1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 23 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 23 2015

ኢትዮጵያውያን አዳጊ እና ወጣት አትሌቶች በዛምቢያ አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ ነው ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ቶትንሀምን ጉድ አድርጎታል ። 1 ተስተካካይ ጨዋታ ቢቀረውም ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል የመሪነቱን ሥፍራ ተረክቧል ። በሴቶች የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ለፍጻሜ ግጥሚያ ለመድረስ አርሰናል እና ቮልፍስቡርግ ለንደን ውስጥ ይጋጠማሉ።

Fußball 1. Bundesliga 30. Spieltag | FC Bayern München - Hertha BSC Berlin
ምስል Mladen Lackovic/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያውያን አዳጊ እና ወጣት አትሌቶች በዛምቢያ አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ ነው ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ቶትንሀምን ጉድ አድርጎታል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቢቀረውም ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል የመሪነቱን ሥፍራ ተረክቧል ።  በጀርመን ቡንደስሊጋ ሔርታ ቤርሊንን በስቃይ ያሸነፈው ባዬርን ሙይንሽንም ዳግም የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል ። በሴቶች የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ለፍጻሜ ግጥሚያ ለመድረስ አርሰናል እና ቮልፍስቡርግ ለንደን ውስጥ ይጋጠማሉ። ከአምሳ ሺህ በላይ ታዳሚዎች ስታዲየም ገብተው የመልስ ጨዋታውን ይከታተላሉ ተብሏል ። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪው ሠርጂዮ ፔሬዝ ድል ቀንቶታል።

አትሌቲክስ

የአፍሪቃ እድሜያቸው ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ውድድሮች በዛምቢያ ንዶላ መካሄዳቸውን ቀጥለዋል ። እስካሁን በተካሄዱ ፉክክሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች በተለያዩ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ነው ። ትናንት ከነበሩ ውድድሮች ከ20 ዓመት በታች የ1500 ሜትር የሴቶች ፉክክር አረንጓዴው ጎርፍ ሊባል በሚችል መልኩ አስደናቂ ውጤት ተመዝግቧል ። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የወርቅ ፤ የብር እና የነሐሱን ሜዳሊያዎች ጠቅልለዋል።  ውብርስት አስቻለ 1ኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ ፤ 2ኛ የወጣችው ሳምራዊት ሙሉጌታ የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች ። 3ኛ ደረጃውም የኢትዮጵያ ሲሆን አትሌት ምጥን እውነቴ የነሐስ ሜዳሊያው እንዲገኝ አስችላለች ። በሌሎች ፉክክሮችም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድልችን ያስመዘገቡበት የአፍሪቃ አትሌቲክስ የጀመረው ቅዳሜ ሚያዝያ 21 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ነው ። ውድድሩ እስከ ሚያዝያ 25 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ለ5 ተከታታይ ቀናት በዛምቢያ ንዶላ ከተማ ይቀጥላል ። ለአዳጊ እና ወጣት አትሌቶቻችን በመላ መልካም ውጤት እንመኛለን ። 

አትሌቶች ለመሮጥ ተዘጋጅተው፦ ፎቶ ከክምችት ክፍልምስል Sven Hoppe/dpa/picture alliance

ከዚሁ ከዛምቢያው ውድድር ጋር በተያያዘ ዜና፦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የአፍሪቃ አትሌቲክስን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንድትመራ መመረጧን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል ዘግቧል ። ደራርቱ ለቀጣይ አራት ዓመታት ምክትል ሆና እንድትመራ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ የተመረጠችው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በዛምቢያ ሉሳካ ፍፃሜውን ባገኘው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ጉባኤ ላይ ነበር ።

ሙዚቃ፥

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት በነበረ ወሳኝ ፍልሚያ ሊቨርፑል ለረዥም ጊዜ ሲያልመው የነበረውን ድል ተቀዳጅቷል ። በትናንቱ ግጥሚያ አስጨናቂ ሆኖ ጨዋታውን የጀመረው ሊቨርፑል በ15 ደቂቃዎች ብቻ ቶትንሀም ሆትስፐር ላይ ሦስት ተከታታይ ግቦችን አስቆጥሯል ። ታሪክ ራሱን ደገመ እንዲሉ ቶትንሀም ሆትስፐር ባለፈው ሳምንትም በኒውካስትል ዩናይትድ 6 ለ1 በተረታበት ግጥሚያ በ21 ደቂቃዎች ብቻ 5 ግቦችን ለማስተናገድ ተገዶ ነበር ።

የሊቨርፑል የ15 ደቂቃዎች በትር በእርግጥም ለቶትንሀም ሆትስፐር እጅግ አስደንጋጭ ነበር ።  ኩርቲስ ጆንስ፤ ሉዊስ ዲያዝ እና ሞሐመድ ሳላህ በፍጹም ቅጣት ምት ሦስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ 15 ደቂቃም አላለፈም ነበር ። «ገንዘባችን እንዲመለስልን እንፈልጋለን» ሲሉ በዝማሬ ተቃውሟቸውን ሲገልጡ የነበሩ የስፐርስ ደጋፊዎች ሦስተኛ ግብ ስትቆጠር የተወሰኑት በንዴት ከሜዳ ወጥተዋል ።  በባለፈው ሳምንት የቶትንሀም ሆትስፐርስ ብርቱ ሽንፈት ደጋፊዎች ስቴዲየም የገቡበት የቲኬት ገንዘብ ተመልሶላቸዋል ነበር ።

ሞሐመድ ሳላኅ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ግብ ሮቢ ፎውለር በሊቨርፑል የ369 ጨዋታዎች ካስቆጠራቸው በአንድ እንዲበልጥ አስችሎታል ። ሞሐመድ ሣላኅ 298 ጊዜ ተሰልፎ ለሊቨርፑል ባስቆጠራቸው ግቦች ከሽቴፋን ዤራርድ በሁለት ግቦች ብቻ ይበለጣል ። ዤራርድ በ710 የሊቨርፑል ጨዋታዎች 186 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል ። በሊቨርፑል ታሪክ ኢያን ረሽ ላይ ግን የሚደርስ አልተገኘም ። ኢያን ለሊቨርፑል በተሰለፈባቸው 660 ጨዋታዎች 346 ግቦችን አስቆጥሯል።

አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ሲጋጠሙ፦ ፎቶ ከክምችት ክፍላችንምስል Martin Rickett/PA Wire/dpa/picture alliance

ትናንት የቶትንሀም ሆትስፐርን ዐይነጥላ የገፈፈችውን የመጀመሪያ ግብ 40ኛው ደቂቃ ላይ ሔሪ ኬን ከመረብ ሲያሳርፍ እግረ መንገዱንም በፕሬሚየር ሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች 208 አድርሷል ። በዚህም ከዋይኔ ሩኒ ጋር ተስተካክሏል ። ሶን ሆይንግ እና ሪቻርሊሰንም በባከነ ሰአት አስቆጥረው ቡድናቸውን አቻ አድርገው ነበር ።

ልብ ሰቃይ በነበረው በትናንቱ ግጥሚያ ቶትንሀም ሆትስፐር አቻ አቻ የምታደርገውን ሦስተኛ ግብ በብራዚሊያዊው አጥቂ ሪቻርሊሰን ደ አንድሬ ያስቆጠረው በ93ኛ ደቂቃ የባከነ ሰአት ነበር ። ሪቻርልሲሰን ግቧ እንደተቆጠረች መለያውን አውልቆ ከወገቡ በላይ ራቁቱን በፈንጠዝያ ሜዳውን ሮጦ አዳርሷል ። ሆኖም እዛው ሜዳ ላይ ለማቀርቀር ግን አንድ ደቂቃም አልቆየ ። መደበኛው የጨዋታ 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው 4ኛ ደቂቃ ላይ በሉቃስ ሙራ ብርቱ ስህተት ዲዬጎ ጆታ ሊቨርፑልን ለድል ያበቃችውን ግብ ከመረብ አሳርፏል ።

ዲዬጎ ጆታ በአራት ግጥሚያዎች ያስቆጠረው አምስተኛ ግቡ አንፊልድን በፈንጠዚያ አነቃንቋል ። የጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ የቀኝ ታፋን ግን አሸማቋል ። አሰልጣኙ የማሸነፊያዋ ግብ ስትቆጠር ቡጢያቸውን ጨብጠው አየር ላይ በመወዝወዝ በንዴት ወደ አራተኛ ዳኛ ለመሮጥ ሞክረዋል ። ያኔም ታፋቸውን ሲሸመቅቃቸው ታይተዋል ።  አራተኛ ዳኛው ፊት ተጠግተው ቁጣቸውን ቢገልጡም «መጥፎ ነገር ግን አልተናገርኩትም» ብለዋል ። በቀልድ መልክም አዋዝተው፦ «ለነገሩ በዚያ ቅጽበት ታፋዬ እንዲሸማቀቅ አድርጌያለሁ ። ያው ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ቀድሞውኑ ተቀጥጫለሁ» ብለዋል ።

ሊቨርፑል 56 ነጥብ ይዞ 5ኛ ደረጃን ተቆጣጥሯል ። ውጤቱ ለቀጣዩ የአውሮጳ ሊግ ተፎካካሪነት የሚያበቃ ነው ። ያም ብቻ አይደለም ምናልባትም በቀጣይ ጨዋታዎች ማንቸስተር ዩናይትድ ነጥቦችን የሚጥል ከሆነ የሻምፒዮንስ ሊግ ስፍራንም የመረከብ እድል አለው ። ይህ እድል ግን እጅግ ጠባብ ነው ።  ምክንያቱም በብሩኖ ፌርናንዴሽ ብቸኛ ግብ አስቶን ቪላን ትናንት ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ሊቨርፑልን በ7 ነጥብ ይበልጠዋልና ።

ቶትንሀም ሆትስፐርስን ጉድ ያደረገው ሊቨርፑል ማንቸስተር ዩናይትድ ላይስ ይደርስ ይሆን? ምስል Nick Potts/PA Wire/dpa/picture alliance

የሊቨርፑል የቀኝ ክንፍ ተከላካይ እና አማካይ አዲስ ሥፍራ የተሰጠው ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ አዲስ ቦታው የተመቸው ይመስላል ። ትናንት ለኩርቲስ ጆንስ የላከውን ጨምሮ ከርቀት በተመጠነ መልኩ በሚልካቸው ኳሶች ብቃቱን ዐሳይቷል ። የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌት በ24 ዓመቱ አሌክሳንደር አዲስ ቦታ ስኬት ሳይደመሙ አልቀሩም ።  

ትናንት በነበሩ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ በርመስ ሊድስ ዩናይትድን 4 ለ1 ቀጥቶታል ።ሳውዝሀምፕተን በኒውካስል የ3 ለ1 ሽንፈትን አስተናግዷል ። ማንቸስተር ሲቲ ፉልሀምን 2 ለ1 በሜዳው አሸንፎታል ። ቀዳሚዋን ግብ በ3ኛው ደቂቃ ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ኧርሊንግ ኦላንድ ቡድኑ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ76 ነጥብ የፕሬሚየር ሊጉን የመሪነት ቦታ ከአርሰናል በአንድ ነጥብ በልጦ እንዲረከብ አስችሏል ። ሁለተኛዋ ግብ የጁሊያን አልቫሬዝ ናት ።አርሰናል ነገ ከቸልሲ ጋር ይጋጠማል ። ኒውካስል ዩናይትድ  በ65 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃውን ይዟል ።

ወራጅ ቀጣናው ውስጥ 18ኛ እና 19ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኤቨርተን እና ላይስተር ዛሬ ማታ ይጋጠማሉ ። ለሁለቱም የምሽቱ ግጥሚያ እጅግ ወሳኝ ነው ። ላይስተር ሲቲ 29 ኤቨርተን 28 ነጥብ አላቸው ።  ከስራቸው 24 ነጥብ ይዞ 20ኛ ደረጃ ላይ የተዘረጋው ሳውዝሀምፕተን ብቻ ይገኛል ። ከበላያቸው ደግሞ ተስተካካይ ጨዋታውን አከናውኖ 30 ነጥብ የያዘው ኖቲንግሀም ፎረስት ሰፍሯል ። ከሁለቱ የአንዱ ማሸነፍ ኖቲንግሀም ፎረስተን ወደ ወራጅ ቀጣናው ጎትቶ ይጥለዋል ። ድል አድራጊ ራሱን ከወራጅ ቀጣና ያስወጣል ።  

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን ትናንት ሔርታ ቤርሊንን 2 ለ0 በማሸነፍ ነጥቡን 62 አድርሶ የመሪነቱን ስፍራ ዳግም ተረክቧል ። የአሰልጣኝ ቶማስ ቱሁል ባዬርን ሙይንሽን በሠርጊዬ ግናብሬ እና ኪንግስሌይ ኮማን ግቦች ሔርታ ቤርሊንን ለማሸነፍ ግን እጅግ ብርቱ ጥረት ማድረግ ነበረበት ። ዐርብ ዕለት ከቦሁም ጋር አንድ እኩል የተለያየው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአንድ ነጥብ ተበልጦ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ተንሸራቷል ።  

የባየርን ሙይንሽን አጥቂ ሠርጊዬ ግናብሬ ሔርታ ቤርሊን ላይ ግብ አስቆጥሮ ሲፈነጥዝምስል Revierfoto/IMAGO

ቅዳሜ ዕለት ከባዬር ሌቨርኩሰን ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ዑኒዮን ቤርሊን እና ኮሎኝን 1 ለ0 ያሸነፈው ፍራይቡርግ ተመሳሳይ 56 ነጥብ ይዘዋል ። ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ሦስተኛ እና አራተኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ።  ላይፕትሲግ ቅዳሜ ዕለት ሆፈንሀይምን 1 ለ0 ቢያሸንፍም በ54 ነጥቡ አምስተኛ ደረጃ ላይ አስፍሯል ። በዕለቱ አይንትራኅት ፍራንክፉርት እና አውግስቡርግ አንድ እኩል ሲለያዩ ሽቱትጋርት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ1 አሸንፏል ። ቬርደር ብሬመን በደረጃ ሰንጠረዡ ከቦሁም ዝቅ ከሔርታ ቤርሊን ከፍ ብሎ 17ኛ ላይ በሚገኘው ሻልከ የ2 ለ1 ሽንፈት ደርሶበታል ። ቮልፍስቡርግ ትናንት ማይንትስን 3 ለ0 አሸንፏል ።

የአውሮጳ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ

በአውሮጳ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የእግር ኳስ ውድድር የፍጻሜ ተጋጣሚ ሁለተኛው ቡድን ዛሬ ማታ ይታወቃል ። ለአምስት ጊዜያት ለፍጻሜ የበቃው የጀርመኑ ቮልፍስቡርግ የእንግሊዙ አርሰናልን ዛሬ ማታ በመልስ ጨዋታው ለንደን ከተማ ውስጥ አሸንፎ ለፍጻሜው ይደርስ ይሆን? ከ50 ሺህ በላይ ታዳሚዎች በሚከታተሉት የዛሬ ፍልሚያ አሸናፊው በፍጻሜው ባርሴሎናን ይገጥማል ። ባርሴሎና በደርሶ መልስ ግጥሚያ ቸልሲን 2 ለ1 አሸንፎ ነው ለፍጻሜ የበቃው ። የፍጻሜ ግጥሚያው ቅዳሜ፣ ግንቦት 26 ይከናወናል ።  

የመኪና ሽቅድምድም

የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም፦ ፎቶ ከክምችት ክፍላችንምስል HOCH ZWEI/picture alliance

አዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ውስጥ በነበረው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪው ሠርጂዮ ፔሬዝ የቡድን አጋሩ ማክስ ፈርሽታፐንን ቀድሞ አሸናፊ ሆኗል ።  የፌራሪው ሻርል ሌክሌር ሦስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ። ፈርናንዶ አልፎንሶን እና ካርሎስ ሳይንዝን ተከትሎ የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን ስድስተኛ ደረጃ አግኝቷል ። በአጠቃላይ 93 ነጥብ ማክስ ፈርሽታፐን የፎርሙላ አንድ ቀዳሚ ነው ። የትናንቱ አሸናፊ ሠርጂዮ ፔሬዝ 87 ነጥብ ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ይከተላል ። ፈርናንዶ አልፎንሶ እና ሌዊስ ሐሚልተን በ60 እና 48 ነጥቦች የሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃዎችን ይዘዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW