1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሐምሌ 22 2014

የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለፈጣሪ ምስጋና እንዲቀርብ ጥሪ የሚያቀርብ ዘለግ ያለ ደብዳቤ የተደበላለቀ ምላሽ አግኝቷል። በጥሪው ተስማምተው «አሜን» ያሉ የመኖራቸውን ያክል ሐይማኖት እና ፖለቲካ መደበላለቁ ያሳሰባቸው፤ አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ ያልተጣጣመላቸው ትችት ጽፈዋል። የአል ሸባብ ጥቃት እና የደራርቱ ቱሉ ጥሪም ውይይት ፈጥረዋል።

Äthiopien Abiy Ahmed Premierminister
ምስል picture-alliance/AP Photo/Saudi Press Agency

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተረጋገጡ የፌስቡክ እና ትዊተር ገፆች የተሰራጨው «ዛሬም እንደ ትላንቱ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን እጃችንን ለምሥጋና እንዘረጋለን» የሚል ደብዳቤ በሳምንቱ መነጋገሪያ ከነበሩ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ ነው። ጠቅላይ ምኒስትሩ በዚህ ደብዳቤያቸው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ የታሪክ፣ የባህል እና የንግድ እንቅስቃሴዎች እየጠቀሱ እርሳቸው «የኢትዮጵያ አምላክ» ላሉት ምስጋና እንደሚገባ ጽፈዋል። 

ኢትዮጵያ የገጠሟትን ረሐብ፣ ድርቅ፣ የርስ በርስ ጦርነት የመሳሰሉ ፈተናዎች ተሻግራለች የሚሉት ዐቢይ ለዚህም ምስጋና ማቅረብ እንደሚገባ ይጠቅሳሉ። በዚሁ ደብዳቤ የጠቅላይ ምኒስትሩ መንግሥት ያከናወናቸውን ተግባራት እና አገሪቱም የገጠሟትን ችግሮች ተዘርዝረዋል። በደብዳቤው ዐቢይ «ከክፉ ወረርሽኝ ጠብቆናል፤ ከአንበጣ መንጋ ታድጎናል። ድርቅ መቅሰፍት እንዳይሆን ከበር ቆሞልናል፤ ከቅርብ እና ከሩቅ የተነሣብንን የማፈራረስ አደጋ ቀልብሶልናል» ለሚሉት ፈጣሪ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ለአንድ ደቂቃ ቆመው ምስጋና እንዲያደርሱ ጥሪ አቅርበው ነበር። 

የጠቅላይ ምኒስትሩ ደብዳቤ አስራ ሦስት ምዕራፎች ያሉት ሲሆን ሶስት ገጽ ነው። ይፍቱ ባሉዳዲ «አንብቤ ስለማልጨርሰው ኮሜንት ላንብብ» ሲሉ ለማጠናቀቅ እንደተፈታተናቸው ጠቆም አድርገዋል። የዐቢይ ደብዳቤ በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጻቸው ከ21 ሺሕ በላይ አስተያየቶች ተጽፈውለታል። አስተያየቶቹ በሙሉ ግን ዐቢይ ባነሱት ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮሩ አይደሉም። አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ አትሌቶች በተደረገው አቀባበል ላይ ጠቅላይ ምኒስትሩ አለመገኘታቸውን እየጠቀሱ «ወዴት ጠፉ?» የሚሉ ናቸው። አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንዲያውም «አብቹ አንተ መሆንህን የማምነው በቪዲዮ ስትቀርብ ብቻ ነው» የሚል አስተያየት ጽፈዋል። አብደል ፈታ የተባሉ ሰው ደግሞ «አብሸሪ ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ ነች። ለኢትዮጵያ አምላክ ምስጋናዬን አቃርበለሁ» በማለት ዐቢይ ላቀረቡት የምስጋና ጥሪ የተስማማ መልስ ሰጥተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሱ «አሜን» ያሉ ዐቢይንም ያመሰገኑ በርካቶች ናቸው። አስራት ዳዲ በበኩላቸው «አብቹዬ በምንም ይሁን በምንም በምታልፍበት ሁሉ አምላክ ከአንተ ጋር ይሁን» የሚል አስተያየት በዚያው በፌስቡክ ከዐቢይ ደብዳቤ ስር መልስ ሰጥተዋል። 

የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ጥሪ በርካታ ተቃውሞዎች እና ትችቶችም ገጥመውታል። ዳዊት ጃቢር «ይኸዉልኽ ጌታው ይሄንን ሀገር ድሀ እና ለማኝ ካረጉት ነገሮች አንዱ ሀይማኖት ነው። ጭራሽ ከፖለቲካ ጋ ሲቀላቀል ደሞ ትልቅ አደጋ ነው» በማለት ያሰፈሩት አስተያየት የሚጠቀስ ነው። «እምነትዎን እና ሥራዎትን አይደባልቁ። በርስዎ እምነት ቤት ደስታ ሆነና እናመሰግን ማለት አግባብ አይደለም» በማለት በቀጥታ የጠቅላይ ምኒስትሩን ሐሳብ የነቀፉት ደግሞ ሳም ኢ ሚካኤል ናቸው። «ከጥቂት ቀናት በፊት ወገኖቻችን አልቀዋል፤ ሞተዋል። እርሶ ደግሞ የጦር ሁሉ አዛዥ ነዎት። «በሞቱት ወገኖች ሀዘን ተሰምቶናል» የሚል ፓርላማ ሳይኖረን እንዴት ለደስታ እናመሰግናለን? ምስጋናችንንስ የቱ አምላክ ነው የሚቀበለው?» እያሉ የሚጠይቁት ሳሚ «ወገናችንን አጥፍተን አምላክን ብናመሰግን ጥቅሙ ምንድነው? የወንጀሉ ተባባሪ ከመሆን በቀር፤ ወቅቱ የንሰሀ ነው» ሲሉ ጽፈዋል። 

አማኑኤል መድሕኔ በትዊተር «የፖለቲካ መሪ ነዎት ወይስ ሰባኪ?» ሲሉ ጠቅላይ ምኒስትሩን ጠይቀዋል። ተሾመ አበበ «ሀሳቡ ከሞላ ጎደል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ራስን የማመስገን (አመስግኑኝ) መልክት ይመስላል። ኢትዮጵያ ለማን ነው የምትተርፈው?» ሲሉ ጠይቀዋል። ናሖም አማረ በበኩላቸው «ጠቅላይ ምኒስትሩን ምንድነው የሚያወሩት?» ሲሉ ይጠይቃሉ። ናሖም «ለየትኛው ነገር ነው ማመስገን ያለብን? ለዋጋ ንረት፣ ለጦርነት? ለግድያዎቹ?» ሲሉ ጽፈዋል። ካሳው የተባሉ ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ ደብዳቤውን አጋርተው «የገባኝ ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ችግር ከማንም ችሎታ እና አቅም በላይ በመሆኑ የፈጣሪ እርዳታ ማሥፈለጉ ነው። ይልቅ ማጉረምረሙን ትተን ያጋጠመንን ውስብስብ ችግር ለመፍታት ባለን አቅም  ቆርጠን መነሣት ወይም መጸለይ ግዴታችን ነው» ብለዋል። 

የአል ሸባብ የሶማሌ ክልል ጥቃት ያጫራቸው ጥያቄዎች

የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን አል ሸባብ የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ የፈጸመው ጥቃት እና አንድምታ ሰሞኑን መነጋገሪያ ሆነው ከሰነበቱ ጉዳዮች አንዱ ሆኗል። የሶማሌ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት ድንበር የተሻገሩ የአል ሸባብ ታጣቂዎች ሁልሁል በተባለ ቦታ «ሙሉ በሙሉ መደምሰሳቸውን» ይፋ አድርጎ ነበር። በአሜሪካ ጦር የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ስቲቭ ታውንሴንድ ትላንት ሐሙስ የአልሸባብ ጥቃት በአብዛኛው በኢትዮጵያ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ገልጸዋል። የአልሸባብ ታጣቂዎች 150 ኪሎ ሜትር ዘልቀው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን፤ ጥቃቱ ሊደጋገም እንደሚችል የጦር መኮንኑ እንደገለጹ ጋዜጠኛ ጄፍ ሴልዲን በትዊተር አስፍሯል። 

ታጣቂ ቡድኑ ጥቃቱን የጀመረው ሐምሌ 13 ቀን 2014 ሲሆን በአፍዴር ዞን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ ገብቷል። አል ሸባብ በሶማሊያ በሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ፈጽሞ የሚያውቅ ቢሆንም ድንበር ተሻግሮ ወደ አገሪቱ መዝለቅ ግን እስካሁን አልተሳካለትም ነበር። 

የሶማሌ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ጥቃቱን መቆጣጠራቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ የሶማሊያ ጦር አዛዥ ጄኔራል ኦዶዋ ይሱፍ እና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴየር ጄኔራል ዘካርያ አብዲ ኻሊፍ በድንበር አካባቢ በምትገኘው ኤልባድሬ የተባለች ከተማ ተገናኝተው እንደነበር ይሱፍ አዳን በትዊተር ፎቶግራፍ አስደግፈው ባሰራጩት መልዕክት ገልጸዋል። 

ዛሬ አርብ ታጣቂ ቡድኑ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድንበር ላይ በምትገኘው አቶ የተባለች ከተማ ላይ ሌላ ጥቃት መሰንዘሩን በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተሰራጩ መረጃዎች ጠቁመዋል። ምስል Farah Abdi Warsameh/AP/picture alliance

ትዊተርን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረ ገጾች በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል እና በአልሸባብ ውጊያ የተገደሉ ታጣቂዎች አስከሬኖችን የሚያሳዩ ምስሎች ሲዘዋወሩ ነበር። የሶማሌ ክልል የጸጥታ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር ያዋሏቸው የታጣቂ ቡድኑ አባላት እጃቸው የፊጥኝ ወደ ኋላ ታስሮ የተለያዩ መልዕክቶች ሲያስተላልፉ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም አሉ። 

ዛሬ አርብ ታጣቂ ቡድኑ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድንበር ላይ በምትገኘው አቶ የተባለች ከተማ ላይ ሌላ ጥቃት መሰንዘሩን በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተሰራጩ መረጃዎች ጠቁመዋል። ጋዜጠኛ ሐሩን ማሩፍ በተረጋገጠ የትዊተር ገጹ እንደጻፈው አልሸባብ ጥቃት የፈጸመው በከተማዋ በሚገኝ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ወታደራዊ የጦር ሰፈር ላይ ሲሆን ውጊያው በሞርታር የተጀመረ ነበር። 

ሞሐድ ዱባድ በትዊተር በእንግሊዘኛ ባሰፈሩት መልዕክት «በሶማሌ ክልል በኩል ኢትዮጵያ ከ1000 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ድንበር ከሶማሊያ ትጋራለች። በሶማሊያ ደግሞ አልሸባብ ይንቀሳቀሳል። ስለዚህ በማንኛውም ጊዜ የጸጥታ ጉድለት ሊከሰት ይችላል። በመሆኑም ጠንካራ ደህንነት እና የመረጃ ልውውጥ ያስፈልጋል» ብለዋል። 

በሶማሊያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በትዊተር ሐሳባቸውን በማጋራት የሚታወቁት ፈይሰል ሮብሌ «የአል ሸባብ ወደ ሶማሌ ክልል መግባት የሚያሳየው የቡድኑን ጥንካሬ ወይንስ የክልሉ ባለሥልጣናት የጸጥታ ዝግጁነት ደካማነት?» ሲሉ ጠይቀዋል። አብርሐም ከበደ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ «ክልሎች ከወራሪዎች ጋር ብቻቸውን እንዲዋጉ የሚተዉት ለምንድነው? የፌድራል መንግሥት የዜጎቹን ደህንነት መጠበቅ ካልቻለ ሚናው ምንድነው?» ሲሉ ጠይቀዋል። ዳዊት ጆቴ «አል ሸባብ በዚያ ክልል መሠረት ሊኖረው አይገባም። ሁለት ልብ ያላቸው ካድሬዎች እና የጸጥታ መዋቅሩ አባላት ካሉ በፍጥነት ሊወገዱ ይገባል» የሚል አስተያየት በትዊተር አስፍረዋል። 

የደራርቱ ቱሉ ጥሪ

በኦሬጎን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካፈሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተደረገላቸው የአቀባበል መርሐ ግብር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ ያቀረቡት ጥሪ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ቀልብ ስቧል። ደራርቱ ትላንት ሐሙስ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ካሰሙት ንግግር መካከል የትግራይ ጉዳይን የተመለከተው ተቀንጭቦ ትዊተርን በመሳሰሉ ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በስፋት ሲዘዋወር ነበር። ይኸ ንግግር የትግራይ ተወላጅ አትሌቶች ከቤተሰቦቻቸው ደስታቸውን የሚጋሩበት መንገድ እንዲበጅ እና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ጥሪ ያቀረቡበት ነበር። 

ደራርቱ ያሰሙት ንግግር የትግራይ ተወላጅ አትሌቶች ከቤተሰቦቻቸው ደስታቸውን የሚጋሩበት መንገድ እንዲበጅ እና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ጥሪ ያቀረቡበት ነበር።ምስል Getty Images/AFP/D. Emmert

ብሌን ማሞ በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት ደራርቱ ቱሉን «ጸጋ፣ ክብር እና ትህትና» የተላበሱ ሲሉ አድንቀዋል። ጆሲ የአብስራ በበኩላቸው «ሰብዓዊነት ከጀግኒትዋ ዕንቁ አትሌት ደራርቱ ቱሉ እንማር» ሲሉ ጽፈዋል። ተክለ ብርሐን ገብረ ሚካኤል የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ «ደራርቱ ምርጥ ሯጭ ብቻ ሳትሆን ውብ አዕምሮ» እንዳላቸው ጠቅሰው ንግግረቸው ሌሎች ሰዎች ሊሰሙት የሚገባ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ደራርቱ በቃላቸው ያሰሙት ንግግር በዝግጅት ከሚቀርብ መግለጫ እንደሚበልጥ ጠቅሰው የኢትዮጵያ ውድ ሐብት ሲሉ አወድሰዋል። ጋዜጠኛ ፍሰሐ ተገኝ «የደራርቱ ቱሉን 5% ያህል ቅንነት ቢኖረን ኢትዮጵያ እጅግ በጣም የምታምር ሰላማዊ አገር ትሆን ነበር፡፡ 5%! ፉገራ የሌለው፣ ያልተቦረሸ፣ ማስመሰል ምን ማለት እንደሆነ በጭራሽ የማያውቅ ያልተመረዘ ቅንነት» በማለት ጽፏል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW