የሙአመር ኧል ጋዳፊ ቀብር እና የደጋፊዎቻቸው አስተያየት
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14 2004ጋዳፊ ቢዘገይ በሀያ አራት ሰዓት ውስጥ መቀበር ሲገባቸው ይህን ያህል ጊዜ ሳይቀበሩ መቆየታቸው የእሥልምናን ደንብ ጥሰዋል። የሽግግሩ ብሔራዊ ምክር ቤት ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ኢብራሂም ቤይት አል ማል የጋዳፊ እና አብረዋቸው የሞቱት ልጃቸው እና የመከላከያ ሚንስትራቸው ቀብር ዛሬ ሊነጋጋ ሲል መፈጸሙን አረጋግጠዋል።
«ቀብሩን የሚያስፈፅም አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞዋል። ይኸው ኮሚቴ በፀጥታ ጥበቃ ምክንያት ሲባል ቀብሩን በአንድ ባልታወቀ ቦታ አስፈጽሞዋል። »
ከግብዓት መሬቱ በፊት ሦስት ሼኮች ለማቾቹ ፀሎት እንዳደረጉላቸው ቤይት አል ማል አክለው አስረድተዋል።
ምዕራቡ ዓለም የጋዳፊን ህልፈተ ሕይወት እንደ ትልቅ ድል ቢመለከተውም፡ ሞታቸው በተለይ የብዙ የአፍሪቃ ሀገሮች ሕዝቦችን ዘንድ አሳዝኖዋል። የሙአመር ኧል ጋዳፊ መንግሥት ባንዳንድ ማሊን በመሳሰሉ ድሆች አፍሪቃውያት ሀገሮች እስከ አንድ መቶ ሀምሣ ቢልየን የሚቆጠር ዶላር አፍስሶዋል። የዜና ምንጮች እንደሚሉት፣ ብዙ አፍሪቃውያን ግን በጋዳፊ ርዳታ ወደተሰሩ መስጊዶች በመሄድ ጸረ ኢምፔርያሊስት እና ለጋሽ የሚሉዋቸው ጋዳፊ በመሞታቸው የተሰማቸውን ሐዘን እየገለጹ ነው። በዩጋንዳ መዲና ካምፓላ ትምህርት ቤት፡ አሠላሣ ሺህ ሰው የሚይዝ መስጊድ፡ ከሞባይል ስልክ ኩባንያዎች እስከ ብስኩት ፋብሪካዎች አሰርተዋል። የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን ኔቶ የጋዳፊ ጦር በሲቭሉ ሕዝብ ላይ ወሰደው ያለውን የኃይል ርምጃ ለማብቃት ሲል በጋዳፊ አንፃር ያካሄደውን ያየር ጥቃት እአአ በ 2002 ዓም ምሥረታው ላይ ጋዳፊ የረዱት የአፍሪቃ ህብረት የአፍሪቃ ህብረት አውግዞታል። የኔቶን ጥቃት በጥብቅ የተቃወሙት የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ጋዳፊ ተይዘው ለፍርድ መቅረብ እንጂ መገደል እንዳልነበረባቸው በቅሬታ ገልጸዋል። ጋዳፊን ከሥልጣን ለማውረድ ኔቶ የተጫወተውን ሚና በአህጉሩ ብዙ የጋዳፊ ደጋፊዎች እንደ ጣልቃ ገብነት እና እንደ አዲስ ቅኝ አገዛዝ ነው የተመለከቱት። በኮንጎ ብራዛቪል መምህርት የሆኑት የሀምሣ ሁለት ዓመትዋ ምቦሳ ነፃ የሆነች አፍሪቃን ማየት አይፈልጉም ያሉዋቸው ምዕራባውያን መንግሥታት አንድ ለሆነች ጠንካራ አፍሪቃ ምሥረታ የሚታገሉትን ሁሉ ለመግደል ወደ ኋላ ብለው አያውቁም በማለት ጋዳፊ በደጋፊዎቻቸ ዘንድ ሁሌ እንደ ሠማዕት እንደሚታዩ ገልጸዋል።
ሀያስያን ጋዳፊ ባደረጉት ርዳታ በአፍሪቃ ብዙ ደጋፊ እንዳተረፉ ቢያስታውሱም፡ በአህጉሩ በጭካኔአቸው የሚፈሩ አንዳንድ ዓማፅያን መሪዎችን እና እጅግ የተጠሉትን የዩጋንዳ አምባገነን መሪ ኢዲ አሚንን የመሳሰሉ አምባገነኖችን በመርዳታቸው ብዙ ወቀሳ ተፈራርቆባቸው እንደነበርም ገልጸዋል። እንደሚታወሰው፡ ጋዳፊ በመጨረሻዎቹ የሥልጣን ዘመናቸው ለመርዳት ስድስት መቶ ወታደሮችን ወደ ዩጋንዳ ልከዋል፤ በቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር ይረዱ የነበሩ ሕፃናትን በውትድርና ይመለምሉና ሰለባዎቻቸውንም እጅና እግር ይቆርጡ የነበሩትን የሲየራ ልዮን ዓማፅያንን በገንዘብ በረዱበት ድርጊት ላካባቢው አለመረጋጋት ድርሻ እንዳበረከቱ ነው የሚናገሩት።
ጋዳፊ በዛሬው ቀብራቸው የመጨረሻውን ዕረፍት ባገኙበት ባሁኑ ጊዜ ልጃቸው ሰይፍ አል ኢዝላም ሊቢያን፡ ኒዠርን እና አልጀሪያን በሚያዋስነው የሶስትዮሽ ማዕዘናዊ ድንበር ወዳለው የጋት አካባቢ መሸሻቸው ተገልጾዋል።
አርያም ተክሌ
ተክሌ የኋላ