1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ በጀርመንና አውሮጳ የመሰረቱት ወዳጅነትና ፋይዳው

ማክሰኞ፣ መስከረም 7 2017

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመንን በመጎብኘት የመጀመሪያ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ በጀርመናውያን ዘንድ ያተረፉት መወደድና ክብር ለህዝባቸውም ተርፎ ነበር። ያኔ ጀርመን የሚመጣ ኢትዮጵያዊ ከንጉሱ ሀገር በመሆኑ ብቻ ይከበራል። የዛሬን አያድርገውና ያኔ ጀርመናውያን ኢትዮጵያውያንን በጥሩ ዓይን የሚያዩበት ወቅት ነበር።

አፄ ኃይለ ሥላሴ በጎርጎሮሳዊው1965 ኢትዮጵያን ከጎበኙት ከብሪታንያዋ ንግሥት ኤልሳቤጥ እና ባለቤታቸው ልዑል ፊሊፕ ጋር
አፄ ኃይለ ሥላሴ በጎርጎሮሳዊው1965 ኢትዮጵያን ከጎበኙት ከብሪታንያዋ ንግሥት ኤልሳቤጥ እና ባለቤታቸው ልዑል ፊሊፕ ጋርምስል AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ በጀርመንና በአውሮጳ የመሠረቱት ወዳጅነትና ፋይዳው፤ ክፍል ሁለት

This browser does not support the audio element.

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሸናፊ ፣ ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተገለለችበት በዚያን ዘመን አጼ ኃይለሥላሴ ከሌላው ዓለም ቀድመው ጦርነቱ ወዳደቀቃት ወደጀርመን በጎርጎሮሳዊው 1948 እርዳታ ይዘው በመምጣት በጀርመናውያን ዘንድ በክፉ ቀን ደራሽነት ወዳጅነታቸውን ማጠናከራቸው ብዙ ጥቅሞች አስገኝቷል።  በጦርነቱ የተንኮታኮተው የጀርመን ኤኮኖሚ ካገገመ በኋላ ይህ ውለታቸው ምክንያት ሆኖ በመጀመሪያው የምዕራብ ጀርመን መራኄ መንግሥት በኮንራድ አደናወር ግብዣ፣ በጎርጎሮሳዊው 1954 ጀርመንን በይፋ ለመጎብኘት የበቁ የመጀመሪያው የዓለም መሪ አድርጓቸዋል። በዚህ ጉብኝትም ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር የነበራትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቅታለች። የንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ፍፃሜ፣ የሪፐብሊኪቱ እጣ

አፄ ኃይለ ሥላሴ በአደናወር መቃብር የአበባ ጉንጉን አኑረዋል


የዶቼቬለ የአፍሪቃ ክፍል የጋዜጠኞች ቡድን የጀርመን ክርቲያን ዴሞክራቲክ ኅብረት በምኅጻሩ CDU ፓርቲ ፖለቲከኛ አደናወር የሞቱበት 50ኛ ዓመት የዛሬ 7 ዓመት ሲታሰብ  በቀድሞው የፌደራል ጀርመን ዋና ከተማ ቦን አጠገብ በምትገኘው በባድሆኔፍ ከተማ  ባለችው የሮንዶርፍ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን መኖሪያ ቤታቸውን እና አጠገቡ የተሰራውን በስማቸው የተቋቋመውን የጥናት ተቋም ቤተ መዘክር ጎብኝቶ ነበር። የኮናርድ አደናወር የጥናት ተቋም  የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶክተር ዩርገን ፔተር ሽሚት ያኔ በሰጡት ገለጻ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከአደናወር ጋር የቅርብ ግኝኙት ከነበራቸው መሪዎች አንዱ መሆናቸውን ተናግረው ነበር። አስጎብኝአችን ሽሚት እንዳሉት የአጼ ኃይለ ሥላሴ ጉብኝት በጀርመን ልዩ ቦታ ይሰጠዋል፤ አጼ ኃይለ ሥላሴም ከአደናወር ሞት በኋላ መቃብራቸው ላይ በመገኘት የአበባ ጉንጉንም አኑረዋል።

አፄ ኃይለ ሥላሴ በጎርጎሮሳዊው 1954 ከልዑካን ቡድናቸው ጋር ጀርመንn በጎበኙበት ወቅት ምስል privat


«የመጡት በ1954 ነው። የፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክን የጎበኙ የመጀመሪያው የውጭ እንግዳ ነበሩ። የኃይለ ሥላሴ ጉብኝት በጣም ትልቅ ቦታ ይይዛል ምክንያቱም የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙ የውጭ መሪ ናቸው። ይህ በርግጥ ከብዙ ዓመታት በኋላም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ጀርመን በተፈጸሙት ወንጀሎች ምክንያት ለተገለለችው ለአዲሲቷ ጀርመን ትልቅ ስኬት ነበር። እናም የርሳቸው ጉብኝት የከዚህ ቀደሙን የጀርመን መገለል ያስቀረ እርምጃ ነበር። በ1940 ዎቹም ከጦርነቱ በኋላ ጀርመን በምግብ እጥረት በተቸገረችበትት ወቅትም ኃይለ ሥላሴ ለጀርመን መንግሥት እርዳታ ልከዋል።ኃይለ ሥላሴ አደናወር ከተቀበሩ ከሁለት ሳምንት በኋላ መቃብራቸው ላይ ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አኑረዋል። »የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ከጀርመን ጋር የመሰረቱት ጥብቅ የወዳጅነት ግንኙነትና ፋይዳው

የመጨረሻው የአጼ ኃይለ ሥላሴ የጀርመን ጉብኝት

ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከ1954ቱ ጉብኝት በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ጀርመን መምጣታቸው አልቀረም። ከስልጣን ሊወርዱ አካባቢም ጀርመን ነበሩ። በዚሁ የመጨረሻው የጀርመን ጉብኝታቸው ወቅት አስተርጓሚያቸው በቦኑ የምዕራብ ጀርመን የንጉሠ ነገሥቱ ኤምባሲ ሁለተኛ ጸሐፊና የፕሬስ ጉዳዮች ሠራተኛ አምባሳደር ተፈራ ሻውል የያኔውን የጀርመንና የኢትዮጵያን ግንኙነት ቅርበት በጣም የተሻሻለበት ወቅት ሲሉ ነው የገለጹት።

አፄ ኃይለ ሥላሴ በመጨረሻው የጀርመን ጉብኝታቸው በጎርጎሮሳዊው መስከረም 1973 ቦን በመጡበት ወቅት የምዕራብ ጀርመን መራኄ መንግሥት ቪሊ ብራንት ሲቀበሏቸውምስል picture alliance/AP/Hinninger

ጀርመናውያን ለአጼ ኃይለ ሥላሴ  የሰጡት ክብር ለህዝባቸውም ተርፎ ነበር

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመንን በመጎብኘት የመጀመሪያ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ በጀርመናውያን ዘንድ ያተረፉት መወደድና ክብር ለህዝባቸውም ተርፎ ነበር። አምባሳደር ተፈራ እንዳሉት ያኔ በትምሕርትም ይሁን በሌላ ምክንያት ጀርመን የሚመጣ ኢትዮጵያዊ ከንጉሱ ሀገር በመሆኑ ብቻ ይከበራል። የዛሬን አያድርገውና ያኔ ጀርመናውያን ኢትዮጵያውያንን በጥሩ ዓይን የሚያዩበት ፣በሩ ሁሉ ለነርሱ ክፍት የሆነበት ወቅት ነበር። እንደአምባሳደር ተፈራ ፣ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ናዚ ጀርመንን ካሸነፉት የተባበሩት ኃይሎች ቀጥሎ በጀርመን ትልቅ ክብር የተሰጣት ሀገር ነበረች። ለዚህ ማሳያ ከሆኑት ስምምነቶች አንዱ አፄ ኃይለ ሥላሴ በወቅቱ ከጀርመን ጋር በመሰረቱት ጥብቅ ግንኙነት ኢትዮጵያውያን ለሦስት ወራት ያለ ቪዛ ጀርመን መቆየት መቻላቸው ነው። ዲፕሎማቱ አምባሳደር ተፈራ የዚህ እድል ተጠቃሚ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አንዱ ኛቸው ። ሆኖም ይህ ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ አልቀጠለም። ይሁንና ኢትዮጵያ ከኃይለ ሥላሴ በኋላ ከምዕራብም ሆነ ከምሥራቅ ጀርመን ጋር የነበራት ግንኙነት ሚዛናዊ  ሆኖ ቀጥሏል።

አፄ ኃይለ ሥላሴ በጎርጎሮሳዊው 1963 አሜሪካንን ሲጎበኙ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ጋር በግልጽ አውቶሞቢል ላይ ሆነው በዋይት ሀውስ ፊት ለፊት ሲያልፉምስል Prince Ermias Sahle-Selassie

ከሩስያና ከቻይና ጋር የመሰረቱት የወዳጅነት ግንኙነት


የቀ/ኃ/ሥ ኪነ-ቅርፅና ትችቱ

ዶቼቬለ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን የተነሱበትን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ያነጋገራቸው ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አሥራተ ካሳ የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ ፣ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከጀርመን ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የአውሮጳ ሀገራት እንዲሁም ከሩስያ እና ከቻይናም ጋር ጥብቅ ግንኙነቶችን መመስረታቸውን አስታውሰዋል።

 ደርግ የዛሬ 50 ዓመት ከሥልጣን አስወግዷቸው ፤በኋላም በታሰሩበት በትራስ ታፍነው መገደላቸው የተረጋገጠው የኢትዮጵያው የመጨረሻ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሦላሴ በሥልጣን ዘመናቸው ከአውሮጳ ሀገራት በተለይም ከጀርመን እንዲሁም ከሩስያና ከቻይና ጋር የመሰረቱትን ጥብቅ ወዳጅነትና ፋይዳውን ወደ ኋላ መለስ ብሎ የቃኘው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን ለማዳመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ያዳምጡ


ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW