1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙቀት ማዕበል

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 30 2011

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በመላው ዓለም የአየር ጠባዩ ከፍተኛ ሙቀት እያስተናገደ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሳይንቲስቶች ታዲያ ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ገሃድ እየሆነ የመምጣቱ ማሳያ ካልሆነ ምን ሊባል ነው? ማለት ጀምረዋል። በእርግጥ የአየር ንብረት ለውጥ እውን ሆነ?

Grönland Wiese Eisberge
ምስል picture-alliance/Mary Evans Picture Library

« የአየር ንብረት ለውጥ መገለጫዎች»

This browser does not support the audio element.

በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት በቀን መቁጠሪያው መሠረት በይፋ ሳይገባ ጀምሮ ነው ዘንድሮ ከፍተኛ ሙቀት በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት የተከሰተው። ያልተለመደው የአየር ጠባይ ያስከተለው ሙቀት ከባቢ አየሩን ብቻ ሳይሆን መሬቱንም አድርቆ መታየቱ የበለፀጉት ሃገራት ከወዲሁ ስለውኃ እጥረት እንዲሰጉ አድርጓል። ሳይንቲስቶች ለምሳሌ በፈረንሳይ እና በኔዘርላንድስ ባለፈው ሐምሌ የተመዘገበው የሙቀት መጠን በታሪክ በአንድ ሺህ ዓመት ውስጥ እንኳ ታይቶ አይታወቅም ባይ ናቸው። በአርክቲክ አካባቢ በፍጥነት መቅለጥ የጀመረው የበረዶ ተራራ እንደወንዝ ሲፈስስ በቪዲዮ ያሳዩት ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅ ካስፐር ሃርሎቭ በአንድ ቀን 10 ቢሊየን ቶን ግግር በረዶ በግሪንላንድ ቀልጦ ውኃው ከወንዝ ተቀላቅሎ ሲወርድ ማስረጃ ይፋ አድርገዋል። በረዶው የቀለጠው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መሆኑም ተነግሯል። «ይህን አካባቢ እና ምሥጢራዊውን ክንውን በዓይን መመልከቱ መደመምን ይፈጥራል።» የሚሉት የፊልም ባለሙያ እንደ አንድ አስፈሪ ፍጥረት የበረዶው ክምር በዚያ ስፍራ ለዘመናት ሲኖር ማንም አንድ ቀን ውኃ ይሆናል ብሎ አስቦ እንደማያውቅ ነው የተናገሩት። የዴንማርክ ራስ ገዝ ደሴት በሆነችው ግሪንላንድ 10 ቢሊየን ቶን የበረዶ ግግር መቅለጡን ከሰሞኑ ሳይንቲስቶች ይፋ አድርገዋል። ግሪንላንድ በአርክቲክ እና አትላንቲክ ባሕር መካከል የምትገኘው ግሪንላንድ ደሴት በታሪኳ 22 ዲግሪ ሴልሽየስ የሙቀት መጠን በሐምሌ ወር ውስጥ እንደተመዘገበባት የዴንማርክ ሜትሪዮሎጂ ተቋም አመልክቷል።

ምስል Getty Images/M. Tama

 ባልተለመደ መልኩ ለወራት የዘለቀው ከፍተኛ የአየር ሙቀት ስጋት የፈጠረባቸው ወገኖች ከየአቅጣጫው ተገቢው ርምጃ እና ጥንቃቄ መወሰድ አለበት እያሉ ነው። ከእነዚህም አንዱ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተረሽ ናቸው። ጉተረሽ ባለፈው ሐምሌ ወር አውሮጳን ያስጨነቀው የሙቀት ማዕበል የበረዶ ግግሩን ለመቅለጥ ያበቃ እና አሳሳቢ ስጋት ያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል።

«ባለፈው ወር አውሮጳ ላይ ተፅዕኖውን ያሳረፈው የሙቀት ማዕበል አሁን በአርክቲክ እና በግሪንላንድ የሙቀት መጠኑ ከ10 እስከ 1,5 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ እንዲል አድርጓል። የአርክቲክ ባሕር ላይ የሚገኘው በረዶ እጅግ ቀንሶ የሚገኝበት ጊዜ በታሪክ ካለ አሁን ነው።»

በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በተለይም ባለፉት ሳምንታት እና ወራት በአውሮጳ እና በአንዳንድ አካባቢዎች የታየው ከፍተኛ ሙቀት የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታ የሚያሳስባቸው የዘርፉ ተመራማሪዎች ሲፈራ የነበረው የአየር ንብረት ለውጥ እውን የመሆኑ መገለጫ መሆኑን እየተናገሩ ነው።  በካናዳ ካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ የሚያተኩረዉ ዘርፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት እና የዘርፉ ተመራማሪ ዶክተር ጌታቸዉ አሰፋ ይህን የሚጋሩ ይመስላል።

በአውሮጳ የተመዘገበው የሙቀት ማዕበል ማሳያ

አሁን የሚታየው ከፍተኛ የሙቀት መጨመርም ሆነ እሱን ተከትለው የሚከሰቱት የአየር ጠባይ ለውጦች ወትሮም ማስጠንቀቂያ ሲቀርብባቸው የነበሩ እና ሰው ሠራሽ መሆኑ መሆናቸው እንደሚታወቅም ዶክተር ጌታቸው አክለው ገልጸዋል። የአየር ንብረት ለውጥን እውንነት እያመላከቱ የመጡትን የተለያዩ መገለጫዎች ለማስተካከል ከዚህ ቀደም ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን ሙቀት አማቂ ጋዞች ለመቀነስ ቃል የገቡ ሃገራት ያሰቡትን ተግባራዊ ቢያደርጉ እንኳን ጊዜ ይፈጃል ባይናቸው ባለሙያው።

የአየር ንብረት መዛባት ወጥ እንዳልሆነ ነው ዶክተር ጌታቸው የሚያመለክቱት። በአንዱ አካባቢ ከፍተኛ ሙቀት ቢኖር ሌላ አካባቢ ከባድ ቅዝቃዜ፤ በሌላው ደግሞ ድርቅ እያለ ይለዋወጣል። አልፎ ተርፎም በሞገድ እና ማዕበል የታጀበ የጎርፍ መጥለቅለቅም ሌላው መገለጫው ነው።

በነገራችን ላይ አድማጮች በጀርመን እና አቅራቢያዋ የሚገኙ የአውሮጳ ሃገራትን አስጨንቆ የሰነበተው የሙቀት ማዕበል፤ በቀጣይ ሳምንታት ምን ደግሶ እንደሁ ባይታወቅም በዚህ ሳምንት በመጠኑ ሰከን ያለ መስሏል። ሙቀቱ መሬቱን በማድረቁ ለምለሙ የጀርመን ገበሬዎች ማሳ ምን ይታጨድበት ይሆን የሚለው ሀገሬውን ማሳሰቡ አልቀረም። እንዲያ ያለው የአየር ጠባይ ለውጥ ምናልባት አልኒኞ እና ላኒኛ ከሚባሉት ክስተቶች ጋር ግንኙነት ለጊዜው የለውም።

ምስል Getty Images/D. Angerer

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ የአየር ንብረት ለውጥ እውንነት እየተገለጠ መምጣቱ ያስከተለባቸውን ስጋት ባለፈው ሳምንት ሲገልፁ፣ ዓለም አጣዳፊ ርምጃ ለሕልውናው ሲል መውሰድ እንዳለበት እንዲህ ነበር ያሳሰቡት።

«የማይቀለበት የመሰለውን የአየር ንብረት መዛባት የመከላከሉ ሩጫ ለሕልውናችን እና ለሕይወታችን ስንል የምናደርገው ነው። ይህን ሩቻ ደግሞ ማሸነፍ እንችላለን፤ ማሸነፍም ይኖርብናል።»

ቆፈን ከሚያስይዘው የክረምት ወራት ተላቀው የሙቀት ማዕበል በተከታተለባቸው ሃገራት የእሳት አደጋው እና ድርቁ ከሚያደርሰው ጊዜያዊ ጉዳት ባለፈ ብዙ አነጋጋሪ ስጋቶችን መጋረጡን ጥናቶች እያመለከቱ ነው። ፖለቲከኞቹ ዛሬም ሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳው በኤኮኖሚያቸው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ኪሳራ በማስላት ተጠምደዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW