የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ
ዓርብ፣ የካቲት 6 2012
«የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ» ተብሎ የሚጠራዉ ዓመታዊ ስብሰባ ደቡባዊ ጀርመን ሙኒክ ዉስጥ ዛሬ ተጀመረ። በዘንድሮው ጉባኤ ላይ የፈረንሳዩን ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ እና የካናዳዉን ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶውን ጨምሮ የ35 ሐገራት ርዕሳነ ብሔራትና መራሒያነ መንግሥታት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ስለ ዓለም ሰላምና ፀጥታ ለሦስት ቀን በሚመክረዉ ጉባኤ የዩናይትድ ስቴትስ፤ የኢራንና የቻይና መንግሥታት በየውጪ ጉዳይ ሚንስትሮቻቸው ይወከላሉ። ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና ካስተዳደራቸዉ ጋር የሚወዛገቡት የዴሞክራቲክ ፓርቲዋ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲም የጉባኤዉ ተካፋይ ናቸው። የጉባኤው አዘጋጅ የበላይ ኃላፊ ቮልፍጋንግ ኢሺንገር እንዳሉት መንግሥታት ዓለምን የሚያብጡ ግጭት፣ ጦርነትና ውዝግቦችን ለመፍታት በጋራ አለመጣራቸው የዓለምን ሰላም ክፉኛ እያወከው ነው። አውሮጶች የሊቢያን የመሳሰሉ ጦርነቶችን ለማስወገድ እንዳዲስ የጀመሩት ጥረት መጠናከር አለበት ባይም ናቸው።«በጣም አስፈላጊው ፖለቲካዊ ጉዳይ እኛ ይሕን የምናደርገዉ ዶናልድ ትራምፕን ለማስደሰት አይደለም። ካደረግነው የምናደርገው የድንበሮቻችን፣ የሕዝባችንን እና የልጆቻችንን ሰላምና ደሕንነት ለማስከበር ነው። ሥለዚሕ ማንም እኛ ላይ ግፊት ሊያደርግ አይገባም። ከጥረቱ ሁሉ ጀርባ ያለው ይኸው ነው።»
እስከ መጪው እሁድ ድረስ ባየሪሸር ሆፍ በተባለዉ ግዙፍ ሆቴል ውስጥ የሚሰበሰቡትን ባለሥልጣናት ደሕንነት ለመጠበቅ 3 ሺሕ 900 ፖሊስ ተመድቧል። የመንግሥታትን መርሕና እርምጃ የሚቃወሙ ወገኖች በሆቴሉ እካባቢ ለመሰለፍ እየተዘጋጁ ነው።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ