1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 30 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 30 2015

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ማንቸስተር ሲቲ ነገ ከሪያል ማድሪድ ጋር የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ወሳኝ ግጥሚያ ይጠብቀዋል ። አርሰናል የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ የማንሳት ተስፋውን ትናንት ዳግም አለምልሟል ። የኒውካስል የትናንት ሽንፈት የአውሮጳ ሊግ ቦታ የያዘው ሊቨርፑል ሻምፒዮንስ ሊጉንም እንዲማትር ተስፋ አጭሮለታል ።

Fußball | DFB Pokal Halbfinale | VfB Stuttgart - Eintracht Frankfurt | Tor 1:0
ምስል ActionPictures/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ማንቸስተር ሲቲ ነገ ከሪያል ማድሪድ ጋር የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ወሳኝ ግጥሚያ ይጠብቀዋል ። ከነገ በስትያ ሁለቱ የጣሊያን ቡድኖች ወደ ፍጻሜው ለማለፍ ይፋለማሉ ። አርሰናል የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ የማንሳት ተስፋውን ትናንት ዳግም አለምልሟል ። የኒውካስል የትናንት ሽንፈት የአውሮጳ ሊግ ቦታ የያዘው ሊቨርፑል ሻምፒዮንስ ሊጉንም እንዲማትር ተስፋ አጭሮለታል ። ባለፈው ግጥሚያ በባከነ ሰአት ለሽንፈት የተዳረገው ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ ታች ባለ ቡድን ትናንትናም ዕድሉን አሳልፎ ሰጥቷል ።  በአውሮጳ ሻምፒዮንስ የሴቶች ፉክክር ለዋንጫ የደረሰው ቮልፍስቡርግ የወንዶቹ ቡድን በቡንደስ ሊጋው የግብ ጎተራ ሆኗል ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በነበሩ ፉክክሮች ድል ቀንቷቸዋል ። በፎርሙላ አንድ ውድድር ባለፈው ሳምንት ያሸነፈው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ሠርጂዮ ፔሬዝ ትናንት ቦታውን ለቡድን አጋሩ ማክስ ፈርሽታፐን ለቋል ።

የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድምምስል HOCH ZWEI/picture alliance

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ ውድድሮች አሸናፊ ሆነዋል ። ትናንት ቼክ ሪፐብሊክ ፕራህ ከተማ ውስጥ በተከናወነው የፕራህ (ፕራግ)ማራቶን በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ወርቅነሽ ኢዴሳ ሦስት ኬንያውያትን አስከትላ ለድል በቅታለች ። በ27ኛው የፕራህ ዓለም አቀፍ ማራቶን ወርቅነሽ አሸናፊ የሆነችው 2:20:42 በመሮጥ ነው ። ኬንያውያቱ ማርጋሬት ዋንጋሪ ሙሪዩኪ፤ ቪዮላ ጄሌጋት ኪቢዎት እና ፓሜላ ሮቲች ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል ።

በዚሁ ማራቶን የወንዶች ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሲሳይ ለማ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል ። ኬንያዊው ሙቲሶ ሙኒያዎ 2:05:09 በመሮጥ የአንደኛ ደረጃ አግኝቷል ። ሲሳይ በአሌክሳንደር የተበለጠው በአንድ ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ነው ። ኬንያውያኑ ፊሌሞን ሮኖ እና ጁስቱስ ካንጎጎ የሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ይዘዋል ። ጃፓናውያኑ አትሌቶች ታካዉኪ ሊዳ፤ ዩኢቺ ያሱኬንያውያኑን ተከትለው ገብተዋል ።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተከናወነው የፒትስበርግ ግማሽ ማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ብዙዬ ድሪባ 1:10:43 በመሮጥ አንደኛ ደረጃ አግኝታ አሸንፋለች ። የወንዶች የግማሽ ማራቶን ድልን ኬንያዊው ዌስሌይ ኪፕቱ በ1 ሰአት ከ1 ደቂቃ 21 ሰከንድ ይዟል ።  

በወንዶች የማራቶን ሩጫ ፉክክር አሜሪካዊው ሯጭ ቴይለር ማክካንድለስ 2:05:09 በመሮጥ አሸናፊ ሆኗል ። በሴቶች ፉክክርም ሌላኛዋ አሜሪካዊት ማርጎ ማሎኔ 2:41.56 ሮጣ አሸናፊ ሆናለች ።  በውድድሩ ከዩናይትድ ስቴትስ 50 ግዛቶች እና ከዐሥር የተለያዩ ሃገራት 35,000 ግድም ሯጮች ተሳትፈውበታል ።

ሯጮች ለውድድር ተዘጋጅተው፦ ፎቶ ከክምችት ማኅደርምስል Sven Hoppe/dpa/picture alliance

በአፍሪቃ አትሌቲክስ ውድድር የተካፈለው ዕድሜያቸው ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በዛምቢያ ውድድሩን አጠናቆ ተመልሷል ። ለአምስት ቀናት ንዶላ ከተማ ውስጥ በተከናወነው ውድድር የኢትዮጵያ ቡድን ከ46 የአፍሪቃ አገራት መካከል በ6 ወርቅ፣ በ11 ብር እና በ6 ነሃስ፣ በድምሩ በ23 ሜዳልያዎች የአራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል ። በውድድሩ ደቡብ አፍሪቃ፣ ናይጄሪያና ኬንያ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንን ወክለው በውድድሩ 30 አትሌቶች ተካፋይ ነበሩ ።

ቀደም ሲል በአዋቂ አትሌቶች ከተገኘው ውጤት ሲነጻጸር የአዳጊና ወጣቶቹ አትሌቶች ውጤት አበረታች ሆኖ ታይቷል ። የኢትዮጵያ ቡድን ቅዳሜ ሚያዝያ 28 ቀን፣ 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገባ የአቀባበል እና የሽልማት መርኃ-ግብር እንደተካሄደለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ዘግቧል ።

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ሴቶች የ2015 ዓ.ም የውድድር ዓመት ፕሪሚየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ውድድሮች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ትናንት ተጠናቀዋል ። የውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ጨዋታዎች ትናንት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መከናወናቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሩ ዘግቧል ።   መጀመሪያ ላይ በተኪያሄደው ግጥሚያ ሀዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1-0 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን በሦስተኝነት አጠናቋል። በፍጻሜው ግጥሚያ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቻልን 2-0 አሸንፏል ። የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ የ2015 የውድድር ዘመን ደግሞ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል ። ሁለተኛው ዙር በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ፍፃሜውን ሲያገኝ ሲዳማ ቡና የዋንጫ እና ወርቅ ሜዳሊያ ፣ ሁለተኛ የወጣው ሀምበሪቾ ዱራሜ የብር እንዲሁም ቂርቆስ ክ/ከተማ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆናቸው ተዘግቧል ።

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ

አርሰናል ትናንት ወሳኝ ድሉን በማስመዝገብ ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ማጥበብ ችሏል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ 82 ነጥብ ይዞ የፕሬሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዡን ይመራል ።  አርሰናል ትናንት ለድል የበቃው በማርቲን ኦዴጋርድ 14ኛ ደቂቃ ላይ እና በፋቢያን ሼር 71ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ነው ። በትናንቱ ግጥሚያ በእርግጥ የኒውካስል ዩናይትድ አጥቂዎች አስጨናቂዎች ነበሩ ። ሆኖም የአርሰናል ቡድን ብቃት እና ቁርጠኝነት ታክሎበት የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ የማንሳት ሕልሙን አለምልሟል ። አርሰናል ትናንት ሽንፈት ቢገጥመው ኖሮ ከ19 ዓመታት ወዲህ ሲመኘው የቆየውን ዋንጫ የማንሳት ተስፋው ይጨልም ነበር ።

ሞሀመድ ሳላኅ ለሊቨርፑል 100ኛ ግቡን አስቆጥሩ ለራሡ ታሪክ ሲጽፍ የቡድኑም ተስፋ አለምልሟል ምስል Mike Egerton/PA/picture alliance

እሁድ ዕለት አርሰናል ከብራይተን እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ ከኤቨርተን ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ውጤት ምናልባትም የዘንድሮ የዋንጫ ባለድል የሚለይበት ይሆን ይሆናል ። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሳምንታት ይቀሩታል ። አርሰናል ሦስት እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ አራት ቀሪ ጨዋታዎች አሏቸው ።  

በሌላ የትናንት ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ በግብ ጠባቂው ዴቪድ ዴጊኣ ዳግም ስህተት በዌስትሀም ዩናይትድ የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል ። ባለፈው ግጥሚያም ባለቀ ሰአት ግብ ተቆጥሮበት ለሽንፈት የተዳረገው ማንቸስተር ዩናይትድ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ ነው ። ከአጠቃላይ ግጥሚያዎች አራት ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ዩናይትድ የፕሬሚየር ሊጉ አራት ምርጥ ቡድን ውስጥ ቆይቶ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍ ብዙ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል ። ከሌሎች ቡድኖች አንጻር አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ63 ነጥቡ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።  አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ኒውካስል ዩናይትድም በ65 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው ።  

ምናልባት ባለፉት ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ያስመዘገበው ሊቨርፑል ለሁለቱም ስጋት ሊሆን ይችላል ። የአውሮጳ ሊግ ቦታውን አምስተኛ ደረጃ ላይ በመስፈር የተረከበው ሊቨርፑል በ62 ነጥቡ ከማንቸስተር በአንድ ከኒውካስል በሦስት ነጥቦች ብቻ ነው የሚበለጠው ። በቅዳሜው ግጥሚያ ሞሀመድ ሳላኅ ለሊቨርፑል 100ኛ ግቡን አስቆጥሩ ለራሡ ታሪክ ሲጽፍ የቡድኑም ተስፋ አለምልሟል ።

በፕሬሚየር ሊጉ ቀሪ አራት ጨዋታዎች በሻምፒዮንስ ሊጉ ውስጥ ለመቆየት፤ ወደሻምፒዮንስ ሊጉ ለመግባት እና ላለመውረድ የሚደረጉ ብርቱ ፉክክሮች የሚታይባቸው አጓጊ ጨዋታዎች ናቸው ። 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ብራይተንም ቢሆን ወደ ዚሁ ፉክክር የመግባት ዕድሉ አልከሰመም ። ብራይተን ዛሬ ማታ ከኤቨርተን ጋር ከተጫወተ በኋላም ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ ይቀሩታል፤ 55 ነጥብ አለው ። ወራጅ ቀጠና ውስጥ 18ኛ እና መጨረሻ 20ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኖቲንግሀም ፎረስት እና ሳውዝሀምፕተን ዛሬ ማታ የሚያደርጉት ጨዋታም የሞት ሽረት ነው ።

ኧርሊንግ አላንድ በፕሬሚየር ሊጉ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰን ሰብሯል ምስል Darren Staples/Newscom/picture alliance

ኧርሊንግ አላንድ በፕሬሚየር ሊጉ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰን ሰብሯል ። ማንቸስተር ሲቲ ረቡዕ ዕለት ከዌስት ሀም ጋር ባደረገው ጨዋታ 70ኛ ደረቂቃ ላይ ያስቆጠራት ግብ የ22 ዓመቱ ኖርዊያዊ አጥቂን ከፍ አድርጋለች ። በዚህ ግብ ኧርሊንግ አላንድ ቡድኑ እንዲያሸንፍ ከማስቻሉም ባሻገር በአላን ሺረር እና አንዲ ኮል ቀደም ሲል ተይዞ የቆየውን የ34 ግቦች ክብረወሰን መስበር ችሏል ። ሁለቱ የቀድሞ ተጨዋቾች በፕሬሚየር ሊጉ የጨዋታ ዓመት ያስቆጠሯቸው 34 ግቦችን ክብረወሰን ሆነው ቆይተው ነበር ።

ማንቸስተር ሲቲ ከትናንት በስትያ ኤትሀድ ስታዲየሙ ውስጥ ባደረገው ግጥሚያ ግን ሁለቱን የማሸነፊያ ግቦች ሊድስ ዩናይትድ ላይ ያስቆጠረው ከቱርክ ቤተሰቦች የተወለደው ጀርመናዊው ኢልካይ ጉንዶዋን ነው ። ማንቸስተር ሲቲ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ኢልካይ አግብቶ ሦስተኛ ግቡ ማለትም ሔትትሪክ እንዲሆንለት በሚል ኧርሊንግ አላንድ ኳሱን አቀብሎታል። የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ኧርሊንግ አጉል በጣም ደግ መሆኑን ያቁም ብለዋል ። የፍጹም ቅጣት ምቷን ኢልካይ ማስቆጠር አልቻለም ፤ ሔትትሪክም ለልሠራም ። ለሊድስ ዩናይትድ ብቸኛዋን ግብ ሮድሪጎ አስቆጥሯል ።

ኧርሊንግ አላንድ በአጠቃላይ የዘንድሮ ውድድሮች ለማንቸስተር ሲቲ እስካሁን 51 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል ። ምናልባትም ገና አፍላ ወጣት አጥቂ ከመሆኑ አንጻር ወደፊት በርካታ ግቦችን በማስቆጠር እነ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ ላይ ሊደርስም ምናልባትም በዚሁ ግስጋሴው ከቀጠለ ሊበልጣቸውም ይችል ይሆናል ።

ቡንደስሊጋ

የቮልፍስቡርግ ደጋፊዎች የአንድ ሳምንት ፌሽታ እና ፈንጠዝያ ትናንት ቀዝቃዛ ውኃ ተሸልሶበታል ። ባለፈው ሳምንት የሴቶች የእግር ኳስ ቡድናቸው አርሰናልን በደርሶ መልስ የ3 ለ2 ውጤት ድል አድርጎ ከለንደን ሲመለስ በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ከባርሴሎና ጋር መድረሱን በማረጋገጥ ነው ። የወንዶቹ ቡድን ግን በቡንደስሊጋው ትናንት ጉድ አድርጓቸዋል ።  በመጀመሪያው አጋማሽ አራት በድምሩ ስድስት ግቦች በቦሩስያ ዶርትሙንድ ተቆጥሮባቸዋል ። 46 ነጥብ ይዘውም 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። በዚህ ውጤት ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ነጥቡን 64 አድርሶ ከመሪው ባየርን ሙይንሽን በአንድ ነጥብ ብቻ ይበለጣል ። ቮልፍስቡርጎች በትናንቱ ብርቱ ሽንፈት ለአውሮጳ ሊግ ኮንፈረንስ የነበራቸው ግስጋሴም ልጓም ገብቶለታል ።  ፍራይቡርግ በ56 እንዲሁም ባዬር ሌቨርኩሰን በ48 ነጥብ 5ኛ እና 6ኛ የአውሮጳ ሊግ ኮንፈረንስ ቦታውን ይዘዋል ።

 በመጀመሪያው አጋማሽ አራት በድምሩ ስድስት ግቦችን ቮልፍስቡርግ ላይ ያስቆጠረው የቦሩስያ ዶርትሙንድ ቡድንምስል Martin Meissner/AP/picture alliance

ትናንት በኬቪን ካምፕል ብቸኛ ግብ ፍራይቡርግን አንድ ለዜሮ ያሸነፈው ላይፕትሲሽ በ57 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። አውግስቡርግን ቅዳሜ 1 ለዜሮ ያሸነፈው ዑኒዮን ቤርሊን እንደፍራይቡርግ 56 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ግን 4ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። መሪው ባየርን ሙይንሽን ቬርደር ብሬመንን ከትናንት በስትያ 2 ለ1 አሸንፏል ። ኮሎኝ ባዬር ሌቨርኩሰንን 2 ለ1፤ ሻልከ ማይንትስን 3 ለ2 አሸንፈዋል ።  በተለይ ሻልከ በቅዳሜ ድሉ እንደምንም ከወራጅ ቀጣናው ወጥቶ 15ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ከስሩ ሽቱትጋርት፤ ቦሁም እና ሔርታ ቤርሊን ከ16ኛ እስከ መጨረሻ 18ኛ ተደርድረዋል ። ሽቱትጋር በሔርታ ቤርሊን 2 ለ1 ተሸንፏል ። ሆፈንሀይም አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 3 ለ1 ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባሽ ቦሁምን 2 ለ0 አሸንፈዋል ።

በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ በነገው ዕለት ማንቸስተር ሲቲ ከሪያል ማድሪድ ጋር ይጋጠማል ። ከነገ በስትያ ደግሞ በጣሊያን ሴሪ ኣ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢንተር ሚላንና ኤሲ ሚላን ይፋለማሉ ። 83 ነጥብ ያለው ናፖሊ የጣሊያን ሴሪኣ ዋንጫ ከወዲሁ መውሰዱን አረጋግጧል ። ተከታዩ ጁቬንቱስ 66 ነጥብ ላትሲዮ 64 እንዲሁም ኢንተር ሚላን እና ኤሲ ሚላን 63 እና 61 ነጥብ አላቸው ።

የመኪና ሽቅድምድም

የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድምምስል Frank Augstein/AP/picture alliance

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪዎች ትናንትናም ድል ቀንቷቸዋል ። በትናንቱ የሚያሚ ሽቅድምድም ማክስ ፈርሽታፐን እንዲሁም ሌላኛው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ሠርጂዮ ፔሬስ ተከታትለው 1ኛ እና 2ኛ ወጥተዋል ። የአስቶን ማርቲን አሽከርካሪው ፈርናንዶ አሎንሶ 3ኛ እንዲሁም የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ጂዖርጅ ሩሴል 4ኛ ደረጃ አግኝተዋል ። የማርሴዲሱ ሌዊስ ሐሚልተን በፌራሪው አሽከርካሪ ካርሎስ ሳይንዝ ተቀድሞ 6ኛ ደረጃ ይዟል ። እስካሁን በተደረጉ አጠቃላይ ውድድሮች ማክስ ፈርሽታፐን በ119 ነጥቦች ይመራል ። ሠርጂዮ ፔሬስ እና ፈርናንዶ አሎንሶ 105 እና 75 ነጥብ ሰብስበው ይከተላሉ ። ሌዊስ ሐሚልተን 56 ነጥብ ይዞ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW