቱ አገግሞ መመለሱን ተናግረዋል። ይህም ክፍተት ለታየበት የሊቨርፑል አማካይ ክፍል ታላቅ እፎይታ ነው። ከዋትፎርድ ጋር በነበረው ግጥሚያ ያልተሰለፉት አሌክሳንደር አርኖልድ እንዲሁም መጠነኛ ጉዳት የነበረባቸው ጆዌል ማቲፕ እና ኩርቲስ ጆንስም ዝግጁ መሆናቸውን ጀመርናዊው አሰልጣኝ ተናግረዋል። «ሙሉ ቡድኑ ዝግጁ ነው»ም ብለዋል። ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ ቅዳሜ ዕለት ዋትፎርድን 2 ለ0 ድል አድርጎ በ72 ነጥቡ የሁለተኛ ደረጃውን አስጠብቋል።
በሌላ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ፦ ማንቸስተር ሲቲ አትሌቲኮ ማድሪድን በተመሳሳይ ሰአት ነገ ማታይገጥማል። ሲቲ በፕሬሚየር ሊጉ ተጋጣሚው በርንሌይን እንደ ሊቨርፑል 2 ለ0 አሸንፎ በፕሬሚየር ሊጉ የአንደኛ ደረጃውን አስጠብቋል። ከሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ብቻ በልጦ 73 ነጥብ ይዟል። ለሻምፒዮንስ ሊግ ከነገ በስትያ ሪያል ማድሪድ እና ቸልሲ እንዲሁም ባየርን ሙይንሽን ከቪላሪያል ጋር ይጋጠማሉ።
ባየር ሙይንሽን በጀርመን ቡንደስሊጋ ተጋጣሚው ፍራይቡርግን በሰፋ የግብ ልዩነት 4 ለ1 ድል አድርጎ በ66 ነጥቡ የመሪነት ደረጃውን እንዳስጠበቀ ነው። በአንጻሩ ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በገዛ ሜዳው ሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም በሰፊ የግብ ልዩነት አስደንጋጭ ሽንፈት አስተናግዷል። በ57 ነጥቡም ተወስኗል። ለአውሮጳ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ሐሙስ ማታ አታላንታን የሚገጥመው ላይፕትሲሽ ነው በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድን 4 ለ1 ጉድ የሠራው። ላይፕትሲሽ በፕሬሚየር ሊጉ 48 ነጥብ ይዞ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 51 ነጥብ ያለው ባየር ሌቨርኩሰን የ3ኛ ደረጃን ተቆናጧል።
የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያ
ለአውሮጳ ሊግ ሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያ ሐሙስ ማታ 4 ጨዋታዎች ይከናወናሉ። የመጀመሪያው ጨዋታ የጀርመኑ ላይፕትሲሽ ከጣሊያኑ አታላንታ ቤርጋሞ ጋር የሚያደርገው ነው። ከዚያም የእንግሊዙ ዌስትሀም እና የፈረንሳዩ ኦሎምፒክ ሊዮን ጨዋታ ይከተላል። በተመሳሳይ ሰአት የስፔኑ ባርሴሎና ከጀርመኑ አይንትራኅት ፍራንክፉርት እንዲሁም የፖርቹጋሉ ብራጋ ከስኮትላንዱ ግላስኮው ሬንጀርስ ጋር ይጋጠማሉ።
አሰልጣኝ ሉዊ ፋን ጋል
የማንቸስተር ዩናይትድ የቀድሞው አሰልጣኝ ሉዊ ፋን ጋል ከአባላዘር እጢ ካንሰር ለመዳን እየታከሙ መሆናቸውን በኔዘርላንድስ ሁምቤርቶ ቲቪ ትናንት ይፋ አድረገዋል። የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቡድናቸው በቅርቡ በነበረው ግጥሚያዎች ተጽዕኖ እንዳይፈጠር በሚል ለተጨዋቾቻቸው ስለሕክምናቸው ሳይነግሩ ቆይተዋል። ስለ ሕክምናቸው ትናንት በይፋ ከተናገሩ በኋላ በርካታ የመልካም ምኞት መግለጫዎችን ከተለያዩ የስፖርት ቡድኖች እና ታዋቂ ግለሰቦች እያገኙ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ በቡድኑ ይፋዊ ትዊተር ገጹ፦ «ማንቸስተር ዩናይትድ የሚገን በአጠቃላይ ከካንሰር ጋር ለሚያደርጉት ትግል ከቀድሞ አሰልጣናችን ሉዊ ፋን ጋል ጎን ነን» የመልካም ምኞት መግለጫውን ጽፏል። የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA)በበኩሉ «ሁላችንም አብረንህ ነን» ሲል በይፋዊ የትዊተር ገጹ ለአሰልጣኙ ድጋፉን ገልጧል።
የ70 ዓመቱ አሰልጣኝ የሚታከሙት ካንሰር እጅግ ብርቱ እንደሆነ ቢናገሩም፤ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው እንደሚቀጥሉ ዐስታውቀዋል። ሉዊ ፋን ጋል የኔዘርላንድስ ቡድንን በማሰልጠን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 የዓለም ዋንጫ የሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። አሁን ደግሞ ቡድናቸውን ለኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ ተሳታፊነት ማብቃት ችለዋል። ኔዘርላንድስ ዐርብ ዕለት በወጣው እጣ መሠረት፦ ከአዘጋጇ ኳታር፣ ሴኔጋል እና ኤኳዶር ጋር በምድብ «ሀ» ተመድባለች። ከእጣ አወጣጡ በፊት ሉዊ ፋን ጋል፦ ውድድሩ ኳታር ውስጥ መከናወኑ እጅግ አስቂኝ ነው ብለው ተችተዋል። በእጣ አወጣጡ ስነስርዓትም አልተገኙም። የቀሩት ግን ተመርምረው የኮሮና ተሐዋሲ ስለተገኘባቸው እንደሆነ ተገልጧል።
ከኔዘርላንድስ ጋር ለዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከ13 የአውሮጳ ቡድኖች 12ቱ አልፈዋል። የዌልስ፣ ስኮትላንድ አለያም ዩክሬን አሸናፊ 12ቱ ቡድኖችን ይቀላቀላል። 12ቱ ቡድኖች፦ ቤልጂየም፣ ክሮሺያ፣ ዴንማርክ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ፖላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ሠርቢያ፣ ስፔን እና ስዊትዘርላንድ ናቸው።
የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ እጣ ድልድል
ዐርብ ዕለት የተከናወነው የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ የእየ ምድቦቹ አራት አራት ተሳታፊ ሃገራት የእጣ ድልድል መታወቁ ጨዋታዎቹን ከወዲሁ አጓጊ አድርጓቸዋል። በእጣው መሠረት እንግሊዝ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን ጋር ትፋለማለች። የታላቋ ብሪታንያ ደርቢ እንዲሉም እንግሊዝ በአውሮጳ ማጣሪያ የመጨረሻ ዙር ላይ ከሚገኙት ከስኮትላንድ አለያም ዌልስ እና ዩክሬን አላፊ ጋር ትጫወታለች። ከአውሮጳ የዓለም ዋንጫ 13ኛ ተሳታፊ ሃገር ለመሆን በምድቡ ዩክሬን ከስኮትላንድ ጋር ተጋጥመው የሁለቱ አላፊዎች ከዌልስ ጋር ይጫወቱ እና ወደ እነ እንግሊዝ የዓለም ዋንጫ ምድብ «ለ» አራተኛ ተወዳዳሪ ሆነው ይገባሉ።
የእጣ ድልድሉ በምድብ «ሐ» የሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲናን ከሜክሲኮ ጋር አላትሟል። ፖላንድ እና ሳዑዲ ዓረቢያም በእዚሁ ምድብ ይገኛሉ። በምድብ «መ» ፈረንሳይ፣ ዴንማርክ እና ቱኒዝያ ይገኛሉ። አንድ ሀገር ምድባቸውን እንዲቀላቀል ይጠብቃሉ። ኳታር ዶሐ ውስጥ ግንቦት 30 አውስትራሊያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በሚያደርጉት ግጥሚያ አላፊው ከከፔሩ ጋር ተጫውቶ ያሸነፈው ወደ ምድቡ ይቀላቀላል። ምድብ «ሠ»ም ከኮስታ ሪካ እና ኒውዚላንድ አላፊ አንዱን ተሳታፊ ሀገር ይጠብቃል። አላፊ ቡድኑ ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ይታወቃል። ስፔን፣ ጀርመን እና ጃፓን ምድቡ ውስጥ ይገኛሉ። በምድብ «ረ» በፊፋ መስፈርት ከዓለም የ2ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቤልጂየም፦ ክሮሺያ፣ ሞሮኮ እና ካናዳን ትገጥማለች። ፊፋ የዓለማችን ቁጥር አንድ ብሎ የሰየማት ብራዚል በምድብ «ሰ» ስዊትዘርላንድ፣ ሠርቢያ እና ካሜሮን ይጠብቋታል። በመጨረሻው ምድብ «ሸ» አፍሪቃዊቷ ጋና ትገኛለች። ከፖርቹጋል፣ ኡራጓይ እና ደቡብ ኮሪያ ጋር ትጋጠማለች።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ