1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙቀት ማዕበል እና ድርቅ በአውሮጳ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 10 2014

ለወትሮው ስለድርቅ ሲነገር በግንባር ቀደምትነት የሚነሱት የአፍሪቃ እና የእስያ ደሀ ሃገራት ነበሩ። ዘንድሮ ድርቁ በኤኮኖሚ ወደበለጸጉት ሃገራትም ጎራ ብሏል።

Record drought threatens Europe's grain
ምስል DW

ጤና እና አካባቢ

This browser does not support the audio element.

የአየር ጠባይ ለውጥ መባባሱ በተግባር እየታየ ባለበት በዚህ ወቅት በርካታ የአውሮጳ ሃገራት ታላላቅ ወንዞች ውኃቸው ቀንሶ ወደ መድረቅ እያዘነበሉ ነው። ለበርካታ ሳምንታት የሙቀት ማዕበል የሚያስተናግዱት የአውሮጳ ሃገራት ከ500 ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ መጋፈጥ ጀምረዋል። 

ጀርመን በክረምት ቅጠላቸውን የሚያረግፉ ዛፎቿ ልምላሜ የሚላበሱት ቅዝቃዜው ለቅቆ የሙቀቱ ወራት ሲጀምር ነው። በበጋ ምድረ ጀርመን የኤደን ገነት ተምሳሌት ሆና ካለፍ አገደም በዚህ ወቅት የምታስተናግደው ዝናብ አየሩን እያቀዘቀዘ ሙቀቱ እንደተናፈቀ ወደ ክረምቱ ቅዝቃዜ መዝለቋ የተለመደ ነበር። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ክረምቱ ከጭለማው በቀር በአብዛኛው አካባቢ እንደወትሮው እጅግ የጠና ቅዝቃዜ የለውም። በጋው ሲመጣም ሙቀቱ ከአየሩ አልፎ ሣር ቅጠሉን ሲያደርቀው እያየን ነው። የዘንድሮው የበጋ ወቅት ደግሞ በዚህም አላበቃም፤ ለሳምንታት የዘለቀው የሙቀት ማዕበል የጀርመንን የውጪ ንግድ ከሚያቀላጥፉ መስመሮች ዋነኛ የሚባለውን የባሕር መጓጓዣ ስጋት ላይ ጥሎታል። ራይን ወንዝ አውሮጳ ውስጥ ካሉ እና እጅግ ለሥራ ከዋሉ ወንዞች አንዱ ነው። ለጀርመን ደግሞ ከጠለ በረከትነቱ ባሻገር የኤኮኖሚዋ መንቀሳቀሻ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ቦን የሚገኘው የዶቼ ቬለ ቀጥታው ስቱዲዮ ሕንጻ ከጀርባው የተደገፈው የራይን ወንዝን እንደመሆኑ ውኃው ሲፈስ፣ በላዩም የሥራም ሆነ የመዝናኛ ጀልባዎች ሲመላለሱበት መመለከት የተለመደ ነው። አሁን ግን ውኃው ቀንሶ ራይን ወንዝ የሚያስተናግደው የወትሮው እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል። ከቢሯችን ባሻገር በመስኮት በቀላሉ ይታየን የነበረው የራይን ወንዝ ውኃም ወርዷል። በአንዳንድ አካባቢዎች እንደውም የወንዙ የታችኛው ክፍል በቀላሉ የሚደረስበት በመሆኑም በውኃው ላይ የሚመላለሱ ትላልቅ መርከቦች ለጊዜው ሥራቸውን መቀጠል እንዳይችሉ ችግር መፍጠሩን መርከበኛው ካፒቴን አንድሬ ኬምፕል ይናገራሉ። ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ የውኃ መቀነስ ወንዙ እንደሚያጋጥመው ያስታወሱት መርከበኛው የዘንድሮው ግን ከወትሮው እንደባሰ ነው ያመለከቱት። በእሳቸው ግምትም የአየር ንብረት ለውጥ መዘዙ በግልጽ እየታየ ነው።

መጓጓዣው የራይን ወንዝ የአሁኑ ይዞታምስል Christoph Reichwein/dpa/picture alliance
ምስል Jochen Tack/picture alliance

«ቀልድ አይደለም። 1 ሜትር ከ50  ጥልቀት ነው ውኃው ያለው፤ የእኛ መርከብ ደግሞ 1 ሜትር ከ20 ነው በውኃው ውስጥ የምትጠልቀው። እናም ውኃው የተኛበትን መሬት ለመንካት የ30 ሴንቲ ሜትር ልዩነት ብቻ ነው የቀረው።»

የራይን ወንዝ የመርከብ መጓጓዣ በአብዛኛው ለጀርመን የኃይል ምንጭነት የሚፈለገውን የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ እና ጋዝ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ማጓጓዣ መሆኑ ነው የሚገለጸው። ካፒቴኑ እንደሚሉት አሁን እንዲህ ባለው የወንዙ ጥልቀት ላይ የሚጫነው ጭነት መቀነስ ይኖርበታል። ያ ማለት ደግሞ ለጀርመን የኃይል ምንጭነት የሚፈለገውን የድንጋይ ከሰል በብዛት ማጓጓዝ የሚቻል አይሆንም። 

የወንዞቿ ውኃ የቀነሰባት ጣሊያን ምስል DW

በአውሮጳ ካሉና ከፍተኛ የሥራ አገልግሎት ከሚሰጡ ወንዞች አንዱ ራይን ወንዝ ለጀርመን ደግሞ ረዥሙ እና በርካታ ከተሞችን አቋርጦ የሚፈስ ወንዝ በመሆኑ ይታወቃል። መነሻው ደቡብ ምሥራቅ ስዊትዘርላንድ የሆነው ራይን ወንዝ የፈረንሳይ እና ጀርመን ድንበሮችን በመታከክ የተለያዩ ታዋቂ የጀርመን ከተሞች አቋርጦ ወደ ሆላንድ በመፍሰሱ ሃገራቱን በኤኮኖሚው እንቅስቃሴ ማስተሳሰር አስችሏል። የራይን ወንዝን የውኃ መጠን የሚከታተሉ ተቋማት ይፋ እንዳደረጉት በተለይ የሙቀቱ መጠን በተባባሰበት በያዝነው  የነሐሴ ወር እጅግ ቀንሶ ጥልቀቱ እስከ 70 ሴንቲ ሜትር ሊወርድ ይችላል።

የራይን ወንዝ ይዞታ በጀርመንምስል Rolf Kosecki/picture alliance

በምዕራብ ጀርመን ራይን ወንዝ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የውኃው መጠን እጅግ ቀንሷል። ለወትሮው በተለይ ኮሎኝ ከተማ የወንዙ ጥልቀት ሦስት ሜትር እንደነበር ነው የተነገረው። አሁን 85 ሴንቲ ሜትር መድረሱን በስፍራው የተገኘችው የዶቼ ቬለ ዘጋቢ ተመልክታለች። በሌሎች አካባቢዎችም ወደ 40 ሴንቲ ሜትር መውረዱም ተመዝግቧል።

ኮሎኝ ከተማ በራይን ወንዝ ላይ ወደሚያስተናግዱት የመርከብ ምግብ ቤቶች መጥተው ሁኔታውን ይመለከቱ ከነበሩት ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዮርክ ብሎክ ወንዙ ከሚነሳበት አካባቢ ዝናብ ቢጥል መጠኑ ሊጨምር እንደሚችል ተስፋ ያደርጋሉ።

«በእርግጥ ስዊዘርላንድ እና ደቡብ ጀርመን አካባቢ ዝናብ ይጥላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ያኔም ጀልባዋን ሊያንሳፍፋት የሚችል ውኃ ይገኛል እናም ዳግም ልትንሳፈፍ ትችላለች።»

ሌሎቹ ታዛቢዎች ደግሞ የወንዙ ውኃ መቀነስ ስጋት እንደፈጠረባቸው አልሸሸጉም።

በውኃ ተከባ ውኃ ያጠራት ሆላንድምስል Moritz Wolf/imageBROKER/picture alliance

«የራይን ወንዝ ውኃ ወትሮ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር መጠኑ መቀነሱ በጣም አሳሳቢ ነገር ነው።»

 «የድርቁ ሁኔታ በጣም አሳስቦኛል፤ ውኃው በመቀነሱ የመርከብ እንቅስቃሴው ተቸግሯል፣ ዓሣዎቹ ተቸግረዋል እንዲሁም የአካባቢው ተፈጥሮ በሙሉ ችግር ገጥሞታል።»

በወንዙ ላይ የሰዎችም ሆነ የዕቃ ማጓጓዣ መርከብ የሚያሽከረክሩ መርከበኞች ውኃው መቀነሱ ሥራቸውን ማስተጓጎሉን ቢያረጋግጡም አንዳች መፍትሄ አይጠፋም የሚል ተስፋ አላቸው። ኒክላስ ቲል ሰዎች እና ዕቃ በራይን ወንዝ ላይ ከሚያጓጉዙ አንዱ ናቸው።

«እንግዲህ ከሁኔታው ጋር መላመድ ይኖርብናል፤ መርከቦቹንም እንዲያው ማድረግ ነው። አስፈላጊ ከሆነም አነስተኛ መርከቦችን መጠቀም ይኖርብናል።»

አሁን ግን ለጊዜው እንደመፍትሄ የወሰዱት የጭነት መጠናቸውን መቀነስ ነው። የዛሬ አራት ዓመት በታየው ታሪካዊ ድርቅ የውኃው መጠን በጣም መቀነሱን ያስታወሱት በበጀርመኑ ፖስትዳም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምርምር ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ሀገን ኮኽ ክስተቱ መደጋገሙን አጽንኦት ይሰጣሉ።

«በ2018 ከነበረው ድርቅ በኋላ ይኽ ነገር በድንገት የተከሰተ ነው ወይስ በ200 ዓመታት አንዴ የሚያጋጥም ይኾን ስንል ራሳችንን ጠይቀናል። ነገር ግን አሁን ከአራት ዓመታት በኋላ በተመሳሳይ መልኩ አጋጥሞናል። ለወደፊትም ሁኔታው ተደጋግሞ በብዛት የሚከሰት ይመስላል።»

ምስል DW

አሁንም በቀጣይ ቀናት የውኃው መጠን መቀነሱ እንደሚጨምር ብዙዎች ስጋት አላቸው። በዚህ ምክንያትም በወንዙ ላይ የሚኖረው እንቅስቃሴ ሊደናቀፍ እንደሚችልም ይገመታል።

በዚህ የየሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት የራይን ወንዝ ብቻም አይደለም የውኃው መጠን የቀነሰው፤ በበርካታ ግዛቶቿ የድርቅ ሁኔታ መኖሩን ይፋ ባደረገችው ብሪታንያ የሚገኘው ቴምስ የተሰኘው ወንዝም የውኃ መጠኑ መቀነሱ ይፋ ሆኗል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉትም የብሪታንያዊ ቴምስ ወንዝ ከ1976 ዓም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዙሪያ ገባው መድረቁ አሳሳቢ ሆኗል። ሁኔታው ያሰጋው የብሪታኒያ መንግሥትም በአንዳንድ አካባቢዎች የጓሮ አትክልት ማጠጣትም ሆነ መኪና ማጠብ እና የመሳሰሉትን በሕግ ወደ ማገድ ሊገባ እንደሆነም ተሰምቷል።

የደረቀው የብሪታንያ ወንዝምስል Andrew Matthews/PA Wire/dpa/picture alliance

ተመሳሳይ የወንዝ መጠን መቀነስ ጣሊያንም ውስጥ አጋጥሟል። ለወትሮው በበጋ ወራት ቱሪስቶች በጀልባ ይዝናኑባቸው የነበሩ ወንዞች አካባቢያቸው ደርቆ በባዶ የመዝናኛ ጀልባዎች መታየታቸው የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል። ስፔን ከ1995 ወዲህ አይታው በማታውቀው የድርቅ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። የቅዝቃዜው ወቅት ሲያልፍ በለመለሙ እርሻዎች የሚሸፈኑ መስኮቿ ዘንድሮ አፈራቸው ተሰነጣጥቆ የድርቅ ምልክት ሆነዋል። በፈረንሳይም የሁለት ወንዞች ውኃ መጠን ባልተለመደ መልኩ በጣም መቀነስ ድርቅ ወደ አውሮጳ የመዝለቁ ማሳያ ተደርጓል። ኔዘርላንድስ ደግሞ በውኃ እጥረት ምክንያት ለ10 ቀናት የጓሮ አትክልትን ማጠጣት፣ በጀልባ መንሸራሸርን እንዲሁም አጠቃላይ በእርሻው ላይ የውኃ አጠቃቀም ገደብ ጥላለች። ሆላንድ ከአውሮጳ በውኃማነቷ የምትታወቅ ቢሆንም አሁን ከተራዘመው ድርቀት ጋር ግብግብ ይዛለች። ኔዘርላንድስ የታወቁ ግድቦች ያሏት፣ ከመስኖ በተጨማሪ በየከተሞቿ በየሰው ደጃፍ በቦይ የሚፈስ ውኃ ያላት፣ ከሀገሪቱ የየብስ አካል ሦስት አራተኛው ከባሕር ጠለል በታች በመሆኑ አንድ ቀን በውኃ ትዋጣለች የሚል ግምት ቢኖርም በአሁኑ ጊዜ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋልጣ ድርቅ እንደጸናባት እየተነገረ ነው። ከተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት የሚወጡ ሁኔታውን የሚያሳዩ የቪዲዮ ዘገባዎች «ይኽ የምታዩት ዘወትር በድርቅ መጠቃቱ የሚነገርለት አፍሪቃ አይደለም» በሚል መንደርደሪያ ይታጀብ ጀምሯል። ድርቁ ደግሞ የእርሻውን ዘርፍ ሊጎዳው እንደሚችል ምልክቶች እየታዩ ነው። ለምሳሌ ስፔን ውስጥ ለጤና የሚመከረው የወይራ ዘይት እና የአቮካዶ ዛፍ በቁሙ እየደረቀ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። የአየሩ ድርቀትም ከሙቀቱ ጋር ተደማምሮ በያለበት የሰደድ እሳት አስነስቷል። የተራዘመው ድርቅ እና የዝናብ መጥፋት የደረቁት ዛፎች በመብረቅ ሳይቀር በእሳት እንዲለኮሱ ምክንያት መሆኑ ነው የሚገለጸው። በዚህም ስፔንን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት፣ ፓስፊኪን ተሻግሮም ዩናይትድ ስቴትስ እና ሜክሲኮ፣ እንዲሁም አውስትራሊያ አልፎም በአፍሪቃ ሞሮኮ ዘለግ ላለ ጊዜ የተራዘመውን የሰደድ እሳት ለማጥፋት ትግል ይዘዋል። በዚህ መሀል ታዲያ በተለይ በጀርመን እና አካባቢው የአየር ጠባይ ትንበያው በቀጣይ ቀናት ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል ያመለክታል። ሆኖም ምን ያኽል ዝናብ በተከታታይ ቢዘንብ የቀነሰውን የወንዞቹን ውኃ ዳግም ወደነበረበት ይመልሰዋል፣ የደረቀውንስ መሬት እና ደን ያረሰርሰዋል የሚለው ግን ትልቅ ጥያቄ ነው።

ምስል W. Layer/blickwinkel/picture alliance

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW