የሚዲያ ነፃነትን የሚጋፉ "በርካታ" አሳሳቢ ጉዳዮች ተለይተዋል - የኢሰመኮ ዓመታዊ ሪፖርት
ዓርብ፣ ጥቅምት 6 2019
የሚዲያ ነፃነትን የሚጋፉ "በርካታ" አሳሳቢ ጉዳዮች ተለይተዋል - የኢሰመኮ ዓመታዊ ሪፖርት
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሚዲያ ነፃነትን የሚጋፉ "በርካታ" ያላቸው አሳሳቢ ጉዳዮች መለየታቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው ዓመታዊ የምርመራ ዘገባው አመለከተ። ብሔራዊዉ የመብቶች ድርጅት "በመንግሥት ኃይሎች በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀሙ የቅድመ ክስ እሥር ድርጊቶች፣ ጋዜጠኞች መረጃ ለማግኘት ፈቃድ እንዲያመጡ መገደድ የመረጃ ነፃነትመብትን በእጅጉ ያጠበቡ "ማነቆዎች" ሆነው ቀጥለዋል ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥታቸውን የቀጣይ አቅጣጫ ሲያቀርቡ "የሚዲያ ምኅዳሩ ሕግን፣ ሀገራዊ እሴቶችን እና ፍላጎቶችን ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀስ ይደርጋል" ማለታቸው ይታወሳል።
በዘርፉ ላይ በክልሎች የተስተዋሉ ጥሰቶች ዝርዝር
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰኔ 2017 እስከ ሰኔ 2018 የነበረውን የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ኹኔታ በዝርዝር ባጠናቀረበት ባለ 126 ገጽ ሪፖርቱ "ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ እና የመረጃ ነጻነት መብትን የሚጥሱና የሚያጣብቡ አሳሳቢ" ያላቸውን ክስተቶች በቦታና በጊዜ ለይቶ ሰንዷል። ለአብነትም በአዲስ አበባ የሚገኙ "አንዳንድ" ያላቸው የግል የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶች አርታዕያን ያሳለፏቸውን ዝግጅቶች ለመገናኛ ብዙኃን ተቋማቱ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ፣ ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ተቋማት እና የሌሎች አካላትን ፍላጎት መሰረት የሚያንጸባርቁ ይዘቶችን ብቻ "እንዲስተላለፉ ማስገደድ" ቀዳሚው ሆኖ የተለየው ነው። ኮሚሽኑ ይህ አሠራር የሕዝብ "ሚዛናዊ እና ገለልተኛ መረጃ የመፈለግ እና የማግኘት መብቱን ያሳጣል" ብሏል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመንግሥት በጀት የሚደገፉ እና የውጪ ሀገር የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች መረጃዎችን ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ የክልሉ የጸጥታ አካላት ወደ አካባቢው ገብቶ የመሥራት ፈቃድ ከአካባቢው የዞን አስተዳዳሪዎች እንዲያመጡ እያስገደዱ መሆኑን፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ በመንግሥት በጀት የሚደገፉ መገናኛ ብዙኃን በሥራቸው ሂደት ማስፈራሪያና ወከባ የሚደርስባቸው መሆኑን፤ የአካባቢው ባለሥልጣናት መገናኛ ዐውታሮች የጀመሩትን የምርመራ ዘገባ አቋርጡ፣ የተሠራውም እንዳይተላለፍ የሚሉ ትዕዛዞችን የሚሰጡ መሆኑንም ኮሚሽኑ አጋልጧል። በተመሳሳይ በሲዳማ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የክልሎቹ ምክር ቤቶች በሚያዘጋጇቸው ጉባዔዎች ላይ በመንግሥት በጀት ከሚደገፉ የመገናኛ ብዙኃን በስተቀር የግል፣ የውጪ ሀገር እና የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን እንዳይዘግቡ የተከለከሉ ስለመሆኑ" በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር ያለፈው ዓመት መገባደጃ ጀምሮ የቀጠለውን እንዲህ ያለውን የግል እና የውጭ የመገኛኛ ብዙኃንን መርጦ የመጋበዝ ሀቅ ግን በዚህ ሪፖርቱ አልጠቀሰውም። ወይም ማካተት አልፈለገም። ይህ ጉዳይ በዚህኛው አዲስ ፓርላማ ይሻሻላል የሚል ተስፋ የነበረ ቢኖርም አሁንም መገናኛ ብዙኃንን መርጦ ለዘገባ መጥራት እስከዛሬ ድረስ ባለው የምክር ቤቱ ውሎ ቀጥሏል። በዘርፉ ላይ የሚሠራ፣ ጥናትም የሚያደርግ አንድ ባለሙያ ይህንን በሚገባ ታዝቧል። የኢሰመኮ ዓመታዊ ዘገባ እንዳመለከተው በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙኃን ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ በሚሠሯቸው ሥራዎች የክልሉ የጸጥታ አካላት ‘‘ያነሳችሁትን ፎቶ እና ቪዲዮ አሳዩን’’፣ ‘‘ማን ፈቅዶላችሁ ነው እየዘገባችሁ ያላችሁት’’ በማለት ወከባ፣ ማስፈራራትና ድብደባ የሚፈጸሙ መሆኑ እንዲሁም እንደ ካሜራ ያሉ ቁሳቁሶችን የመንጠቅ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ መሆኑን ዘርዝሯል። ኮሚሽኑ በክትትል የለያቸው ጥሰቶች "ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ እና የመረጃ ነጻነት መብትን የሚጥሱና የሚያጣብቡ አሳሳቢ ኹኔታዎች መካከል ናቸው" ብሏል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ሪፖርቱን ያቀረቡ ዕለት ይህንኑ ጠቅሰዋል
የኢሰመኮ ሪፖርት "በመንግሥት ኃይሎች በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀሙ የቅድመ ክስ እሥር ድርጊቶች፣ ጋዜጠኞች መረጃ ለማግኘት ፈቃድ እንዲያመጡ መገደድ የመረጃ ነፃነት መብትን በእጅጉ ያጠበቡ "ማነቆዎች" ሆነው ቀጥለዋል ብሏል። የአሶሼትድ ፕረስ የኢትዮጵያ ዘጋቢ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ ምስል ሲቀርፅ በመታየቱ በፖሊስ ተይዞ ለቀናት ታስሮ ቆይቶ ተለቋል። በተመሳሳይ ስለጉዳዩ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከታገደ ውራቶች እንደተቆጠሩ ከምንጮቻችን ማረጋገጥ ችለናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥታቸውን አቅጣጫ ሲዘረዝሩ የመገናኛ ብዙኃንንየተመለከተውንም አብረው መጥወሳቸው ይታወሳል።
ስለ ኢትዮጵያ የሚድያ ምኅዳር የቀረቡ ጥሪዎች
የኢትዮጵያሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ - ኢሕአፓ "በእሥር ላይ ያሉ የማንነትና የፖለቲካ እስረኞች" እና "ሕጋዊ መሠረት ሳይኖር የተያዙ" ያላቸው ሰዎች በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ እንዲፈቱ ሲል በጠየቀበት መግለጫው "ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ተሳታፊዎችና የማኅበረሰብ አንቂዎች ሙያቸውንና ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ የሕግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው" ጠይቋል። በተመሳሳይ ሲፒጄ ኢትዮጵያ ውስጥ በሽብር ተከሰው በእሥር ላይ የሚገኙ 5 ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጠይቋል። ኢንተርናሽናል ሚድያ ሰፖርት ከወራት በፊት ባወጣው የግሪጎሪያን 2025 የዘርፉ የጥናይ ውጤት ኢትዮጵያ ውስጥ በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ "ሰፊ እሥራቶች፣ አፈናዎች እና ትንኮሳዎች የተጋረጡበት ወቅት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል" ብሎ ነበር። የጥናት ግኝቱ በተጠቀሰው 2025 "ቢያንስ 44 ጋዜጠኞች በጸጥታ ኃይሎች ወይም ባልታወቁ ጥቃት አድራሾች ታፍነዋል ወይም ታስረዋል" ሲል በጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ነው የተባለው ጥቃት በዓይነትም ሆነ በመጠን መጨመሩን ጠቁሞ ነበር።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ