1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 27 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 27 2013

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ማንቸስተር ሲቲ የሻምፒዮንስ ሊጉን ጨምሮ 4 ዋንጫዎችን ወስዶ ታሪክ ለመድገም እየተንደረደረ ነው። ለአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ነገና ከነገ በስትያ ወሳኝ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ። ሪያል ማድሪድ ከሊቨርፑል እንዲሁም ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የሚያደርጓቸው አጓጊ ጨዋታዎች በበርካቶች ዘንድ ይጠበቃሉ።

 Fußball Bundesliga 27. Spieltag | VfB Stuttgart - Werder Bremen
ምስል Batic/Nordphoto/imago images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ማንቸስተር ሲቲ የሻምፒዮንስ ሊጉን ጨምሮ አራት የተለያዩ ዋንጫዎችን ወስዶ ታሪክ ለመድገም እየተንደረደረ ነው። በሻምፒዮንስ ሊጉ ነገ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድን ይገጥማል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ ለማግኘት በቡንደስሊጋ የነበረውን ወሳኝ ግጥሚያ በሳምንቱ መጨረሻ በሽንፈት ቋጭቷል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናልን በባዶ የሸኘው ሊቨርፑል ነገ በሻምፒዮንስ ሊግ የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ይጠብቀዋል። ከምን ጊዜው በላይ አስተማማኝ አቋም ላይ የሚገኘው ካሪም ቤንዜማ ለሊቨርፑል ፈተና መሆኑ አይቀርም። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የአንደኛ ደረጃን ለማስጠበቅ በነበረው ግብግብ ላይፕትሲሽን በትግል ያሸነፈው ባየርን ሙይንሽን ረቡዕ ዕለት ከፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ይጠብቀዋል።  በዌስት ብሮሚች የ5 ለ2 አስደንጋጭ ሽንፈት ያስተናገደው ቸልሲም ከነገ በስትያ በሻምፒዮንስ ሊጉ የፖርቹጋሉ ፖርቶን ይፋለማል። በግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኬንያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። 

ለአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ነገ እና ከነገ በስትያ ወሳኝ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ። ሪያል ማድሪድ ከሊቨርፑል እንዲሁም ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የሚያደርጓቸው አጓጊ ጨዋታዎች በበርካቶች ዘንድ ይጠበቃሉ።

ፕሬሚየር ሊግ

ምስል Laurence Griffiths/PA/dpa/picture alliance

ማንቸስተር ሲቲ ዘንድሮ እጅግ ጠንካራ የሚባል ቡድን ኾኗል። ምናልባትም ዘንድሮ የፕሬሚየር ሊጉን ጨምሮ አራት የተለያዩ ዋንጫዎችን አሸንፎ የመሰብሰብ ዕድል ሳይኖረው አይቀርም። በፕሬሚየ ሊጉ በሁለተኛነት ከሚከተለው ማንቸስተር ዩናይትድ በ14 ነጥብ ርቀት ላይ ይገኛል። በእርግጥ 60 ነጥብ ያለው ማንቸስተር ዩናይትድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቢቀረውም ማለት ነው። ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት ላይስተር ሲቲን 2 ለ0 በማሸነፍ 31ኛ ጨዋታውን በድል አጠናቋል።  በኤፍ ኤ ካፕ ግማሽ ፍጻሜ ቸልሲ ይጠብቀዋል። ቸልሲን ማሸነፍ ከቻለ በፍጻሜው ከላይሰር ሲቲ እና ሳውዝሐምፕተን አሸናፊ ጋር በወርሃ ግንቦት፤ በ7ኛው ቀን ይፋለማል።

በማስታወቂያ ጉዳይ ካራባዎ የተሰኘው የእንግሊዝ የሊግ ዋንጫን የማንሳትም ዕድል ማንቸስተር ሲቲ ከፊቱ ይጠብቀዋል። ያለፈው የካራባዎ ዋንጫን ማንቸስተር ሲቲ አስቶን ቪላን 2 ለ1 ረትቶ ሲጨብጥ ከ82 ሺህ በላይ ታዳሚያን በስታዲየም ውስጥ ተገኝተው የፍጻሜ ጨዋታውን ተከታትለዋል። ዘንድሮ የእንግሊዝ እግር ኳስ ሊግ (EFL) ከ20 ቀናት በኋላ በሚያዘጋጀው የካራባዎ ፍጻሜ በኮቪድ ምክንያት የሚታደሙት 8,000 ደጋፊዎች ብቻ ናቸው ተብሏል። በፍጻሜ ግጥሚያውም ማንቸስተር ሲቲ ቶትንሀምን ዌምብሌይ ስታዲየም ውስጥ ይገጥማል። ሲቲ አሸንፎ ዋንጫውን ዘንድሮም የሚወስድ ከሆነ አራት የተለያዩ ዋንጫዎችን ለመጨበጥ የሚያደርገው ግስጋሴ አንዱ ምዕራፍ በድል ይዘጋል ማለት ነው። የካራባዎ ዋንጫን በተደጋጋሚ በማንሳት እስካሁን ሊቨርፑል ላይ የሚደርስ አልተገኘም። በፕሬሚየርሊጉ ቅዳሜ ዕለት አርሰናልን 3 ለ0 ያሸነፈው ሊቨርፑል የካራባዎን ዋንጫ ለ8 ጊዜያት አሸንፎ ወስዷል።

በሻምፒዮንስ ሊጉም ቢሆን ዋንጫ የማንሳት ዕድል አለው። ሆኖም እንደ ሌሎቹ የዋንጫ ግጥሚያዎች ዕድሉ ሰፊ የሚባል አይመስልም። ከቦሩስያ ዶርትሙንድ በሩብ ፍጻሜው፤ እንዲሁም የባየር ሙይንሽን እና ፓሪ ሳን ጃርሞ አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ይጠብቁታል። ለፍጻሜው ከደረሰ፦ የሪያል ማድሪድ፣ ሊቨርፑል፣ ፖርቶ እና ቸልሲ አሸናፊዎች ጋርም ነው የሚጫወተው።

ሻምፒዮንስ ሊግ

ማንቸስተር ሲቲ በሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ ጋር የሚያደርጉት የነገው ጨዋታ በበርካቶች ዘንድ እጅግ የሚጠበቅ ነው። በ2018 የክሪስቲያኖ ሮናልዶ እና ጋሬት ቤል ኳስ አመቻች የነበረው ፈረንሳዊው ካሪም ቤንዜማ ነገ የቡድኑ ዋና ሰው ኾኖ ነው የሚሰለፈው። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ጁቬንቱስ፤ ጋሬት ቤል ደግሞ በውሰት ወደ ቶትንሀም ሆትስፐር ማቅናታቸው የ33 ዓመቱ ካሪም ቤንዜማ በሻምፒዮንስ ሊጉ የነገ ግጥሚያ የመሀል ቦታውን እንዲምነሸነሽበት ዕድል ይፈጥርለታል።

ምስል Bernat Armangue/AP Photo/pictue alliance

በሪያል ማድሪድ ታሪክ ከካሪም ቤንዜማ የበለጠ ለቡድኑ ግብ ያስቆጠሩ ተጨዋቾች አራት ብቻ ናቸው። ራውል በ323፣ አልፍሬዶ ዲ ስቴፋኖ በ308፣ እንዲሁም ሳንቲላና በ290 ግቦች ካሪም ቤንዜማን ይበልጡታል። በእርግጥ የክሪስቲያኖ ሮናልዶን 450 ግቦች የሚጠጋ ባይኖርም ካሪም ቤንዜማ ለሪያል ማድሪድ 273 ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።

በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ደግሞ በርካታ ግብ በማስቆጠር ካሪም ቤንዜማን የሚበልጡት ሦስት ተጨዋቾች ናቸው። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፣ ሊዮኔል ሜሲ እና ሮቤርት ሌቫንዶስቭስኪ። በዚህ የጨዋታ ዘመን በሁሉም የጨዋታ ውድድሮች 24 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። 11ዱ ግቦች ባለፉት 10 ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ናቸው።

በሳምንቱ መገባደጃ ላይ በጀርመን ቡንደስሊጋ ከተከናወኑ ሁለቱ ጨዋታዎች ወሳኝኝ የሚባሉ ናቸው። የአንደኛ ደረጃን ለማስጠበቅ እና ለመንጠቅ የተደረገው የባየርን ሙይንሽን እና የላይፕትሲሽ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር የታየበት ነበር። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለቀጣይ የውድድር ዘመን በሻምፒዮንስ ሊጉ ለመቆየት ዕድሉን የሚያሰፋበትን ግጥሚያ በአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጨንግፎበታል። ሁለቱን ጨዋታዎች በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክራለን።

ባየርን ሙይንሽን ላይፕትሲሽን 1 ለ0 ያሸነፈው በትግል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የላይፕትሲሽ ተጨዋቾች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ለማሸነፍ አለያም አቻ ለመውጣት በብርቱ ታግለዋል።  አንድ እኩል የመውጣት ዕድላቸውንም ዳኛው ፍጹም ቅጣት ምት ነፍጎ አሰናክሎባቸዋል።  ባየርን ሙይንሽን በአማካዩ ሌዎን ጎሬትስካ ብቸኛ ግብ ድል አድርጓል፤ በቡንደስሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ ልዩነቱን በ7 ነጥብ አስፍቶታል።

በእርግጥ ባየርን ሙይንሽን ይኼን ጨዋታ ማሸነፉ ልዩ ትርጉም ቢሰጠውም ገና እስከ መጨረሻው 34ኛ ግጥሚያ ድረስ ግን ብርቱ ግጥሚያዎች ይጠብቁታል። ከቀሪ 7 ጨዋታዎቹ መካከል አራቱ እንደዋዛ የሚታዩ አይደሉም። 29ኛው ፉክክር 54 ነጥብ ይዞ በቡንደስሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ 3ኛ ላይ ከሚገኘው ቮልፍስቡርግ ጋር ነው። ባየርን ሙይንሽን ቮልፍስቡርግን የሚበልጠው በ10 ነጥብ ነው። 30ኛው ጨዋታ ከአውሮጳ ሊግ የማጣሪያ ግጥሚያ በቀጥታ ወደ አውሮጳ ሊግ ፉክክር ለመግባት ከሚሟሟተው ባየርን ሌቨርኩሰን ጋር ይሆናል። እንደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ 43 ነጥብ ያለው ባየርን ሌቨርኩሰን በደረጃ ሰንጠረዡ 6ኛ ላይ ይገኛል።

ምስል Gibun3/REUTERS

ባየርን ሙይንሽን ሌላው 31ኛው ግጥሚያው ከማይንትስ ጋር ነው። 25 ነጥብ ይዞ በ15ኛ ደረጃ ወራጅ ቀጣና ጠርዝ ላይ የሚገኘው ማይንትስ ለባየርን ሙይንሽን ቀላል ይሆናል ማለት ይከብዳል። ወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኙት ኮሎኝ እና አርሜኒያ ቢሌፌልድ ከማይንትስ በ2 ነጥብ ብቻ ነው የሚበለጡት። ባየርን ሙይንሽን የሚያከናውነው 32ኛ ግጥሚያው ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር ነው። ግላድባኅ 39 ነጥብ ይዞ 9ኛ ደረጃ ላይ ቢገኝም አምስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ የሚበለጠው በ4 ነጥብ ብቻ ነው። ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ ማለትም የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለመያዝ በሚደረገው ፉክክር ዕድሉ ስላለው ለባየርን ሙይንሽን ብርቱ ተፎካካካሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ላይፕትሲም ከቀሪ 7 ጨዋታዎቹ አራቱ እንደ ባየርን ሙይንሽን ከባድ የሚባሉ ናቸው። በሚቀጥለው ሳምንት የሚገጥመው 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቬርደር ብሬመን ጋር ነው። ከዚያም 29ኛ ግጥሚያውን ከሆፈንሃይም ጋር ያከናውናል። ሆፈንሀይም እንደ ቬርደር ብሬመን 30 ነጥብ ይዞ ደረጃው 12ኛ ነው። የላይፕትሲሽ 30ኛ ግጥሚያ በ23 ነጥብ ወራጅ ቀጣና ጠርዝ ላይ ከሚገኘው ኮሎኝ ጋር ይሆናል። ለላይፕትሲሽ ከሽቱትጋርት ጋር የሚያደርገው 31ኛው ግጥሚያ፤ 32ኛው ከዶርትሙንድ፣ 33ኛው ከቮልፍስቡርግ፣ እንዲሁም 34ኛው ከዑኒዮን ቤርሊን ጋር የሚያከናውናቸው ጨዋታዎች ቡድኑን የሚፈትኑት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃሉ።

በባየር ሙይንሽን እና ላይፕትሲሽ ግጥሚያ፦ አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ሽቱትጋርትን 4 ለ0 ባሸነፉበት ግጥሚያ ካሰለፏቸው ተጨዋቾች ጄሮም ቦአቴንግን በቢጫ ካርድ ማሰለፍ አልቻሉም። በዕለቱ ግጥሚያ በቀይ ካርድ የወጣው አልፎንሶ ዳቪስም አልተሰለፈም። ሁለት የቡንደስሊጋ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ አይችልም።  ከአጥቂ መስመር፦ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በጉልበት ጉዳት አልተሰለፈም። ለብሔራዊ ቡድኑ ተሰልፎ የነበረው ሠርጌ ግናብሬ 72ኛው ደቂቃ ላይ ኪንግስሌይ ኮማንን እስኪተካ ድረስ ተቀያሪ ወንበር ላይ መቀመጥ ነበረበት። በአንጻሩ ሉቃስ ሔርናንዴዝ፣ ዮሹዋ ኪሚሽ፣ ኪንግስሌይ ኮማን እና ኤሪክ ማክሲም ቾፖ ሞቲንግ ከዐሥራ አንዱ ተሰላፊዎች ውስጥ ነበሩ። በእለቱ ተሰላፊ የነበረው ኦስትሪያዊው ተከላካይ ዳቪድ አላባ ለባየርን ሙይንሽን ለ274 ጊዜ በመሰለፍ ከውጭ ተጨዋቾች ለቡድኑ በርካታ ጊዜ በመሰለፍ ቀዳሚ መሆን ችሏል። ከእዚህ በፊት የውጭ ሀገር ተጨዋች ሆኖ ለባየርን ሙይንሽን በተደጋጋሚ በመሰለፍ ቀዳሚው ፍራንክ ሪቤሪ ነበር።

ምስል Annegret Hilse/REUTERS

ላይፕትሲሾች ገና ከመነሻው በተደጋጋሚ በማጥቃት አላባ እና የባየርን ሙይንሽን ተከላካዮች ላይ ሥራ አብዝተውባቸው ነበር። ላይፕትሲሽ በተለይ በክንፍ በኩል በርካታ የማጥቃት ሙከራዎችን አድርጎ ነበር። 19ኛው ደቂቃ ላይ ማርሴል ሳቢትሰር ከርቀት ያደረገው ብርቱ ሙከራ ይጠቀሳል። ባየርን ሙይንሽን በመከላከል ላይ ቢያዘነብልም፦ ኪሚሽ ድንቅ በሚባል አጨዋወት ወደ ላይፕትሲሽ ግብ ክልል አስርጎ ለቶማስ ሙይለር የላካት ኳስ ለውጤት በቅታለች። ከላይፕትሲሽ ተከላካዮች ትኩረት ውጪ ነጻ ለነበረው ሌዎን ጎሬትስካ ኳሷን አመቻችቶ በመላክ ጎሬትስካ 38ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም ኹኔታ ከመረብ አሳርፏታል። 

ቶማስ ሙይለር ቡድኑን ወሳኙን ድል እንዲቀዳጅ ካስቻለ በኋላ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኗል። ኪከር የተባለው የድረ ገጽ መጽሄት ለ200,000 ሰዎች ባደረገው ቃለ መጠይቅ 89 ከመቶ ያህሉ የቃለ መጠይቁ ተሳታፊዎች ሙይለር ወደ ብሔራዊ ቡድኑ እንዲመለስ መሻታቸውን ገልጠዋል። በ2020/21 ቶማስ ሙይለር ዐሥር ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ዐሥራ አምስቱን ለግብ አመቻችቷል።

ላይፕትሲሾችም ተደጋጋሚ የመከኑ ሙከራዎችን አድረገዋል። ክሪስቶፈር ንኩንኩ በ49ኛው ደቂቃ፣ ዳኒ ዖልሞ በ52 እና 53፤ ማርሴል ሳቢትሰር በ49፣ 56 እና 59 ደቂቃዎች ላይ ያደረጓቸው ሙከራዎች አንድም ግባቸውን የሳቱ አለያም ለግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር እዚህ ግቡ የሚባሉ አልነበሩም።

አይንትራኅት ፍራንክፉርት 2 ለ1 በማሸነፍ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለቀጣይ ዙር የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለመያዝ የነበረውን ዕድል ለጊዜው አምክኖበታል። አንድሬ ሲልቫ በመጨረሻ ደቂቃዎቹ በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ ያሳረፈው ኳስ የሻምፒዮንስ ሊግ ግብ ተሰኝታለች።  ቀዳሚዋን ግብ በ11ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ኒኮ ሹልትስ ነው። ለዶርትሙንድ 44ኛው ደቂቃ ላይ ማትስ ሑመልስ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል።

አትሌቲክስ

ምስል Bob Martin/London Marathon Events/empics/picture alliance

ኬኒያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕንጌቲች ቱርክ ውስጥ በተከናወነው የኢስታንቡል የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር አሸናፊ ኾናለች። ቼፕንጌቲች ትናንት ያሸነፈችበት ውድድር ክብረ ወሰን ቀደም ሲል በኢትዮጵያዊቷ አትሌት አባበል የሻነህ የተያዘ ነበር። ኬኒያዊቷ ሯጭ የግማሽ ማራቶኑ ፉክክርን ያሸነፈችው አንድ ሰአት ከአራት ደቂቃ ከኹለት ሰከንድ በመሮጥ ነው። ክብረ ወሰኑ ቀደም ሲል በኢትዮጵያዊቷ አትሌት አባበል በአንድ ሰአት፣ ከአራት ሰከንድ ከሰላሳ አንድ ሰከንድ የተያዘ ነበር። በውድድሩ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ያለምዘርፍ የሁዋላ አንድ ሰአት ከአራት ደቂቃ ከዐርባ ሰከንድ በመሮጥ በኹለተኛነት አጠናቃለች።ሌላዋ ኬኒያዊት አትሌት ሄለን ኦቢሪ ከያለምዘርፍ 11 ሰከንዶች ዘግይታ በመግባት የሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች።

በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቱ ኪቢዎት ካንዲዬ በማሸነፍ የኬንያን ድል እጥፍ ድርብ አድርጎታል። ኪቢዎት የሀገሩ ልጅ ዝነኛው ሯጭ ጄኦፍሬይ ካምዎሮርን በመቅደም ያገኘው ድል በልዩ ኹኔታ ተመዝግቦለታል። ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜም 59 ደቂቃ ከ35 ሰከንድ ነው። ጄኦፍሬይ ካምዎሮር ኬንያ ኤልዶሬት ከተማ ውስጥ ባለፈው ሰኔ ወር በሞተር ብስክሌት ከተገጨ በኋላ ባደረገው የመጀመሪያ ውድድሩ በጥቂት ሰከንዶች ተቀድሞ የኹለተኛ ደረጃን ይዟል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW