1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 10 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ ሚያዝያ 10 2014

እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ አዳጊ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን መንገዳቸው እያመቻቹ ነው። ብርቱ ፍልሚያ በታየበት የኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ የእግር ኳስ ግጥሚያ ሊቨርፑል ዋነኛ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲን ከመንገድ አስቀርቶታል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። ሙሉ የስፖርት ዘገባው ከታች ይገኛል።

Champions League - Quarter Final - Second Leg - Liverpool v Benfica
ምስል Jason Cairnduff/Action Images via Reuters

በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ 3 ግጥሚያዎች ይቀራቸዋል

This browser does not support the audio element.

እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ አዳጊ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን መንገዳቸው እያመቻቹ ነው። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ታላቅ የሚባል ድል አስመዝግበው ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል። ብርቱ ፍልሚያ በታየበት የኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ የእግር ኳስ ግጥሚያ ሊቨርፑል ዋነኛ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲን ከመንገድ አስቀርቶታል። በፍጻሜው ቸልሲን ይገጥማል። ሊቨርፑል ዘንድሮ አራት የተለያዩ ዋንጫዎችን ለመሰብሰብ ግስጋሴውን ተያይዞታል። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም ለግማሽ ፍጻሜ ደርሷል።  በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቶትንሀም ነጥብ ሲጥል ማንቸስተር ዩናይትድ ድል ቀንቶታል። አርሰናል ሽንፈት ገጥሞታል። ከሻምፒዮንስሊግ የተሰናበተው ባየር ሙይንሽን በጀርመን ቡንደስሊጋ ግን አሁንም በድል ጎዳና እየገሰገሰ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቮልፍስቡርግን አስደንጋጭ በሆነ የግብ ልዩነት ድል አድርጎ ባየርን ሙይንሽንን በደረጃ ሰንጠረዡ እየተከተለ ነው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። 

እግር ኳስ

ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ያደረገውን የመጀመሪያ ግጥሚያ በድል ያጠናቀቀው እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ አዳጊ ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከሁለት ሳምንት በኋላ የመልስ ጨዋታውን ያከናውናል። ደቡብ አፍሪቃን ዐርብ እለት በሜዳው ጆሐንስበርግ ከተማ ውስጥ 3 ለ0 ድባቅ የመታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቅዳሜ ማምሻውን አዲስ አበባ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ዐርብ ዕለት ቢድቬስት ስታዲየም ውስጥ በነበረው ግጥሚያ ለኢትዮጵያ ቀዳሚውን ግብ ያስቆጠረችው እየሩስ ወንድሙ ናት። ከዚያም ደቡብ አፍሪቃዊቷ ንታንዶ ፋላ የራሳቸው ግብ ላይ በስኅተት አስቆጥራለች። ሦስተኛው ግብ ለኢትዮጵያ የተገኘው በቁምነገር ካሣ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪቃን በሜዳዋ 3 ለ0 አሸንፋለች። 

ምስል DW/S. Assarsson

ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር የተጋጠመችው በሁለተኛው ዙር ግጥሚያ በደርሶ መልስ ከኡጋንዳ ጋር ተጫውታ ሦስት እኩል ተለያይታ በማሸነፏ ነው። ምንም እንኳን ከአንድ ወር ግድም በፊት በተከናወነው ግጥሚያ ሁለቱ ቡድኖች አቻ ቢለያዩም ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈችው ከሜዳ ውጪ ባገባ በሚለው ሕግ ነው። አሁንም ከሜዳዋ ውጪ ተጫውታ 3 ለ0 ማሸነፏ ለመልሱ ጨዋታ ይበልጥ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ እድሉ እጅግ የሰፋ ነው።  

እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች አዳጊ ሴቶች የዓለም እግር ኳስ ግጥሚያ ከስድስት ወራት በኋላ ሕንድ ውስጥ ይከናወናል። ሕንድ ያለፈውን የ2020 የዓለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ ተፈቅዶላት የነበረ ቢሆንም፤ በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ግን የያኔው የዓለም ዋንጫ ተሰርዟል። የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ሕንድ ከማክሰኞ ጥቅምት 1 ቀን፣ 2015 ዓ.ም እስከ እሁድ ጥቅምት 20 ቀን፣ 2015ዓ.ም ድረስ ታስተናግዳለች። በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የመጀመሪያ ውድድሩን በአመርቂ ውጤት በድል ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያ በአራት ዙሮች የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በሚከናወኑበት የማጣሪያ ፉክክር ሦስተኛ ዙር ሁለተኛ ግጥሚያዋ ላይ ደርሳለች። ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪቃን በሜዳዋ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ ካሸነፈች አለያም አቻ ከወጣች በመጨረሻው ዙር ከግብጽ እn ከናጀሪያ አላፊዎች ከአንዱ ጋር ትፋለማለች።

ኤፍ ኤ ካፕ

ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ከሊቨርፑል ጋር ማንቸስተር ሲቲን በኤፍ ኤ ካፕ ፍልሚያ ድል ነስተው ለዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያ ደርሰዋል። ከዚህ ቀደም እንደተገመተው የዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑል ከኤፍ ኤ ካፕ በተጨማሪ አጠቃላይ አራት ወሳኝ ዋንጫዎችን የመሰብሰብ እድሉን እያጠናከረ ነው። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ታሪክ እንዲህ ላለ ደረጃ የደረሰ አንድም ቡድን የለም። ሊቨርፑል አራቱን ዋንጫዎች የመሰብሰብ እድሉን ለማሳካት እስከ ሻምፒዮን ሊግ ፍጻሜ ድረስ 11 ጨዋታዎችን ማከናወን ይኖርበታል።

ምስል Darren Staples/ZUMAPRESS.com/picture alliance

ዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑልን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 በአሰልጣኝነት ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ አምስት የተለያዩ ዋንጫዎችን ሰብስበዋል። እስካሁን የካራባዎ የሊግ ዋንጫ፣ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ ፕሬሚየር ሊግ፣ የዓለም ቡድኖች ዋንጫ እና የአውሮጳ ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን አሸንፈዋል። አሰልጣኙ በሊቨርፑል ቆይታቸው የቀራቸው የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ማንሳት ብቻ ነው። ለዚያም አሁን ከጫፍ ደርሰዋል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ሊካኼድ የነበረውን የማንቸስተር ሲቲ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያን ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ባደረገው እና ረዥም ዘመን ባስቆጠረው ኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ላይም ድል ቀንቷቸዋል።

141ኛው የኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ትናንት እና ከትናንት በስትያ ተከናውኖ ለዋንጫ አላፊዎቹ ሁለቱ ቡድኖች ተለይተዋል። በ4 3 3 አሰላለፍ ወደ ዌንብሌይ ስታዲየም ሜዳ የገባው ሊቨርፑል በቅድሚያ ነበር ግቦችን አከታትሎ ያስቆጠረው። 9ኛው ደቂቃ ሳይሞላ የተገኘውን የማእዘን ምት ኢብራሂም ኮናቴ በጭንቅላት ገጭቶ ለሊቨርፑል የመጀመሪያውን ግብ ከመረብ አሳርፏል። 17ኛው ደቂቃ ላይ በግብ ጠባቂ ስህተት ሊቨርፑል ሁለተኛ ግብ አግኝቷል። ግብ ጠባቂው ዛክ ስቴፋን ወደ ፊት ለፊቱ ተንደርድሮ የመጣው ሳዲዮ ማኔን አታልላለው ብሎ ጉድ ኾኗል። ሳዲዮ ማኔ መሬት ላይ ተንሸራቶ ኳሷን በመግጨት ከመረብ ቀላቅሏታል። 20 ደቂቃ ሳይሞላ ሁለት ግቦችን ለማስተናገድ የተገደደው ማንቸስተር ሲቲ የጨዋታ ውሉ ጠፍቶበት ታይቷል። ተጨዋቾቹ በተደጋጋሚ ኳሶችን ሲያመክኑ እና ጥፋት ሲሠሩ ተስተውለዋል።

ምስል Martin Rickett/empics/picture alliance

ቲያጎ ከትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ጋር ተቀባብሎ የላካትን ኳስ 44ኛው ደቂቃ ላይ ሳዲዮ ማኔ በድንቅ ሁኔታ ከመረብ አሳርፏታል። በዚያም ለራሱ ሁለተኛውን ለሊቨርፑል ደግሞ 3 ለ0 የመራበትን ግብ ማስቆጠር ችሏል።  የማንቸስተር ሲቲ ተከላካዮች ሙሉ ሐሳባቸውን ወደ ኳሷ አድርገው ባሉበት በስተቀኝ በኩል ለብቻው ኳሷን አድፍጦ ሲጠብቅ የነበረውን ሳዲዮ ማኔ ዘንግተው ብርቱ ስህተት ሠርተዋል። ሳዲዮ ማኔ በቲያጎ የተላከችለትን ኳስ መሬት ሳታርፍ አየር ላይ በቀጥታ ወደ ግቡ አክርሮ መትቶ ነው ግብ ያስቆጠረው።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሊቨርፑል 3 ለ0 እየመራ ነበር ረፍት የወጡት። 46ኛው ደቂቃ ላይ ጋብሬል ጄሱስ በድንቅ አጨዋወት ለጃክ ግሪሊሽ ያቀበለውን ኳስ ግሪሊሽ ከመረብ በማሳረፍ ማንቸስተር ሲቲን ከ3 ለ0 ወደ 3 ለ1 አሸጋግሮታል። መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው 1 ደቂቃ ላይ ቤርናርዶ ሲልቫ ሁለተኛ ግብ ለማንቸስተር ሲቲ ቢያስቆጥርም ሁሉም ነገር ዘግይቶ ነበር። እናም ሲቲ በቀያዮቹ የ3 ለ2 ሽንፈት ገጥሞት ተሰናብቷል። አሁን በተለይ የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን በእጁ ለማስገባት ሁሉንም ቀሪ ጨዋታዎች ማሸነፍ ይኖርበታል። አለዚያ በ1 ነጥብ ከስሩ አድፍጦ የሚጠብቀው ሊቨርፑል እሱንም ሊመነትፈው ይችል ይሆናል። አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላን በ10 የተለያዩ ጨዋታዎች በማሸነፍ የመጀመሪያው አሰልጣኝ ኾነዋል።

በኤፍ ኤ ካፕ ሌላ ግጥሚያ ሌላኛው ጀርመናዊ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል የፓትሪክ ቪዬራ ክሪስታል ፓላስን 2 ለ 0 ድል አድርገው ለፍጻሜ ደርሰዋል። ለቸልሲ ትናንት ሩበን ሎፉስ-ቺክ በ65ኛው እንዲሁም ማሶን ማውንት በ76ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል። ለዋንጫ ሽሚያ የፍጻሜ ፍልሚያ ሁለቱ ጀርመናዊ አሰልጣኞች ይፋጠጣሉ። የሊቨርፑሉ ዬርገን ክሎፕ ከቸልሲው ቶማስ ቱኁል።  ባለፈው የካራባዎ የሊግ ዋንጫ የፍጻሜ ፍልሚያ በመለያ ምት ቸልሲን ጉድ የሠሩት ዬርገን ክሎፕ ዳግም ድል ይቀናቸው ይሆን ወይንስ ቶማስ ቱኁል ሽንፈታቸውን ይበቀላሉ? ከሦስት ሳምንት በኋላ የፍጻሜ ፍልሚያውን ግንቦት 6 ቀን መመልከት ነው።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ትናንት ኒውካስል ዩናይትድ ሌስተር ሲቲን 2 ለ1 አሸንፏል። ማንቸስተር ሲቲ ለኤፍ ኤ ካፕ በነበረው ጨዋታ ምክንያት ከዎልቨርሀምፕተን ጋር የነበረው ቀጠሮ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። ቅዳሜ በነበሩ ጨዋታዎች ማንቸስተር ዩናይትድ ኖርዊች ሲቲን 3 ለ2 ሲያሸንፍ፤ ቶትንሀም ሆትስፐር እና አርሰናል በተመሳሳይ 1 ለ0 በብራይተን እና ሳውዝሀምፕተን ተሸንፈዋል። በተለይ በቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን የቆረጠው ቶትንሀም ሽንፈት የገጠመው ከታችኛው ዲቪዚዮን ባደገው ብራይተን መሆኑ ለደጋፊዎቹ አስደንጋጭ ነበር። ቅዳሜ ዕለት በሳውዝሀምፕተን የተሸነፈው አርሰናል ቀጣይ ጨዋታውን ቢያሸንፍ እንኳን በሰፊ የግብ ልዩነት ስለሚበለጥ የሻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻውን ቦታ ከቶትንሀም ሊረከብ አይችልም። በነጥብ ግን ሊስተካከል ይችላል።  ከነገ በስትያ የሚገጥመውም ቸልሲን ነው። ብራይተን ማንቸስተር ሲቲን ረቡዕ ማታ ይፋለማል። ነገ ማታ ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊቨርፑል ጋር ይጋጠማሉ። መሪው ማንቸስተር ሲቲ 74 ሊቨርፑል 73 ነጥብ አላቸው። ሊቨርፑል በግብ ክፍያ ይበልጣል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቸልሲ በ62 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል። አንድ ትርፍ ጨዋታ ያደረገው ቶትንሀም 57 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ዩናይትድ እና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው አርሰናል ተመሳሳይ 54 ነጥብ አላቸው፤ አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በርንሊ፣ ዋትፎርድ እና ኖርዊች ወደታችኛው ዲቪዚዮን ሊመለሱ ከታች ከ18ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ በዝቅተኛ ነጥብ ተደርድረዋል።

ቡንደስሊጋ

ከሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ በቪላሪያል የተሰናበተው መሪው ባየርን ሙይንሽን በጀርመን ቡንደስሊጋ ትናንት አርሚኒያ ቢሌፌልድን 3 ለ0 አሸንፎ ነጥቡን 72 አድርሷል። 63 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ የሚከተለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቮልፍስቡርግን አስደንጋጭ በሆነ የግብ ልዩነት 6 ለ1 የግብ ጎተራ አድርጎታል። ኧርሊንግ ኦላንድ ሁለት ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ፤ ቶም ሮተ፣ አክሰል ቪትሰል፣ ማኑዌል አካንጂ እና ኤምሬ ካን አንድ አንድ ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል። ለቮልፍስቡርግ ብቸኛዋን ግብ ሪድል ባኩ 81ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል። ባየር ሌቨርኩሰን ትናንት ለላይፕሲሽ እጅ ሰጥቷል። ባየር ሌቨርኩሰን በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በፈጣን አጨዋወት የበለጠ ወደ ግብ እየቀረበ ሙከራዎችን ሲያደርግ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን ላይፕትሲሽ እንኩንኩን ቀይሮ መግባቱ በማጥቃቱ በኩል ገኖ ዕንዲታይ አድርጎታል። ኮሶኑ መሬት ላይ አዳልጦት በሠራው ብቸኛ ስህተት ባየር ሌቨርኩሰን ሽንፈት አስተናግዷል። ኮሶኑ ያመለጠችውን ኳስ እንኩንኩ 69ኛው ደቂቃ ላይ ለዶሚኒክ ሶቦስላይ አመቻችቶ ያቀብላል፤ ዶሚኒክም በሦስት ተከላካዮች መሀል አሳልፎ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፏታል። በዚህም ላይፕሲሽ ባየር ሌቨርኩሰንን 1 ለ0 አሸንፎ ነጥቡን 54 በማድረስ የሦስተኛ ደረጃውን ከባየርን ሌቨርኩሰን ተረክቧል። ሌቨርኩሰን በ52 ነጥቡ ተወስኖ ወደ 4ኛ ደረጃ ተንሸራቷል።  ፍራይቡርግ እና ትናንት ፍራንክፉርትን 2 ለ0 የሸኘው ዑኒዮን ቤርሊን 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ቅዳሜ እለት ቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅን 3 ለ1 ኩም ያደረገው ኮሎኝ ከዑኒዮን ቤርሊን በአንድ ነጥብ ልዩነት የአውሮጳ ሊግ ምድብ ውስጥ ለመግባት 7ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሮ ወደ ላይ እያማተረ ነው። ሽቱትጋርት፣ ቢሌፌልድ እና ግሮይተር ፊዪርትስ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ።

ምስል Roger Petzsche/Picture Point LE/IMAGO

አትሌቲክስ 

ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ትናንት በተከናወነው ከ2 ሰአት ከ5 ደቂቃ በታች ብርቱው የሴዑል የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሞስነት ገረመው የቦታውን ክብረ-ወሰን በማሻሻል አሸነፈ።  የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለድሉ ሞስነት 42ቱን ኪሎ ሜትር ሮጦ ለማገባደድ የፈጀበት 2:04:43 ነው። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሄርጳሳ ነጋሳ ከሞስነት ለጥቂት በስድስት ሰከንዶች ብቻ ተቀድሞ የሁለተኛነት ደረጃን ይዟል። ከሄርጳሳ ለጥቂት በ2 ሰከንዶች የተቀደመው የብራዚሉ ሯጭ ዳንኤል ፌሬራ ዶ ናሲሜንቶ የሦስተኛነትን ደረጃ አግኝቷል። ብራዚላዊው አትሌት ውድድሩን ያገባደደው 2:04:51 በመሮጥ ነው። ይህም በብራዚል አዲሱ ክብረ-ወሰን ተብሎ ተመዝግቦለታል።

ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

በሴቶች ተመሳሳይ ርቀት ፉክክር ሁለት ሯጮች የ2:18 ገደብን ተጠግተው ሩጫቸውን በማጠናቀቅ ብቃታቸውን አስመስክረዋል። በዚሁ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱቱሜ አሰፋ 2:18:12 በመሮጥ ለጥቂት የሁለተኛነት ደረጃን አግኝታለች። ሮማኒያዊቷ አትሌት ያሸነፈችው ለጥቂት በስምንት ሰከንዶች ልዩነት ብቻ ነበር።

ቅዳሜ እለት በተከናወነው የቦስተን 5 ኪሜ የጎዳና ሩጫ ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ አሜሪካዊት እና ኬንያዊት ሯጮችን አስከትላ ለድል በቅታለች። ሰንበሬ የቦታውን ሰአት በማሻሻል አንደኛ የወጣችው 14:49 በመሮጥ ነው። አሜሪካዊቷ ዌይኒ ኬላቲ ከ15 ሰከንድ በኋላ በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች። ሦስተኛ ደረጃን ያገኘችው ኬኒያዊቷ ሻሮን ሎኬዲ ውድድሯን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 15:16 ነው። በተመሳሳይ የወንዶች ፉክክር ካናዳዊው ሻርል ፊልቤር-ቲዮቦቱ አንደኛ ሲወጣ፤ የኔዘርላንዱ ሯጭ ጌኦርዲ ቤአሚሽ የሞሮኮው አትሌት ዞሃይር ታልቢን አስከትሎ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። በወንዶችም በሴቶችም ፉክክር አብዛኛው ተሳታፊዎች አሜሪካውያን ነበሩ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW