የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 17 2016የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጉዱሩ ወረዳ፣ ባሮ በሚባል ስፍራ ባለፈዉ ሰኞ አደረሰዉ በተባለ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ስምንት ሰዎች መገደላቸውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አስታወቀ።ኦነግ ባወጣዉ መግለጫ በጥቃቱ የተገደሉና የቆሰሉ ያላቸዉን የ10 ሰዎች ስም ዘርዝሯል።የኢትዮጵያ መንግስት ግን የትኛዉም ወታደራዊ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ አያደርግም ብሏል።መንግስት በበኩሉ በየትኛውም ወታደራዊ ጥቃቱ ንጹሃን ዜጎች ኢላማ አይደረጉም ብሏል፡፡
በድሮን ጥቃት ሰዎች ተገደሉ-ኦነግ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በዚሁ ዘርዘር ባለው መግለጫው በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በጠመንጃ የሚደገፍ መጠነሰፊ ጥቃት በመፈጸም ከሷል፡፡ ፓርቲው በዚሁ መግለጫው መንግስት ከውይይት ይልቅ በጠመንጃ አፈሙዝ ችግሮችን ለመፍታት መጓዙ የህዝብ እልቂት፣ የንብረት ውድመትና የአገር ውድቀት ከማስከተል ውጪ ፋይዳ አይኖረውም በማለትም ወቅሷል፡፡
ኦነግ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ታህሳስ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አመሻሹንበሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጉዱሩ ወረዳ ልዩ ስሙ ባሮ በተባለች ስፍራ ተፈጽሟል ባለው የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ስምንት ሰዎች ተገድለው ሌሎች ሁለት ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት በማስተናገድ ከሞት ተርፈዋል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በዚሁ ላይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ ጥቃቱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል፡፡ “የጥቃቱ ኢላማ ባሮ በሚባል ቦታ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ላይ ነው ያረፈው፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው አመሻሽ ላይ ነው፡፡ በዚህም ጥቃት ስምንት ሰዎች ሲሞቱ ሁለት ሰዎች በህይወት ተርፈዋል፡፡ ከጥቃቱ ቆስለው ከተረፉት እንደተረዳንም በአምልኮ ላይ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን እና ፣መንግስት ሰላማዊ ሰዎችን ማጥቃቱን የተረዳንበት” ነው ብለዋል፡፡
የከባድ መሳሪያዎች አጠቃቀም አውድ
የኦነግ መግለጫ ከድሮን በተጨማሪ ከባባድ የእግረኛ ወታደሮች የጦር መሳሪያዎችም በተለያዩ አከባቢዎች ጥቅም ላይ ስውሉ ንጹሃን ዜጎችን ተጎጂ እንደሚያደርጉ ያስረዳል፡፡ እንደ ኦነግ መግለጫ ከባባድ የጦር መሳሪያዎቹ በመኸር ላይ የነበሩ ሰላማዊ አርሶ አደሮችንም የጉዳቱ ሰለባ አድርጓል፡፡ ፓርቲው ለሶስት ዙሮች ተደርጓል ባለው ጥቃቱ የቤት እንስሳትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን አትቷል፡፡
የስምንት ሰዎችን ስም ዝርዝር በሟችነት እና ሁለት ሰዎችን በከፍተኛ የአካል ጉዳት ማስተናገድ የጠቃቀሳቸው ኦነግ፤ ጥቃቱን ኃላፊነት የማይሰመው በሚልም ተችቷል፡፡
የኦነግ የህዝብ ግንኙነትኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ አክለው በሰጡን ማብራሪያ ውጥኑ ህዝቡን በኃይል እርምጃ የማንበርከክ ነው ብለዋል፡፡ “ህዝቡን በኃይል እርምጃ የማንበርከክ ሁኔታ ነው የሚታየው፡፡ ሸማቂ የሚኖረው ቤተክርስቲያን ውስጥ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ይህ ጥቃት የፕሮተስታንት ሙሉወንጌል ቤተክርስቲን ላይ የደረሰ ነው፡፡ ድርጊቱ መንግስት በጦር አፈሙዝ ወደማሳመን መግባቱን ሚያሳይ ነው” ብለዋል፡፡ ኦነግ በዚሁ መግለጫው የመንግስት ጦርን የንጹሃን ዜጎች ግድያ ከመፈጸም ባሻገር በጅምላ እስርና የዜጎችን ቤት በማውደም ከሷልም፡፡ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ይፈጸማል ያለውን የመብት ጥሰት እንዲመለከት በማለትም ጥሪውን አሰምቷል፡፡
የሰው አልባ ወታደራዊ መሳሪያዎች የመንግስት ምላሽ
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ በቅርቡ የአገሪቱ ኢታማጆር ሹም በጉዳዪ ላይ ከሰጡት ማብራሪያ ላይ ተጨማሪ ወታደራዊ ማብራሪያ የመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸው፤ መንግስት በየትኛውም አውድ ንጹሃን ዜጎችን የወታደራዊ ኢላማ የሚያደርግብት ምንም ምክኒያት ባለመኖሩ በሚወሰዱ ወታደራዊ እርምጃዎች ሰላማዊ ዜጎች አይጠቁም በማለት አጠር ያለ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
በቅርቡ የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ በተለይም የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) አጠቃቀምን በተመለከተ ሰራዊታቸው በተጠና መንገድ ሰላማዊ ዜጎችን ከታጣቂዎች ለይቶ እርምጃውን በጥንቃቄ እንደሚወስድ ማብራራታቸው አይዘነጋም፡፡
ለአምስት ዓመታት በኦሮሚያ በተለይም በክልሉ ምእራባዊ አከባቢዎች የቀጠለው የታጣቂዎች እና መንግስት ጦር ውጊያ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ የበዛ ጉዳት ስለመመድረሱ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ