1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጤ ጠል ጥቃት በደቡብ አፍሪቃ ፤የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር የአፍሪቃ ጉብኝት

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 6 2011

በየጊዜዉ የሚያገረሸዉ የደቡብ አፍሪቃ መጤ ጠል ጥቃት ከሰሞኑም በአፍሪቃዉያን የዉጭ ዜጎች ላይ ባነጣጠረ መልኩ ጥቃት ተፈፅሟል።

Südafrika Xenophobie Unruhen Rassimus
ምስል Getty Images/M.Longari

ጥቃት በደቡብ አፍሪቃ፤ የጀርመን የዉጭ ጉዳይሚ/ር ጉብኝት

This browser does not support the audio element.


 በዚህ ጥቃት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች እና የንግድ ተቋሞቻቸው ሰለባ ሆነዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ጥቃቱን ያወገዘ ሲሆን፤ የፕሬዝዳንት ሴሪል ራማፎዛ መንግሥት የኢትዮጵያዉያኑን ጥቃት ያስቆማል። የዜጎቻችን ደኅንነትም ያስጠብቃል የሚል ዕምነት  እንዳለዉ የኢትዮጵያ መንግስት ገልጿል።  በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ሽፈራዉ ተክለማርያም እስካሁን በጥቃቱ ሕይወቱ የጠፋ ኢትዮጵያዊ አለመኖሩን አረጋግጠዉ፤ ኢትዮጵያዉያኑን ከጥቃት ለመጠበቅ እየተሰራ ነዉ ሲሉ ቀደም ሲል ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
ከአንድ ሳምት በላይ የዘለቀዉ በሌላ አፍሪካ ሃገራት ዜጎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካ  ዜጎቻቸዉ  ሰለባ ከሆኑባቸዉ  የአፍሪቃ ሃገራት መካከል ናይጀሪያ አንዷ ናት። ከዚህ ከጥቃት ጋር በተያያዘም ደቡብ አፍሪቃ በናይጄሪያ የሚገኜዉን ኤምባሲዋን እስከመዝጋት ደርሳለች።
ደቡብ አፍሪካ የናይጄሪያውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት የተገደደችው በደቡብ አፍሪካ ናይጄሪያውያን ላይ እየደረሰ ባለው ጥቃት ሳቢያ ናይጄሪያ በሚገኜዉ ኤምባሲዋ ላይ የአፀፋ ጥቃት በመሰንዘሩ ነው። ናይጄሪያ አቡጃ በሚገኜዉ የደቡብ አፍሪቃ ኢምባሲ ጥቃቱን በማዉገዝ ለተቃዉሞ የወጣዉ አቡ መሃመድ የሀገሩ መንግስት ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲያቋርጥ ይፈልጋል።።
«እንደማስበዉ በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ መንግስታት በተለይ  ናይጄሪያ ከደቡብ አፍሪቃ መንግስት ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቆም አለባት ። ይህ ጥቃት በተደጋጋሚ እየተፈፀመ ነዉ። የናይጀሪያ መንግስት ይህንን ጥቃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያስቆም አልያም የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲያቋርጥ እፈልጋለሁ።»
ባለፈው ሳምንት እሁድ የጀመረው በሌላ አፍሪካ ሃገራት ዜጎች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት የብዙዎች ንብረት ተዘርፏል እንዲሁም ወድሟል የሰዉ ህይወትም ጠፍቷል። ያ በመሆኑ ሁኔታዉ በሀገሪቱ በሚገኙ የዉጭ ዜጎች የደህንነት ስጋት አሳድሯል።
ኑኩቶላ ኑዱቩ በንግድ ስራ የምትተዳደር የጀዋንስበርግ ከተማ ነዋሪ ነች። ጥቃቱን ተመልክታለች። እሷ እንደምትለዉ በመቶ የሚቆጠሩ የደቡብ አፍሪቃ ወጣቶች ከማሊ፣ ከዚምባብዌና ከናይጄሪያ የመጡ ዜጎችን ቤት ሲያቃጥሉ ሲዘርፉና ጥቃት ሲያደርሱ በቅርብ ርቀት አይታለለች። ከዚያ ወዲህ እሷም ይሁን ቤተሰቦቿ  የደህንነት ስጋት እንደሚሰማቸዉ ትገልፃለች። እናም ችግሩን በጋራ መዋጋት ይገባል ትላለች።
«ቤተሰቦቼ የደቡብ አፍሪቃዉያን ብቻ አይደሉም። የብዙ አፍሪቃ ሀገሮች ቅልቅል ናቸዉ። እናም ጥቃቱንና ቃጠሎዉን ከቤት ሆኜ ተመልክቸዋለሁ። በጣም በጣም ይጎዳል። ስለ ሁኔታዉ ማዉራትም በጣም ጥሩ አይደለም። ምክንያቱም ሁኔታዉን አይቀይረዉም። ከመንግስታትና ጋር እንዲሁም እንደ አህጉር ከአፍሪቃ ጋር ይህንን ለመዋጋት በጋራ ልንሰራ ይገባል።»
ጥቃቱን የተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት መንግስታት እንዲሁም የአፍሪቃ ህብረት ያወገዙት ሲሆን  የደቡብ አፍሪካ  መንግስትም ለሀገሩ የሚያሳፍር ጉዳይ መሆኑን ገልጾ፤ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ቃል ገብቷል። ያም ሆኖ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ወጣቶች ስራ አጥ  በሆኑባት ደቡብ አፍሪቃ ችግሩ በቀላሉ የሚፈታ እንዳልሆነ ነዉ የሚነገረዉ።
ደቡብ አፍሪቃ ከጠቅላላዉ ህዝብ 30 በመቶ የስራ አጥ ቁጥር ያላት ሲሆን ከዚህም ዉስጥ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነዉን ቁጥር የያዙት ጥቁር ደቡብ አፍሪቃዉያን ናቸዉ። ይህ የስራ አጥነት ችግር  በአነስተኛና በርካሽ ዋጋ በሚሰሩ ጥቁር ድሃ አፍሪቃዉያን ላይ  እንዲበረታ አድርጎታል።  ማቲዉ ቡደን በርግ የጀርመን ደቡብ አፍሪቃ የንግድ ቻንበር ስራ አስፈፃሚ ናቸዉ። በጅዋንስበርግ ለ19 ዓመታት ኖረዋል። የችግሩ መንስኤ ማህበራዊ ኢ ፍትሃዊነት ነዉ ይላሉ። ጥቁር ደቡብ አፍሪቃዉያን ከአፓርታይድ ስርዓት ነፃ ቢሆኑም አሁንም ድረስ በኢኮኖሚ ረገድ ከድህነት ሊወጡ አልቻሉም። ያም ሆኖ  በመንግስት በኩል ስራ አጥነትን ለመቀነስና ኢኮኖሚን ለማሳደግ የሚደረገዉ ጥረት ችግሩን በአግባቡ የሚፈታ አይደለም ነዉ የሚባለዉ። እናም ቡደንበርግ እንደሚሉት በሀገሪቱ የሚታየዉ ዝርፊያ፣ ግድያና በሴቶች ላይ የሚደረግ ጥቃት በፖሊስና ሀይል  ሳይሆን ኢኮኖሚዉን በማሳደግና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የሚፈታ ነዉ።
የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ማስ በዚህ ሳምንት ባደረጉት የአፍሪቃ ጉብኝት መጀመሪያ ያመሩት ወደ ሱዳን ነበር። ማስ ሀገሪቱን ለሶስት አስርተ ዓመታት ያስተዳደሩት ኦማር አልበሽር ከስልጣን ከወረዱ ካለፈዉ ሚያዚያ ወዲህ ሀገሪቱን የጎበኙ የመጀመሪያዉ  የጀርመን ባለስልጣን ናቸዉ።በጉቭኝቱ  ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር የተወያዩ ቢሆንም ብዙ ጊዜያቸዉን ያሳለፉት በተቃዉሞዉ ወቅት ንቅናቄ ሲያደርጉ ከነበሩ ሀይሎች ጋር ነበር።ምክንያቱም መንግስታቸዉ በሱዳን የተካሄደዉን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የመደገፍና ይህንን እዉን ለማድረግ ለታገሉ  እዉቅናና ከበሬታ የመስጠት ፍላጎት አለዉ።እናም የአልበሽርን መንግስት ከስልጣን ለማዉረድም ይሁን እሳቸዉ ከስልጣን ከተወገዱ በኃላ ስልጣን የያዘዉን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት በመቃወም አደባባይ በመዉጣት ትግል ካደረጉ በርካታ የጥበብ ሰዎችና ወጣቶች ጋር በወቅቱ የሱዳን ሁኔታ ላይ ዉይይት አድርገዋል።
የ31 ዓመቷ የፎቶግራፍ ባለሙያ አላ ጃፋር ከተወያዮቹ መካከል አንዷ ናት።አላ በተቃዉሞ ወቅት የነበሩ አሳዛኝ ትይንቶችን በካሜራዋ አስቀርታለች። እነዚህን ፎቶግራፎች በዉይይቱ ወቅት የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ተመልክተዋል።ወጣቷ የፎቶግራፍ ባለሙያ  እንደገለፀችዉ በተቃዉሞ ወቅት አስደንጋጭና አሳዛኝ ሁኔታዎችን ቢገጥሙንም ምንም አማራጭ ስላልነበረን ትግሉ ቀጥለናል ብላለች።
የአላ ካሜራ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉበትን የተቃዉሞ ወቅት ጥቃቶችን ብቻ ሳይሆን ወደ ፍትሃዊ ምርጫ የሚወስደዉን የወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤቱንና የተቃዋሚዎችን ስምምነትም ቀርጿል።የአላ ጃፋር ካሜራ ወደፊትም የሀገሪቱን እድገት፣ አስተማማኝ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲቀርጽ ከሱዳናዉያን ቁርጠኝነት በተጨማሪ ሀገሪቱ ድጋፍ ትሻለች።ጀርመን በዚህ በኩል አወንታዊ ምላሽ የሰጠች ይመስላል። ጀርመን በሱዳን እየተካሄደ ያለዉን የነፃነትና የዲሞክራሲ ጉዞ ከመደገፍ ባሻገር በሰላም፣ በኢኮኖሚና በፀጥታ ጉዳዮች መንግስታቸዉ ከሱዳን ጋር አብሮ ለመስራትና ለመደገፍ  እንደሚፈልግ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃይኮ ማስ በጉብኝቱ ወቅት አረጋግጠዋል።
« ሀገሪቱ በእድገት ትቀጥላለች ወይም ሰዎች ያቀዷቸዉ ግቦችስ ይሳካሉ የሚለዉን በዚህ ሁኔታ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።በዚህ ደረጃ ሀገሪቱ ከጀርመንና ከአዉሮፓ ድጋፍ ያስፈልጋታል።»
የጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ መንግስት የሱዳናዉያን ህይወት ለማሻሻል የገንዘብ ድጋፍ የሚያስፈልገዉ ቢሆንም ሀገሪቱ አሸባሪዎችን ይደግፋሉ ከሚባሉ ሀገሮች ዝርዝር ዉስጥ በመሆኗ  በአሜሪካ ተጥሎባት የቆየዉ ማዕቀብ ዓለም አቀፍ ብድር ለማግኜት ማነቆ ሆኖባታል።ማስ ይህንን ለማስቀቀየር ብዙ ተፅዕኖ ባይኖራቸዉም «የኢኮኖሚ እድገትን የሚደግፍ ማንኛዉም አካል የመንግስታትን ማሻሻያ መደገፍ አለበት »በሚለዉ ሀሳባቸዉ የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሱዳን ሰብአዊ  እርዳታ ከ በዓመት 5 ሚሊዮን የነበረዉን  ወደ 15 ሚሊዮን ዩሮ ከፍ እንደሚል ቃል ገብተዋል። በጎርጎሮሶዉያኑ ከ1989 ዓ/ም ወዲህ ተቀዛቅዞ የነበረዉ የሱዳን  የልማት ዕርዳታም እንደገና ሊቀጥል እንደሚችል ጀርመን ቃል ተብታለች።
የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ሀይክ ማስ ቀጣዩ ጉብኝት ወደ ኮንጎ ሲሆን ወደ ስልጣን ከመጡ 7 ወራትን ብቻ ያስቆጠሩት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ሽስኬዲ ጋር ተወያይተዋል።ፕሬዝዳንቱ ጆሴፍ ካቢላን ተክተዉ ያለፈዉ ጥር ወር ወደስልጣን የመጡ ሲሆን በሀገሬዉ ሰዎች ብዙ ተስፋ የተጣለባቸዉ ናቸዉ።ያም ሆኖ በአንድ በኩል በአመት 2ሺ የሚደርሱ ሰዎችን የገደለዉ የኢቦላ በሽታን በሌላ በኩል የሶስት አራተኛዉ ህዝብ የቀን ገቢ  ከ2 ዶላር በታች መሆን ፈተና ሆኖባቸዋል።
በእርግጥ ቀደም ሲል የነበረዉ የፖለቲካ መከፋፈልና በታጠቁ አማፂ ሚሊሻዎች ይደርስ የነበረዉ ጥቃት ፕሬዝዳንቱ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ  በሀገሪቱ ጋብ ማለቱ ይነገራል።
የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃይኮ ማስ ፕሬዝዳንቱ  ይህንን  ዕድል ተጠቅመዉ ሁኔታዎችን ማሻሻል ይችሉ ዘንድ መከረዋቸዋል። «
የሰወችን ምኞትና ፍላጎት ለማሟላትና ለማረጋገጥ መንግስት እና ፕሬዝዳንቱ በእጃቸዉ ነዉ። አሁን የበለጠ ደህንነት አለ።  የኢቦላ በሽታን በዘላቂነት ለመከላከል ክትትል አለ። እነዚህ ነገሮች ሰዎችን የበለጠ ለመልማት የበለጠ ለማበልፀግ ዕድሎች ናቸዉ። ትምህርት ትልቁና አስፈላጊ ጉዳይ ቢሆንም፤ እንደ እኛ አመለካከት በኮንጎ በሴቶች ላይ የሚደርሰ በደል እንዲሁም አስገድዶ መድፈር ከፍተኛ ነዉ።ይህንን ለማስቆም ስራ መሰራት አለበት። »
የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃይኮ ማስ በጉብኝታቸዉ ቀደም ሲል በኢቦላ በሽታ የተጠቁ አካባቢዎችን የጎበኙ ሲሆን ኮንጎ የሚገኙትን የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ ጋርም በጤናዉ ዘርፍ ለሀገሪቱ ድጋፍ ስለሚደረግበት ሁኔታ ተወያይተዋል።
ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ

ምስል Imago Images/photothek/X. Heinl
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld
ምስል Getty Images/AFP/M.Safodien
ምስል DW/S. Möhl

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW