1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 9 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 9 2016

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደተለመደው በተለያዩ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ፉክክሮች ድል ተቀዳጅተዋል ። ግብጽ በበላይነት በምትመራው የአፍሪቃ ጨዋታዎች ምሽቱን ኢትዮጵያ ሁለት ወሳኝ ፉክክሮች ይጠብቋታል ። እጅግ አጓጊ በነበረው የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ ትናንት ቸልሲ በባከነ ሰአት ለድል በቅቷል ።

Champions League | Bayern München - Lazio
ምስል Angelika Warmuth/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደተለመደው በተለያዩ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ፉክክሮች ድል ተቀዳጅተዋል ። ግብጽ በበላይነት በምትመራው የአፍሪቃ ጨዋታዎች ምሽቱን ኢትዮጵያ ሁለት ወሳኝ ፉክክሮች ይጠብቋታል ። እጅግ አጓጊ በነበረው የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ ትናንት ቸልሲ በባከነ ሰአት ለድል በቅቷል ። ሊቨርፑል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የበላይነቱን አሳልፎ ሰጥቷል ።

አትሌቲክስ

ደቡብ ኮሪያ ውስጥ እናንት እሁድ በተካሔደው የሴዑል የማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ድል ተቀዳጁ ።  ብርቱ ፉክክር በታየበት የወንዶቹ የማራቶን ሩጫ አትሌት ጀማል ይመር በአንደኛነት ሲያሸንፍ፤ በሴቶች ደግሞ አትሌት ፍቅርተ ወረታ ለድል በቅታለች ።  አትሌት ጀማል ይመር ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀበት፦ 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ08 ሰከንድ ነው ። ኬንያውያኑ ሮንዛስ ሎኪታም ኪሊሞ እና ኢድዊን ኪፕሮፕ ኪፕቶ ከጀማል በአንድ እና ሁለት ሰከንዶች ብቻ ተበልጠው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል።

በሴቶች ፉክክር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፍቅርተ ወረታ 2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ32 ሰከንድ በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች ። ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የባሕሬን አትሌት ደሲ ጂሳ መኮንን ከ47 ሰከንዶች በኋላ ተከትላ በመግባት የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። በፍቅርተ በ1 ደቂቃ ከ20 ሰከንዶች የተበለጠችው ኬንያዊቷ ቪዝሊን ጄፕኬሾ ሦስተኛ ደረጃ በማግኘት አጠናቃለች ።

ስፔን ላሬዶ ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በተካሔደው የ10 ሺሜትር የሩጫ ፉክክር የቤት ውስጥ ፉክክር ክብረወሰን ባለቤቱ ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ 26.36 በመሮጥ  አሸንፏል ።   ዩጋንዳዊው ጆሽዋ ቼፕቴጊ እና ኢትዮጵያዊው አዲሱ ይሁኔ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል ። የመጋቢት 2 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በሴቶች ተመሳሳይ ርቀት ፉክክር ጀርመናዊቷ ኮንስታንስ ክሎስተርሐልፈን 31:07 በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች ።  ኬንያዊቷ ፒዩሪ ጊቶንጋ እና ስፔናዊቷ ኢርኔ ሳንቼዝ ኤስክሪባኖ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል ።

የኢትዮጵያ ቡድን 62 ወንዶች እና 75 ሴቶች በድምሩ 137 አትሌቶችን አካቷል ።  በሩጫ ፉክክር 89 ወንዶች እና ሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፉበታል ።ምስል Sven Hoppe/dpa/picture alliance

የአፍሪቃ ጨዋታዎች በጋና

ሁለተኛ ሳምንቱን ባስቆጠረው እና የተለያዩ የስፖርት ዘርፎችን በሚያካትተው የአፍሪቃ ጨዋታዎች ግብጽ አሁንም በበላይነት ትመራለች ። ግብጽ እስካሁን 91 የወርቅ፤ 35 የብር እና 30 የነሐስ በድምሩ 156 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አሁንም የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጣለች ። ናይጄሪያ 27 የወርቅ፤ 21 የብር እንዲሁም 30 የነሐስ በድምሩ 78 ሜዳሊያዎችን ሰብስባ የሁለተኛ ደረጃ ይዛለች ። ደቡብ አፍሪቃ በ25 የወርቅ፤ በ29 የብር እና በ38 የነሐስ በድምሩ 92 ሜዳሊያ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገናለች ። እንደ ደቡብ አፍሪቃ ካለፈው ሳምንት ደረጃዋ በአንድ ዝቅ ያለው አልጄሪያ በ22 የወርቅ፤ በ30 የብር እና በ37 የነሐስ በድምሩ 89 ሜዳሊያዎች አራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍራለች ።

የኤርትራ ቡድን 6 የወርቅ፤ 2 የብር እና 5 የነሐስ በድምሩ 13ሜዳሊያዎችን ሰብስቦ ከአንድ እስከ ዐሥር ካሉት ሃገራት ተርታ በመሰለፍ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።

እስካሁን 1 የብር ሜዳሊያ ያገኘው የኢትዮጵያ ቡድን 26ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።  የብር ሜዳሊያው የተገኘው በወንዶች የብስክሌት ፉክክር በኪያ ጀማል ባለፈው ዐርብ ነው ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን እጅግ በሚጠበቅበት የሩጫ ፉክክር ተሳታፊ የሁኑ አትሌቶች በሁለተኛ ዙር ትናንት አክራ ጋና ገብተዋል ።

ጋና አክራ በሚካሄደው የአፍሪቃ ጨዋታዎች እግር ኳስ፤ የእጅ ኳስ፤ ነጻ ትግል፤ ባድሜንተን፤ የውኃ ዋና፤ ጁዶ፤ ቴኳንዶ፤ ብስክሌት፤ ቴኒስና ቡጢን ጨምሮ በ23 የስፖርት ዘርፎች ግጥሚያዎች ይኖራሉ ።  ምስል Sergiy Tryapitsyn/PantherMedia/IMAGO

ከዛሬ እስከ ዐርብ ድረስ በተከታታይ በተለያዩ ርቀቶች የሩጫ ፉክክሮች ይኖራሉ ። የ3000 ሜትር የወንዶች መሰናከል፤ የሴቶች 5000 ሜትር የፍጻሜ ውድድሮች ምሽቱን ይከናወናሉ ። በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ፈጣን ለውጥ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል ። የኢትዮጵያ ቡድን 62 ወንዶች እና 75 ሴቶች በድምሩ 137 አትሌቶችን አካቷል ።  በሩጫ ፉክክር 89 ወንዶች እና ሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፉበታል ።

የፊታችን ቅዳሜ በሚጠናቀቀው የአፍሪቃ ጨዋታዎች፦ እግር ኳስ፤ የእጅ ኳስ፤ ነጻ ትግል፤ ባድሜንተን፤ የውኃ ዋና፤ ጁዶ፤ ቴኳንዶ፤ ብስክሌት፤ ቴኒስን ጨምሮ በ23 የስፖርት ዘርፎች ግጥሚያዎች ይኖራሉ ።  

ኤፍኤ ካፕ

በትናንቱ የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ የማሸነፍ መንፈሱን አነቃቅቷል ። ዐራት ዋንጫዎችን ለማንሳት ያለመው ሊቨርፑል ሕልሙ መክኗል ።  አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ ቡድናቸው ማንቸስተር ዩናይትድ የዘመናት ባላንጣው ሊቨርፑልን ትናንት በኤፍ ኤ ካፕ ድል ማድረጉ ለእሳቸውም ሆነ ለቡድናቸው መነቃቃት እጅግ ወሳኝ እንደነበር ተናግረዋል ። ማንቸስተር ዩናይትድ መጀመሪያ ከ2 ለ1 ከዚያም ከ3 ለ2 መመራት ተነስቶ ፍጻሜውን ወደ 4 ለ3 ድል ገልብጦታል ።

በኤፍ ኤ ካፕ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ ከመጀመሪያው እና መጨረሻው ዐሥር ደቂቃዎች በስተቀር ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ የበላይ የነበረው ሊቨርፑል የማታ ማታ በማንቸስተር ዩናይትድ ጉድ ሆኗል ። አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ እቅዳቸው መክኖ ሽንፈት ተከናንበዋል ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Peter Byrne/dpa/picture alliance

በእርግጥ ከመጀመሪያው እና መጨረሻው ዐሥር ደቂቃዎች በስተቀር ሊቨርፑል ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ የበላይ ነበር ማለት ይቻላል ። ምንም እንኳን ዳርዊን ኑኔዝ ግብዙ ጥረት ቢያደርግ የጨዋታውን መልክ ሊቀይሩ የሚችሉ ኳሶችን አምክኗል ። ሌላኛው ድንቅ ግብ ያስቆጠረው ሐርቬይ ኤሊዮት የፈጠረው ስህተት ማንቸስተር ዩናይትድ በመልሶ ማጥቃት ሊቨርፑልን ጉድ ያደረገ ብሎም የገደለ አጋጣሚ ነበር ። በጉዳት የትሬንት አርኖልድ አለመሰለፍ ሊቨርፑልን ከኋላ መስመር እጅግ ጎድቶታል ። አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ  በክንፍ መስመር የጨዋታውን ፍጥነት ሲዘውር የነበረው አንድሪው ሮቤርትሰንን መቀየራቸውም ግራ የሚያጋባ ነበር ። 

በሌላ መልኩ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ እየተመሩ በነበረበት የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ተከላካይ አስወጥተው ተጨማሪ አጥቂ በማስገባት ደፋር ውሳኔ ዐሳይተዋል ። ድፍረታቸው በእርግጥም ሠርቷል ። ብዙ ሲተች የነበረው አንቶኒ ተቀይሮ በመግባት ማንቸስተርን አቻ የምታደርገውን ወሳኝ ኳስ ከመረብ አሳርፏል ።  የ21 ዓመቱ አይቮሪኮስታዊ አጥቂ አማድ ዲያሎ በመልሶ ማጥቃት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ መላ ኦልድትራፎርድን አስቦርቋል ። የማሸነፊያ ግቧን ካስቆጠረ በኋላ ግን መለያ ካናቴራውን በማውለቁ ቀደም ሲል ቢጫ ካርድ ዐይቶ ስለነበር በቀይ ከሜዳ ወጥቷል ። መልበሻ ክፍል ውስጥ ሆኖ ግን ብቻውን ደስታውን ለማጣጣም አልተገደደም ። ጨዋታው ወዲያው በማንቸስተር ዩናይትድ የ4 ለ3 ድል ተጠናቋል ።

በትናንቱ የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ የማሸነፍ መንፈሱን አነቃቅቷል ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Dave Thompson/AP Photo/picture alliance

ማንቸስተር ዩናትድ ከአንድ ወር በኋላ በግማሽ ፍጻሜው የሚገጥመው እታችኛው ዲቪዚዮን የሚገኘው ኮንቬንትሪን ነው ። ያም በመሆኑ ወደ ፍጻሜ የማለፉ ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ ሳይታለም የተፈታ ነው ። ምናልባትም አሰልጣን ኤሪክ ቴን ሀግ በፍጻሜው ማንቸስተር ሲቲን ወይንስ ቸልሲን ይሆን የምገጥመው እያሉም ይሆናል የሚያሰሉት ።

ቸልሲ ትናንት መደበኛ 90 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በጭማሪ የባከኑ ደቂቃዎች ተጋጣሚው ላይስተር ሲቲን ጉድ አድርጎ 4 ለ2 አሸንፏል ። የማሸነፊያ ግቦቹን በ92 እና 98ኛው ደቂቃ ላይ በድንቅ ሁኔታ ያስቆጠሩት ካርኔይ ቹክዌሜካ እና ኖኒ ማዱዌኬ ናቸው ። በትናንቱ ጨዋታ ቸልሲ የበላይነቱን ዐሳይቶ ነው ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፉን ያረጋገጠው ። ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት በቤርናርዶ ሲልቫ የመጀመሪያው አጋማሽ ግቦች ኒውካስትልን 2 ለ0 አሸንፏል ። ኮንቬንትሪ ሲቲ ደግሞ ዎልቭስን  በገዛ ሜዳው 3 ለ2 ድል አድርጎ ነው ለግማሽ ፍጻሜው የበቃው ።

ሻምፒዮንስ ሊግ

እጅግ በርካታ ተመልካቾችን እና አድናቂዎችን ያፈራው የሴቶች የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናል ። በነገው ዕለት፦ የሆላንዱ አያክስ አምስተርዳም ቡድን የእንግሊዙ ቼልሲን ይገጥማል ። የፖርቹጋሉ ቤኔፊካ ከፈረንሳዩ ሊዮ ጋ ይፋለማል ። ከነገ በስትያ ደግሞ፦ የስዊድኑ ቢኬ ሔይከን የፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ጃርሞን ያስተናግዳል ። የስፔኑ ባርሴሎና የኖርዌዩ ኤስ ኬ ብራንን በብራን ስታዲየም ውስጥ ይገጥማል ። በሚቀጥለው ሳምንት በሚኖሩ የመልስ ግጥሚያዎች የግማሽ ፍጻሜ አላፊ ቡድኖች ይለያሉ ።

እጅግ በርካታ ተመልካቾችን እና አድናቂዎችን ያፈራው የሴቶች እግር ኳስምስል Memmler/Eibner-Pressefoto/picture alliance

የወንዶች የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ አላፊ ቡድኖች የጨዋታ ድልድል ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት ወጥቷል ። በድልድሉ መሰረት፦ የእንግሊዙ አርሰናል የጀርመኑ ባዬርን ሙይንሽንን ይገጥማል ። ሌላኛው የእንግሊዝ ቡድን ማንቸስተር ሲቲ የደረሰው የስፔኑ ብርቱ ቡድን ሪያል ማድሪድ ነው ። የፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ጃርሞ ከስፔኑ ባርሴሎና ጋ ሲጋጠም፤ ሌላኛው የስፔን ቡድን አትሌቲኮ ማድሪድ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድን ያስተናግዳል ። የሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች የሚከናወኑት ከሦስት ሳምንት በኋላ ነው ። የካቲት 26 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ መሪው ባዬርን ሌቨርኩሰን ዘንድሮ ዋንጫ ለማንሳት ግስጋሴውን ቀጥሎበታል ። ባዬርን ሌቨርኩሰን ትናንት ወደ ፍራይቡርግ አቅንቶ በ3 ለ2 ድል ተመልሷል ። የፍራይቡርግ አሰልጣኝ ክርስቲያን ሽትይሽ ከ12 ዓመታት ቆይታ በኋላ በፍራይቡርግየ አሰልጣኝነታቸው እንደማይቀጥሉ ይፋ አድርገዋል ። የ58 ዓመቱ አሰልጣኝ በቡንደስሊጋ አንድ ቡድንን ረዝም ጊዜ በማሰልጠን ሁለተኛው ሰው ለመሆን በቅተዋል።  የቡንደስሊጋው የምንጊዜም የረዥም ዓመታት አሰልጣኝ በመሆን የሚስተካከላቸው ያልተገኘው የሐይደንሀይም አሰልጣኝ ፍራንክ ሽሚድት ናቸው ። የ50 ዓመቱ አሰልጣኝ ቡድናቸው የሐይደንሀይምን ከ16 ዓመታት በላይ አሰልጥነዋል ። የባዬርን ሌቨርኩሰን የትናንቱ ድሉን ጨምሮ እስካሁን 70 ነጥብ ሰብስቦ ቡንደስሊጋውን በአንደኛነት ይመራል ። በ60 ነጥብ የሚከተለው ባዬርን ሙይንሽንም ቅዳሜ ዕለት ዳርምሽታድትን 5 ለ2 ድል አድርጓል ።

የቡንደስሊጋው የምንጊዜም የረዥም ዓመታት አሰልጣኝ በመሆን የሚስተካከላቸው ያልተገኘው የሐይደንሀይም አሰልጣኝ ፍራንክ ሽሚድት ናቸው ። የ50 ዓመቱ አሰልጣኝ ቡድናቸው የሐይደንሀይምን ከ16 ዓመታት በላይ አሰልጥነዋል ምስል Tom Weller/dpa/picture alliance

56 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሽቱትጋርት ሆፈንሀይምን ከትናንት በስትያ 3 ለ0 አሸንፏል ። በ50 ነጥብ ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት አይንትራኅት ፍራንክፉርትን አስተናግዶ 3 ለ1 ሸኝቷል ። የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ኮሎኝን 5 ለ1 ያደባየው ላይፕትሲሽ 49 ነጥብ ሰብስቦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ40 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ማይንትስ በ25 ነጥብ ወራጅ ቀጣናው ግርጌ 16ኛ ላይ ይገኛል ። ኮሎኝ እና ዳርምሽታድ በ18 እና 13 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ሰፍረዋል ። በሳምንቱ ማገባደጃ ላይ በተደረጉ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ ማይንትስ ቦሁምን 2 ለ0፤ ዑኒዮን ቤርሊን ቬርደር ብሬመንን 2 ለ1 አሸንፈዋል ። ለቡንደስሊጋው አዲስ የሆነው ሐይደንሀይም የአውሮጳ ግጥሚያዎች ላይ ብዙ ልምድ ካካበተው ቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋ ተጋጥሞ አንድ እኩል ተለያይቷል ። ቮልፍስቡርግ በሜዳው በአውግስቡርግ የ3 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW