1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙሴቬኒ ያገዛዝ ስልት

ቅዳሜ፣ ጥር 8 2013

በዘመን ሒደት እድሜም፣ ጤናም፣ አዕምሮ-ጉልበትም መክዳቱን...አለመቀበላቸዉ ነዉ የአንጋፋዉ ፖለቲከኛ ጥፋት።ከ1971 ጀምሮ እንደአለቃ የተከተለ፣ የታዘዘ፣ ያገለላቸዉን ታማኛቸዉን፣ ከ1986 ጀምሮ እንደ መሪ የተገዛ፣ያከበረ፣የደገፈ-ያደነቀቸዉ ሕዝብ እንደ፣ እንዳከበራቸዉ ሊሰናበቱት አለመፈለጋቸዉ ነዉ-ሙጋቤን እንጂ ኔሬሬን ያለመሆናቸዉ ዋቢ።

Bildkombo | Yoweri Museveni und Bobi Wine

የሙሴቬኒ ያገዛዝ ስልት፣የዩጋንዳ ምርጫ፣

This browser does not support the audio element.

እሳቸዉ፣ «በተለይ ተቃዋሚዎቹ፣ ሰዉ ድምፅ እንዳይሰጥ እያገዱ ነዉ።» እሱ«ይሕን፣ የ1986ቱን  አምባገነናዊ ዝንባሌን እንድትቃወሙ እንጠይቃለን።»ዩጋንዳ በርግጥ መረጠች።ሐሙስ።ሙሴቬኒና ዋይኒ።እሳቸዉና እሱ።ጠመንጃና ጊታር።ካርዱ ይገላግላቸዉ ይሆን?                                        
            
ሮበርት ክያጉላኒ ወይም ቦቢ ዋይን «1986 ላይ ያለን ይመስል» ይላል ደጋግሞ።1986 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ያኔ እሱ እንደ 4 ዓመት ጨቅላ ድክድክ ሲል፣ እሳቸዉ፣ እንደ ጦር ጄኔራልም፣እንደ ሲቢል ፖለቲከኛም የመሩት ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የፕሬዝደንት ሚልተን ኦቦቴን መንግስት አስወግዶ እሳቸዉን ካምፓላ ቤተ-መንግስት ዶለ።ዘንድሮ 35ኛ ዓመቱ።
 «ከ1971 ጀምሮ ትግል ላይ ነኝ።የሽምቅ ዉጊያችን 16 ዓመታት አስቆጥሯል።አሁን ትግሉን ግማሽ መንገድ ላይ አቋርጬ ልተወዉ?ፖለቲካ ራሱ ትግል ነዉ።ልዩነቱ አሁን የምንታገለዉ ጫካ ሆነን ሳይሆን የመንግስት ሥልጣን ይዘን መሆኑ ነዉ።»
ብለዉ ነበር ባንድ ወቅት።ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ።ለስልጣን የበቁት ፕሬዝደንት ኢዲ አሚን ዳዳና ሚልተን ኦቦቴን የመሳሰሉ አምባገነኖችን ለ16 ዓመታት በነፍጥ ተዋግተዉ፣ የቅርብ ጓዶቻቸዉን ጨምሮ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዩጋንዳዉያን ወጣቶችን ሰዉተዉ ነዉ።ሸማቂ ከሚባሉ ይልቅ «የነፃነት ታጋይ» መባሉን ይመርጣሉ።
የነፃነቱ ታጋይ አምባገነኖችን አስወግደዋል።ዩጋንዳን ያወደመዉን የርስበርስ ጦርነት አስቁመዉ ሠላም አስፍነዋል።የዩጋንዳ የቀድሞ ቅኝ ገዢ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ዊንስተን ቸርችል «የአፍሪቃ ዕቁ» ያሏቷን ምሥራቅ አፍሪቃዊት ሐገርን እንበለ-ሰዉ ያስቀራታል ተብሎ የተፈራዉን የኤድስ ስርጭትን  ተቆጣጥረዋል።
ለምዕራባዉያን ታማኝነታቸዉን አስመስክረዋል።የዚያኑ ያክል እንደማንዴላ ባይሆን-እንደ ኔሬሬ ለአፍሪቃና ለአፍሪቃዉያን ክብር ተሟግተዋል።ዘመኑ ግን ራቀ።ትዉልዱም ተለወጠ።በዩጋንዳ የጀርመኑ የፍሬድሪሽ ኤበርት ሽቲፍቱንግ ጥናት ተቋም ኃላፊ ማራይከ ሌ ፔሊይ እንደሚሉት ሙሴቬኒ የዘመኑን ርቀት-የትዉልዱን መለወጥ አልተገነዘቡትም።ወይም የተገነዘቡ አይመስሉም።
 «ብዙ ዩጋንዳዉያን የጦርነቱን ዘመን አያስታዉሱም።የተወለዱት ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ነዉ።ዩጋንዳ የወጣቶች ሐገር ናት።አብዛኛዉ ወጣት ሥራ ይፈልጋል።ከዩጋንዳ ሕዝብ 78 ከመቶዉ ከ30 ዓመት በታች ነዉ።50 ከመቶዉ ደግሞ ከ15 ዓመት በታች ነዉ።ፍላጎቱ ካልተሟላላት ተስፋ መቁረጡ ይባባሳል።»   
በዘመን ሒደት እድሜም፣ ጤናም፣ አዕምሮ-ጉልበትም መክዳቱን፣ አዳዲስ አስተሳሰብ መጎምራቱን አለመቀበላቸዉ ነዉ-የአንጋፋዉ ፖለቲከኛ ጥፋት።ከ1971 ጀምሮ እንደአለቃ የተከተለ፣ የታዘዘ፣ ያገለላቸዉን ታማኛቸዉን፣ ከ1986 ጀምሮ እንደ መሪ የተገዛ፣ያከበረ፣የደገፈ-ያደነቀቸዉ ሕዝብ እንደ፣ እንዳከበራቸዉ ሊሰናበቱት አለመፈለጋቸዉ ነዉ-ሙጋቤን እንጂ ኔሬሬን ያለመሆናቸዉ ዋቢ።
እንዲያዉም አሁንም እታገላለሁ ባይ ናቸዉ።ትግሉ ግን  ከእሳቸዉ የመጨረሻ ልጅ በሁለት ዓመት፣ ከእሳቸዉ በ38 ዓመት ከሚያንሰዉ፣ ከ38 ዓመቱ ድምፃዊ-ፖለቲከኛ ጋር ነዉ።የትግሉ ሥልትም  ምርጫ እንጂ በርግጥ ጠመንጃና ዉጊያ አይደለም።የ76 ዓመቱ አሮጌ አንበሳ ግን በምርጫዉም ቢሆን «እጅ አልሰጥም» እንዳሉ ነዉ።
«እጅ አልሰጥም» ባይ አምባገነኖችን ለማስወገድ 16 ዓመት በነፍጥ የታገሉት ሽማግሌ ፖለቲከኛ፣ ከ34 ዓመት ዘመነ-ሥልጣን በኋላም፣ ከ34 ዓመት በፊት ያሰወገዷቸዉን አምባገነኖች ዓይነት የመሆናቸዉን ዚቅ «አለመታደል» ይለዋል ተቀናቃኛቸዉ ቦቢ ዋይን።
«ሙሴቬኒ እኔን በሚያክሉበት በዚያ ዘመን አግኝቼያቸዉ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ጓደኛሞች እንሆን ነበር።ምክንያቱም አሁን እኔ የምላቸዉን አብዛኞቹን ነገሮች፣ ሙሴቬኒ እኔን ያክሉ በነበረበት በ1980ዎቹ ይሏቸዉ ነበር።ጫካ ገብተዉ ለመዋጋት ያሳመፃቸዉን የቀድሞዉን መንግስት ምግባሮች አሁን ራሳቸዉ መድገማቸዉ በርግጥ አለመታደል ነዉ።»
 ለሐሙሱ ምርጫ የተደረገዉ የምረጡኝ ዘመቻ በተጋጋመበት ባለፈዉ ሕዳርና ታሕሳስ ሙሴቬኒ በተቃዋሚዎቻቸዉ ላይ ያዘመቱት ፀጥታ አስከባሪ ከ10 የሚበልጡ ሰዎችን ገድሏል።ብዙ መቶዎችን አስሯል።ሙሴቬኒ ዋነኛ ተቀናቃኝ የቦቢ ዋይን ጠባቂ ሳይቀር በመኪና አደጋ ተገድሏል።
ድምፃዊዉ የምክር ቤት እንደራሴ እንደሚለዉ ጠባቂዉን የገደሉት ፀጥታ አስከባሪዎች ናቸዉ።እራሱ ዋይን ካንዴም-ሁለቴ ሶስቴ እየታሰረ ተፈትቷል።የምርጫዉ ዕለት ሲቃረብ ደግሞ አብዛኛዉ የዩጋንዳ ወጣት የሚያዘወትረዉን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴን አስዘግተዋል።ሁሉንም አድርገዉ፣ ለሁሉም ድርጊት ተቃዋሚዎችን ይወነጅላሉ።
«ወከባ ይፈፀማል።በተለይ ተቃዋሚዎቹ ሕዝቡ ድምፅ እንዳይሰጥ እያስፈራሩት ነዉ።አንዳድ አካባቢዎች ደግሞ ሰላማዊ ዜጎችን እስከ መደብደብ ደርሰዋል።»
የሐሙሱን  ምርጫ ለመታዘብ ያመለከቱ አብዛኞቹ የሲቢል ማሕበረሰብ ቡድናት ፈቃድ አላገኙም።ዩናይትድ ስቴትስም  የምትፈልገዉን ያክል ታዛቢ ለማሰማራት ፈቃድ በመከልከሏ አጠቃላይ ምርጫዉን ከመታዘብ ራስዋን አግልላለች።የአፍሪቃ ሕብረትና የምሥራቅ አፍሪቃ ማሕበረሰብ ታዛቢዎችን የድምፅ አሰጣጡን ሒደት ተከታትለዋል።የሙሴቬኒ ዋነኛ ተቀናቃኝ ቦቢ ወይን እንደሚለዉ ደግሞ የድምፅ አሰጣጡን ሒደት የሚከታተሉ ተወካዮቹ ከብዙ የምርጫ ወረዳዎች ተባርረዋል።
«ከ22 ወረዳዎች የኛ ቡድን አባላት፣ የኛ የድምፅ ቆጠራ ተወካዮች፣አስተባባሪዎችና ረዳቶች ልክ እንደወንጀለኛ በፖሊስና በጦር ሠራዊት በመከበባቸዉ ከየድምፅ መስጪያዉ አካባቢ ሸሽተዋል።»
ሙሴቬኒ ከሐሙሱ ምርጫ በፊት አምስቴ ተወዳድረዉ አምስቴም አሸንፈዋል።ሰዉዬዉ ተዋግተዉም፣ ተሟግተዉም፣ ተወዳድረዉም ማሸነፍን እንጂ ሽንፈትን አይቀበሉም።አይወዱምም።በ1990ዎቹ መጀመሪያ ዓለም «መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ» እያለ ሲዘምር እሳቸዉ፣ «የብሔራዊ ተቋቁሞ ንቅናቄ» (NRM በምሕፃሩ) ከሚባለዉ የፖለቲካ ፓርቲ ዉጪ ሌላ ፓርቲ ዩጋንዳ ዉስጥ እንዳይኖር በሕገ-መንግስት አሰሩት።
የመድብለ ፓርቲን የሚከለክለዉ ሕግ-መንግስት በፀደቀ በ10ኛዉ ዓመት ግድም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሰበብ አስባቡ አዳክሞ ማሸነፍ እንደሚቻል ርግጠኛ ሲሆኑ ሕገ-መንግስቱን አሻሽለዉ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ፈቀዱ።2005።
አንድ ነገር ግን ሳይዘነጉ አልቀሩም።የፕሬዝደንቱን ዘመነ-ሰልጣን በሁለት ዘመን የሚገድበዉን አንቀፅ ሳይቀይሩት አለፉ።ጥቂት ከረምረም ብለዉ፣ የፕሬዝደንቱን ዘመነ-ሥልጣን በሁለት ጊዜ የሚገድበዉን አንቀፅ አስ-ሰረዙት።ፕሬዝደቱ እሳቸዉ ናቸዉ።ስድስቴም አይደል፣ እድሜ ከሰጣቸዉ 10ሬም መመረጥ እንዲችሉ አድርገዉ በሕገ-መንግስት አጠሩት።
ለሙሴቬኒ 6ኛ፣ ለቦቢ ዋይን የመጀመሪያ በሆነዉ በሐሙሱ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ 45 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የዩጋንዳ ሕዝብ 18 ሚሊዮኑ ድምፅ ሰጥቷል ተብሎ ይገመታል።የሐሙሱ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት ሰላማዊ ነበር።ዉጤቱ ሲቆጠር ትናንት ግን ወቀሳ፣ አቤቱታ፣ ዉዝግብ፣እስራት-እገታዉም እንደገና ብሷል።

ምስል Abubaker Lubowa/REUTERS
ምስል Baz Ratner/REUTERS
ምስል Jerome Delay/AP/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW