1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት በአማራ ክልል

ማክሰኞ፣ ጥር 18 2013

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ታዳጊዎች የማህፀን ጫፍ ካንሰር ቅድመ መከላከያ ክትባት እየሰጠ ይገኛል። በኢትዮጵያ በዚህ በሽታ 5ሺህ ያህል ሰዎች ህይወታቸው እንደሚያልፍ ተነግሮአል።  

Äthiopien Bahardar Felege Hiwot Krankenhaus
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ባለሙያዎች እንደሚሉት በርካታ የካንሰር ዓይነቶች መነሻቸው አይታወቅም፤  ዝርያቸውም በርካታ ነው፡፡ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ግን መነሻው ቫይረስ እንደሆነ በአማራ  ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራሞች  አስተባባሪ  አቶ ወርቅነህ ማሞ አስረድተዋል፡፡ የበሽታው ዋና መተላለፊያ መንገድ ግብረስጋ ግንኙነት ሲሆን በተለይ ከአንድ በላይ ፆታዊ ግንኙነት የሚያደርጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቂ ሲሆኑ እድመያቸው ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ሴቶች የግብረስጋ ግንኙነት ከፈፀሙ ችግሩ ሊያጋጥም እንደሚችል ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
በድሪም ኬር ሆስፒታል የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ሰፔሸያሊስት ዶ/ር መኮንን አይችሉህም በሽታው ምልክት ሳያሳይ አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበው መልክት ካሳየ በኃላ ግን በሽታው አስከፊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የማሕፀን ጫፍ ካንሰር በዓለም ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱንና በዓለም ደረጃ በየዓመቱ 550ሺህ ሰው በበሽታው እንደሚያዝና 275 ሺህ ያህሉ እንደሚሞት በኢትዮጵያም በየዓመቱ 7ሺህ 500 አዳዲስ በሽተኞች ሲመዘገቡ 5ሺህ ያህሉ ህወታቸው ያልፋል፡፡
በሽታውን ለመከላከል የተለያዩ ዘዴዎች እንዳሉ የሚያስረዱት አቶ ወርቅነህ የመጀመሪያው ስለበሽታው ግንዛቤ መፍጠር ነው፣ ሆኖም አብዛኛው ሰው ስለበሽታው ያነሰ ግንዛቤ እንዳለው ነው ያመለከቱት፡፡
አንድ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ እንዳሉት እንደዚህ ዓይነት በሽታ ስለመኖሩ እንኳ ያወቁት በቅርቡ ነው፣ ግንዛቤም የላቸውም፡፡ የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ሰፔሸያሊስቱ ዶ/ር መኮንን ደግሞ ተከታታይነት ያለው ቅስቀሳና ትምህርት ለህብረተሰቡ መሰጠት እንዳለበት ያምናሉ፡፡
አብዛኛዎቹ የካንሰር በሽታዎች ክትባት እንደሌላቸው የተናገሩት አቶ ወርቅነህ፣ የማሕፀን ካንሰርን ግን በክትባት መከላከል ይቻላል ብለዋል፡፡ ሌላው መከላከያ መንገድ በየጊዜው ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራ ማድረግ ነው፡፡
ክትባቱ በአገራችን ከተጀመረ ገና 3 ዓመቱ እንደሆነ አመልክተው በግብዓት እጥረት ምክንያት ሁሉንም መከተብ ባይቻልም በእድሜ ገድቦ ክትባቱ እየተሰጠ ነው፡፡
የአማራ ጤና ቢሮ ታዲያ ከትናንት ጥር 17/2013 ዓ ም ጀምሮ እስከ ፊታችን ቅዳሜ ጥር 22/2013 ዓ ም ድረስ እድመየያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት ለሆናቸው 590ሺህ 669 ታዳጊዎችየማህፀን ጫፍ ካንሰር ቅድመ መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ አቶ ወርቅነህ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
ክትባቱ ሁለት ጊዜ እንደሚሰጥ አስተባባሪው አመልክተው የመጀመሪያ ተከታቢዎች ከ6 ወራት በኋላ በድጋሜ እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል፡፡

ምስል Alemnew Mekonnen/DW


ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW