የሚያዝያ 16 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 16 2015ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ አሸንፈው ለፍጻሜ በቅተዋል ። በፕሬሚየር ሊጉ ቶትንሀም ሆትስፐር በኒውካስል ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል ። ትውልደ ኤርትራዊ ስዊድናዊው አጥቂ አሌክሳንደር ይሳቅ ብቃቱን አስመስክሯል ። አሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማንን ባልተጠበቀ ወቅት ያሰናበተው ባየርን ሙይንሽን አዲስ አሰልጣኙ ቶማስ ቱሁል ሽንፈቶችን እያስተናገደ ነው ። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ መሪነቱን ለቦሩስያ ዶርትሙንድ አስረክቧል ። በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።
አትሌቲክስ
እንግሊዝ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የለንደን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዓለሙ መገርቱ ለጥቂት በአራት ሰከንዶች ተበልጣ የሁለተኛ ደረጃ አግንታለች ። በዚሁ ውድድር ለኔዘርላንድ የምትሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሲፋን ሐሰን ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የማራቶን የሩጫ ውድድር አሸናፊ ሆናለች ። በኦሎምፒክ በ5,000 እና በ10,000 ሜትር የሩጫ ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ሲፋን በለንደን ማራቶን አሸናፊ የሆነችው 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ በመሮጥ ነው ። በዚህ ውድድር ኬንያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር ሦስተኛ ሆናለች። ያለምዘርፍ የኋላው 5ኛ፣ አልማዝ አያና 7ኛ እንዲሁም ታዱ ተሾመ 8ኛ ደረጃ ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል ።
በለንደን ማራቶን የወንዶች ፉክክር ኬኒያዊው ኬልቪን ኪፕቱም 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ25 ሰከንድ በመሮጥ አሸናፊ ሆኗል ። ያገሩ ልጅ ጄኦፍሪ ካምዎሮር እና ኢትዮጵያዊው ታምራት ቶላ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። ልዑል ገብረሥላሴ 4ኛ፤ ሰይፉ ቱራ 5ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል ። በለንደን ማራቶን ለመጨረሻ ጊዜ የተወዳደረው ትውልደ ሶማሊያ የብሪታኒያው አትሌት ሞ ፋራህ ውድድሩን 9ኛ በመውጣት አጠናቋል ።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ከሳውዝሀምፕተን ጋር ሦስት እኩል መለያየቱ የዋንጫ ግስጋሴውን ገትቶታል ። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ሲቲ በአርሰናል የሚበለጠው በአምስት ነጥቦች ብቻ ነው ። ማንቸስተር ሲቲ ቀሪ ሁለቱን ጨዋታዎች ካሸነፈ ነጥቡን 76 አድርሶ አርሰናልን በአንድ ነጥብ በመብለጥ የመሪነቱን ስፍራ ይረከባል ። ያም በመሆኑ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ከነገ በስትያ የሚያደርጉት ግጥሚያ የሞት ሽረት ነው ። ኖቲንግሀም ፎረስትን 3 ለ2 ያሸነፈው ሊቨርፑልም ለአውሮጳ ሊግ የማለፍ እድሉን ከፍ አድርጓል ። ረቡዕ በሚኖረው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ሊቨርፑል ካሸነፈ ነጥቡን እንደ ቶትንሀም 53 አድርሶ ግን ደግሞ በግብ ክፍያ በልጦ የአውሮጳ ሊግ አምስተኛ ደረጃ ቦታውን ይረከባል ። ያም በመሆኑ የሊቨርፑል እና ዌስትሀም ዩናይትድ የረቡዕ ግጥሚያም እጅግ የሚጠበቅ ነው ።
ዌስትሀም ዩናይትድ ትናንት ቦርመስን 4 ለ0 አንኮታኩቷል ። ቶትንሀም ሆትስፐር በኒውካስል ዩናይትድ የ6 ለ1 ብርቱ ሽንፈት ደርሶበታል ። አምስቱ ግቦች ጨዋታው በተጀመረ 21 ደቂቃዎች ውስጥ መቆጠራቸው ለቶትንሀም እጅግ አስደንጋጭ ነበር ። ትውልደ ኤርትራዊ ስዊድናዊው አጥቂ አሌክሳንደር ይሳቅ በ19ኛው እና 21ኛው ደቂቃ ላይ በተከታታይ አስቆጥሯል ። ከኤርትራ ወደ ስዊድን ከተሰደዱ ቤተሰቦች የተወለደው አሌክሳንደር ይሳቅ በእንግሊዝ ብቃቱን እዕያሳየ ነው ። ከስፔኑ ሪያል ሶሴዳድ ለእንግሊዙ ኒውካስትል ዩናይትድ ባለፈው ዓመት የፈረመው በ70 ሚሊዮን ዩሮ ነበር ። ጄኮብ መርፊ ቀዳሚዋን እና ተከታዩዋን ግብ በ2ኛው እና 9ኛው ደቂቃ ላይ ለኒውካስል ከመረብ ሲያሳርፍ፤ ካሉም ዊልሰን 67ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ አሳርገዋል ። ለቶትንሀም ብቸኛውን ግብ 49ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሐሪ ኬን ነው ።
አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ብርቱ ቀውስ ውስጥ የገባው ቸልሲ አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድን ሊተኩ መሆኑ ተዘገበ ። ቀደም ሲል ከባየርን ሙይንሽን በድንገት የተሰናበቱት ወጣቱ አሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማን ቸልሲን ሊያሰለጥኑ ነው እየተባለ ነበር ። አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ቸልሲን እስከ ዘንድሮ የጨዋታ ዘመን መጠናቀቂያ ድረስ ያሰለጥናሉ ተብሎ ነበር ።
ኤፍ ኤ ካፕ
በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ማንቸስተር ሲቲ ለፍጻሜ ደርሰዋል ። ማንቸስተር ዩናይትድ ለፍጻሜ የበቃው ትናንት ከብራይተን ጋር ያደረገው ጨዋታ መደበኛው ጊዜ ያለምንም ግብ ተጠናቆ በፍጹም ቅጣት ምት መለያ በማሸነፍ ነው ። በመለያ ምቱ ማንቸስተር ዩናይትድ ብራይተንን በጠበበ ልዩነት 7 ለ6 አሸንፏል ። ማንቸስተር ዩናይትድን በፍጻሜው የሚገጥመው ማንቸስተር ሲቲ ነው ። በአንጻሩ ማንቸስተር ሲቲ ተጋጣሚው ሼፊልድ ዩናይትድን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ0 ባሸነፈበት ግጥሚያ በጨዋታ ፍጹም ብልጫ ዐሳይቷል ።
እድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች የጀርመን ቡንደስሊጋ የዋንጫ ግጥሚያ ማይንትስ ቦሩስያ ዶርትሙንድን ትናንት 4 ለ2 አሸንፎ ዋንጫ ወስዷል ።
በሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ የጀመርን ቮልፍስቡርግ ቡድን ከእንግሊዝ አርሰናል ጋር ትናንት ፎልክስ ቫገን አሬና ስታዲየም ውስጥ ባለቀ ሰአት ሁለት እኩል ተለያይቷል ። የዐርብ ሳምንት የመልስ ጨዋታ እንግሊዝ ኤሚሬት ስታዲየም ውስጥ ይከናወናል ። በሌላ ግጥሚያ ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ ያቀናው ባርሴሎና የቸልሲ ቡድንን 1 ለ0 አሸንፏል ። ሐሙስ የመልስ ግጥሚያ ይኖራል ።
ቡንደስ ሊጋ
ላይፕትሲሽ ትናንት በባየርን ሌቨርኩሰን የ2 ለ0 ሽንፈት ደርሶበታል ። ፍራይቡርግ ሻልከን 4 ለ0 ኩም አድርጓል ። ሻልከ 24 ነጥብ ይዞ ወራጅ ቀጣናው 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ከስሩ በ2 ነጥብ ዝቅ ያለው ሔርታ ቤርሊን ብቻ ሰፍሯል ።
በማይንትስ ቅዳሜ ዕለት የ3 ለ1 ሽንፈት ያስተናገደው ባየርን ሙይንሽን በአንድ ነጥብ ተበልጦ መሪነቱን ለቦሩስያ ዶርትሙንድ አስረክቧል ። በዕለቱ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 4 ለ0 ያደባየው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቡንደስሊጋውን በ60 ነጥብ ይመራል ። አውግስቡርግ ከሽቱትጋርት ጋር አንድ እኩል ሲለያይ፤ ቮልፍስቡርግ ቦሁምን 5 ለ1 አሸንፏል ። ኮሎኝ ሆፈንሀይምን 3 ለ1 ረትቷል ።
አድማጮች አሁን በቀሩን ደቂቃዎች ደግሞ ዶይቸ ቬለ አካዳሚ ለአፍሪቃውያን የስፖርት ጋዜጠኞች ለሁለት ዓመት ግድም ስለሰጠው ስልጠና የምንለው ይኖረናል ። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪቃ ለተለያዩ ሰባት ወጣት የስፖርት ጋዜጠኞች ስልጠናውን የሰጠው በርሊን ከተማ የሚገኘው የዶይቸ ቬለ አካዳሚ ነው ። ሁለቱም ጋዜጠኞች ከስልጠናው ልምድ መቅሰማቸውን ገልጠዋል ። ጋዜጠኛ ምሕረት ተስፋዬ ላለፉት ሁለት ዓመታት ግድም ከዶይቸ ቬለ አካዳሚ ያገኙት ስልጠና የተሰጠው ልምድ ባካበቱ አሰልጣኞች ነው ብላለች ።
ጋዜዘኛ እዩኤል ዘሪሁን በስፖርት ጋዜጠኝነት ስልጠና ሲያገኝ የዶይቸ ቬለ የመጀመሪያው ነው ። ሥልጠናው ለሞያው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተለት አብራርቷል ። ሁለቱ ጋዜጠኞች በስልጠናው ማገባደጃ ቦን ከተማ ጀርመን እንዲመጡ እድሉ ቢሰጣቸውም በቪዛ ችግር ግን በአካል ጀርመን መገኘት አልቻሉም ። በአካል ጀርመን ከተገኙት የኬንያ እና የደቡብ አፍሪቃ አራት ጋዜጠኞች ጋር ግን በኢንተርኔት ጉብኝት አድርገዋል ።
መሰል ስልጠና አፍሪቃውያን የስፖርት ጋዜጠኞች ልምድ እንዲቀስሙ ከማስቻሉም ባሻገር በአውሮጳ የሚገኙ ቡድኖች አፍሪቃ ውስጥ ለሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እገዛም ይኖረዋል ። የጀርመኑ ሆፈንሀይም ቡድን በአፍሪቃ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል ። ጋዜጠኛ ምሕረት በስልጠና ያገኘችውን አጋጣሚ በመጠቀም ቡድኑ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ጠይቃለች ። ምን ምላሽ ተሰጣት?
ጋዜጠኞቹ ሁለት ዓመታት ግድም በዶይቸ ቬለ በኩል በዲጂታል ያገኙት ስልጠና ማጠናቀቂያው ጀርመን ውስጥ ቢሆንም በቪዛ ምክንያት ግን ኢትዮጵያውያኑ ሊገኙ አልቻሉም ። ከደቡብ አፍሪቃ እና ከኬንያ የመጡ አራት ጋዜጠኞች የአማርኛ ክፍሉን ጨምሮ የዶይቸ ቬለ ማሰራጪያን እንዲጎበኙ አድርገናል ። በወቅቱ እነ እዩኤልም በአካል ባይገኙም በኢንተርኔት ግን የጉብኝቱ አካል ሆነው ነበር።
ኢትዮጵያውያኑ ወጣት የስፖርት ጋዜጠኞች ምሕረት ተስፋዬ እና እዩኤል ዘሪሁን ከዶይቸ ቬለ አካዳሚ ባገኙት ሥልጠና እና ልምድ በመታገዝ በኢትዮጵያ የስፖርት ዘርፍ ጉልኅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ተስፋ እናደርጋለን ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ