1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2016

አርሰናል የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ ተፎካካሪነቱን አጠናክሯል ። ሊቨርፑል ዳግም ነጥብ ጥሎ ዋንጫ የማግኘት እድሉን አመንምኗል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ በግስጋሴው ቀጥሏል ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም መድረክ እንደተለመደው ድል ተቀዳጅተዋል ። የዓለም ክብረወሰን ተሰብሯል፤ በሴትም በወንድም ድሉ የኢትዮጵያ ሆኗል ።

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባለድል የነበረው ሊቨርፑል ዘንድሮ በብርቱ ተንገዳግዷል
ከአምስት ዓመት በፊት የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባለድል የነበረው ሊቨርፑል ዘንድሮ በብርቱ ተንገዳግዷል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Actionplus/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

አርሰናል የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ ተፎካካሪነቱን አጠናክሯል ። ሊቨርፑል ዳግም ነጥብ ጥሎ ዋንጫ የማግኘት እድሉን አመንምኗል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ በግስጋሴው ቀጥሏል ።  ማንቸስተር ዩናይትድ የአውሮጳ ሊግ ተሳታፊነት ትልሙ ላይ ወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኘው በርንሌይ ውኃ ቸልሶበታል ። ሼፊልድ ዩናይትድ ከፕሬሚየር ሊጉ ተሰናባች መሆኑን አረጋግጧል ። ከቡንደስ ሊጋው ደግሞ ዳርምሽታድት ተሰናባች ነው ። ኮሎኝ የስንብት ብርቱ ሥጋት ተጋርጦበታል ።  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም መድረክ እንደተለመደው ድል ተቀዳጅተዋል ። በ5 ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ሲሰበር፤ቻይና ውስጥ በተደረገ የ5000 ሜትር ፉክክር ደግሞ በሴትም በወንድም ድሉ የኢትዮጵያ ሆኗል ።

አትሌቲክስ

ቻይና ሻንጋይ ውስጥ በተደረገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ5000 ሜትር በሁለቱም ፆታ አሸናፊ ሆኑ ። ቅዳሜ ዕለት በነበረው የ5000 ሜትር ርቀት ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል ። በዚህ ውድድር፦ መቅደስ ዓለምሸት (14፡36.70) በመሮጥ የ1ኛ ደረጃ አግኝታለች ። አትሌት አያል ዳኛቸው (14:36.86) 2ኛ ስትወጣ፤ ለተሰንበት ግደይ (14:37.13)3ኛ ደረጃ አግኝታለች ። 4ኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያዊት አትሌት ውብርስት አስቻለ (14:37.28) ናት።

በተመሳሳይ ርቀት የወንዶች የ5000 ሜትር ፉክክር ደግሞ፦ አትሌት ሰለሞን ባረጋ (12:55.68) የውድድሩን ክብረወሰን በመስበር ጭምር አሸናፊ ሆኗል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቢኒያም መሃሪ (12:56.37) ሁለተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ።

አትሌቶች ሲሮጡ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Charlie Neibergall/AP/picture alliance

ቅዳሜ (ሚያዝያ 19 ቀን፣2016 ዓ.ም) የአዲዳስ ኩባንያ ባዘጋጀው አዲዜሮ የ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ከ20 ዓመት በታች ውድድር ደግሞ አትሌት መዲና ኢሳ የዓለም ክብረ ወሰንን በመስበር አሸነፋለች ። አትሌትዋ የ5 ኪሎ ሜትር ርቀቱን አጠናቃ ለድል የበቃችው 14 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ በመሮጥ ነው ። በዚሁ ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መልክናት ውዱ (14:40) 2ኛ፤ እንዲሁም ፎቲየን ተስፋይ (14:41) 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቀዋል ። በወንዶች 5 ኪ.ሜ ርቀት አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ (13:00) 1ኛ እንዲሁም አዲሱ ይሁኔ (13:05) 2ኛ ደረጃን በመያዝ ተከታትለው ለድል በቅተዋል ።

እግር ኳስ

በኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ፦ ኢትዮጵያ ቡና ሀዋሳ ከተማን 2 ለ0 አሸንፎ ለፍጻሜ በቅቷል ። ወላይታ ድቻ ደግሞ ለፍጻሜ የደረሰው ኢትዮጵያ መድንን 1-0 አሸንፎ ነው ።  በዚህም መሠረት የ2016 የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚዎች፦ ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና ናቸው ። የፍጻሜ ግጥሚያው ሰኔ ወር ውስጥ እንደሚካሄድ ተገልጧል ።

የአዲስ አበባ ስታዲየም ከርቀት ሲታይ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Omna Tadel

ፕሬሚየር ሊግ

ዘንድሮ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳሉ ተብለው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ሦስት ቡድኖች መካከል አንዱ እድሉን አምክኗል ።  ሁለቱ አንገት ለአንገት ተናንቀዋል ። ባለፉት አምስት የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች የሊቨርፑልን ዋንጫ የማግኘት እድል ከ0 በታች አውርደውታል ። ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች በተከታታይ እና በአስተማማኝ ሁኔታ ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ ዋንጫውን የማንሳት እድሉ ከፍተኛ ነው ። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ የተሸነፈው አርሰናልም ቢሆን በብርቱ ተፎካካሪነቱ ገፍቶበታል ። እንደ ማንቸስተር ሲቲ ባይሆንም ዋንጫ የማንሳት እድሉ ግን አለው ። የሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

እስካሁን በተደረጉ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 35 ግጥሚያዎች አርሰናል 80 ነጥብ ሰብስቦ በደረጃ ሰንጠረዡ ቁንጮ ላይ ተቀምጧል ። አርሰናል ትናንት 3 ለ 2 ያሸነፈው በቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ጫፍ የደረሰው ቶትንሀም ሆትስፐርን በገዛ ሜዳው መሆኑ ብርታቱን ያሳያል ። ቶትንሀም ሆትስፐር ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ60 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።

ከዎልቭስ ጋ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ በ79 ነጥብ ከአርሰናል በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።  ኖቲንግሀም ፎረስትን ትናንት 2 ለ0 ድል ካደረገው ማንቸስተር ሲቲ የዘንድሮ አቋም አንጻር ተስተካካይ ጨዋታውን አሸንፎ የደረጃ ሰንጠረዥ መሪነቱን መረከቡ ብዙም አያጠራጥርም ። የኳስ ነገር ግን ዐይታወቅም ።

46 ነጥብ ሰብስቦ 11ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ዎልቭስ ከእንግዲህ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎቹን ቢያሸንፍ እንኳ ለቡድኑ የአውሮጳ ሊግ ጠርዝ ጋ ከመጠጋት ውጪ የሚፈይድለት ነገር የለም ። ማንቸስተር ሲቲን ማሸነፍ ግን ለዎልቭስ ከምንም በላይ ታላቅ ድል አድርጎ ስለሚቆጥረው የቅዳሜውን ጨዋታ አጓጊ ያደርገዋል ።

የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና የፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞ በሲግናል ኢዱና ፓርክ ይጋጠማሉ ምስል Ralf Ibing/firo Sportphoto/augenklick/picture alliance

ረቡዕ ዕለት በኤቨርተን 2 ለ0 ጉድ ሆኖ፤ ቅዳሜ ዕለት ከዌስትሀም ዩናይትድ ጋ ሁለት እኩል የተለያየው ሊቨርፑል በ75 ነጥብ ተወስኖ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሊቨርፑል በሦስት ቀናት ልዩነት በእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ያጣው 5 ነጥብ ዓመቱን ሙሉ የለፋበትን መና ያስቀረ ነው ።

ዋና ተሰላፊ የነበረው ግብጻዊው አጥቂ ሞሐመድ ሳላኅ በቅዳሜው ግጥሚያ እስከ 79ኛው ደቂቃ ድረስ ተቀያሪ ወንበር ላይ በመቆየቱ ከጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ጋ ቅራኔ አጭሯል ። ጨዋታው በአቻ እንደተጠናቀ ሞሐመድ ሳላኅ ለመገናኛ አውታር፦ «ብናገር እሳት ነው የሚነሳው» ሲልንዴቱን ገልጧል ። ጋዜጠኛው፦ «እሳት?» ብሎ ሲጠይቀውም «አዎ፤ እሳት» ሲል መልስ ሰጥቷል ። ይህ ንግግሩ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭቷል ። ከዘንድሮ ውድድር ዘመን በኋላ ሊቨርፑልን ትተው የሚሄዱት አሰልጣኙም፦ «ስለዚያ ጉዳይ መልበሻ ክፍል ውስጥ እንነጋገራለን» ሲሉ በጉዳዩ ማምረራቸውን ዐሳውቀዋል ።

ቅዳሜ ዕለት በገዛ ሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ከበርንሌይ ጋ አንድ እኩል የተለያየው ማንቸስተር ዩናይትድ 54 ነጥብ ይዞ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሉቶን ታወን እና በርንሌይ በ25 እና 24 ነጥብ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ። መሰናበቱን ከወዲሁ ያረጋገጠው ሼፊልድ ዩናይትድ በ16 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ላይ ሰፍሮ ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ ይጠብቃል ። 

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግና የአውሮጳ ሊግ ፍልሚያዎች

የሻምፒዮንስ ሊግ

የጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን በሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የደርሶ መልስ መጀመሪያ ጨዋታውን ነገ በአሊያንትስ አሬና ስታዲየም የስፔኑ ሪያል ማድሪድን ያስተናግዳል ።

የባዬርን ሙይንሽን አሰልጣን ቶማስ ቱኁል ቡድናቸው ከፍራንክፉርት ጋ ተጋጥሞ 2 ለ1 ባሸነፈበት ግጥሚያምስል Frank Hoermann/SVEN SIMON/picture alliance

ዘንድሮ የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዋንጫን ባዬርን ሌቨርኩሰን አስቀድሞ መውሰዱን በማረጋገጡ  ባዬርን ሙይንሽን አንድ የቀረው የዋንጫ ተስፋ የሻምፒዮንስ ሊግ ብቻ ነው ። በግማሽ ፍጻሜው የደረሰው ሪያል ማድሪድ ደግሞ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለ14 ጊዜያት ዋንጫ ማንሳት የቻለ ብርቱ ተፎካካሪ ነው ። ያም ብቻ አይደለም በስፔን ላሊጋ የደረጃ ሰንጠረዡን በ13 ነጥብ የሚመራው ሪያል ማድሪድ የላሊጋውንም ዋንጫ ለማንሳት ጫፍ የደረሰ ቡድን ነው ። ከዋነኛ ተፎካካሪው ባርሴሎናም በ14 ነጥብ ርቆ ይገኛል ።

በእርግጥ በላሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ ሦስተኛ ላይ የሚገኘው ባርሴሎና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 70 ነጥብ አለው ። በአንጻሩ ባዬርን ሙይንሽን የዋንጫ ባለድሉ በታወቀበት ቡንደስሊጋ 69 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በዚህ ነጥቡም ከመሪው እና ዘንድሮ የቡንደስሊጋ የዋንጫ ባለድሉ ባዬር ሌቨርኩሰን በ12 ነጥብ ይበለጣል ። ነገ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት የባዬርን ሙይንሽን እና የሪያል ማድሪድ የመልስ ጨዋታቸው የሚከናወነው በሳምንቱ ረቡዕ ነው ።

የፊታችን ረቡዕ ሌለኞቹ የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና የፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞ በሲግናል ኢዱና ፓርክ ይጋጠማሉ ። የከነገ ወዲያውን የሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ግጥሚያ የሚያስተናግደው የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቡንደስሊጋው 57 ነጥብ ይዞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ቅዳሜ ዕለት ከለ ሐርብ ጋ ሦስት እኩል የተለያየው ፓሪ ሳንጃርሞ በ70 ነጥቡ የሊጉ ዋንጫን ከወዲሁ መውሰዱን ያረጋገጠ ብርቱ ቡድን ነው ።

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጋጣሚ ቡድኖችን ለመለየት ጣ ሲወጣ ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Martial Trezzini/KEYSTONE/dpa/picture alliance

የአውሮጳ ሊግ

በአውሮጳ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የደርሶ መልስ ግጥሚያ የመጀመሪያ ጨዋታዎች የፊታችን ሐሙስ ይከናወናሉ ። የፈረንሳዩ ማርሴ የጣሊያኑ አታላንታን ያስተናግዳል ። አታላንታ ለግማሽ ፍጻሜ ሲደርስ በታሪኩ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ። የመልስ ጨዋታዎች በሳምንቱ ይከናወኑና የዋንጫ ተፋላሚዎች ይለያሉ ። ሐሙስ ማታ በተመሳሳይ ሰአት የጣሊያኑ ሮማ የጀርመኑን ቡንደ ሲላ ዋንጫን የውድድር ዘመኑ ሳይጠናቀቅ መውሰዱን ካረጋገጠው ባዬርን ሌቨርኩሰን ጋ ይጋጠማል ። ባዬርን ሌቨርኩሰን ለግማሽ ፍጻሜ ሲደርስ ለአምስተኛ ጊዜ ነው ። በአንጻሩ ሮማ በአውሮጳ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ውድድር ሲበቃ ይህ አራተኛ  ሆኖ ተመዝግቦለታል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW