1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሊና የሊቢያ ወቅታዊ ሁኔታ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3 2005

በሊቢያ እስካሁን መረጋጋት አልሰፈነም፤ በማሊም እንዲሁ። በተለይ ሰሜን ማሊ ካለፉት ወራት አንስቶ በአክራሪ ሙስሊም ቡድኖች ቁጥጥር ስር ትገኛለች። በአሁኑ ሰዓት ሰሜን ማሊን ከሙስሊም ፅንፈኞች ቁጥጥር ነፃ ለማድረግ ያለው አማራጭ ወታደራዊ ርምጃ ብቻ ይመስላል።

Libyen © VRD #30779901
ምስል fotolia
የባኒ ዋሊድ ከተማምስል Getty Images

የሊቢያ አቢዮት ከአበቃ አንድ አመት አለፈው፤ ሞዓመር አል ጋዳፊም ከተገደሉ ወራቶች ተቆጠሩ። ነገር ግን በሀገሪቷ እስካሁን መረጋጋት አልሰፈነም። በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ፀጥታ አስከባሪዎች የባን ዋልዲን ከተማ ከበው እየጠበቁ ነው። መንስዔው በቅርቡ በዚሁ አካባቢ በአምባገነኑ መሪ ተከታዮች እና ተቀናቃኝ ሚሊሺያዎች መካከል የተጀመረው ግጭት ነው። በምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል በቤንጋዚ ከተማም እንዲሁ በዮናይትድ እስቴትስ አምባሳደር ላይ የተፈፀመው ግድያ ምን ዓይነት የአሜሪካ ምላሽ እንደሚያስከትል ህዝቡ እየተጠባበቀ ይገኛል። በመዲናይቱ ትሪፖሊም አልፎ አልፎ ግጭት ይታያል። ከሳምንት በፊት ተቃዋሚዎቹ የብሔራዊ ሸንጎውን ለተወሰነ ጊዜ በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል ሙከራ ማድረጋቸውም ይታወሳል። ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ተሹመው የነበሩት ሙስጠፋ አቡ ሻጉር ያቀረቡት የካቢኔ አባላት ስም ዝርዝር ይወክለናል ብለው ስለማያምኑ ለውጥ እንዲያደርጉ ሲጠይቁ ከለውጡም በኋላ ግን የሊቢያ ምክር ቤት በካቢኔው አባላት ባለመስማማቱ  አቡ ሻጉርን ባለፈው ሰኞ ከስልጣን አሰናብቷቸዋል።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አሊ አልጊቤሺ የጠ/ሚንስትሩን ከስልጣን መባረር ምክንያት

ከሙስሊም ወንድማማቾች ጋ ያላቸው ግንኙነት ሳይሆን አይቀርም ባይ  ናቸው።

« ይህ ሊሆን የቻለው በሊቢያ ፓርላማ በሙስሊም ወንድማማቾች እና በብሔራዊ ግንባር መካከል ሊቢያን ነፃ ለማውጣት ጥምረት በመመስረቱ ነው። ይህ ጥምረት ውጤተቢስ አልነበረም። እንደውም ዶክተር ሙስጠፋን ይህ ጥምረት ጫና ስላደረገባቸው ነው። ዶክተር ሙስጠፋ በሁሉም ነጥቦች አልተስማሙም ነበር። ይህም በመጨረሻ በስራ ላይ እንዳይውል አድርጎታል። »

በሊቢያ ቤንጋዚምስል Reuters

ለሊቢያ ብሔራዊ ሸንጎ ምርጫ ሲካሄድ አብዛኛውን ድምፅ ያገኙት የቀድሞ የሊቢያ ሽግግር ም/ቤት ሊቀመንበር ማህሙድ ጂብሬል ነበሩ። ጂብሬል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ የሙስሊም ወንድማማቾች ባለማይፈልጉ፤ በምርጫ 3ኛ ድምፅ የነበራቸው አቡ ሻገር ጠ/ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ነበር። እሳቸውም የሙስሊም ወንድማማቾችን የሚደግፍ ካቢኔ ለማቋቋም ነበር የሞከሩት። ለአቡ ሻጉር ከስልጣን መሰናበት ግን የጥምረቶች ሹኩቻ ብቻ አይደለም ተጠያቂው። ከስልጣን የወረዱት ጠ/ሚኒስትር በደቡብ ምስራቅ ያለውና  ራሱን እንደ ጎሳ አባል ብቻ እንጂ እንደ ሊቢያ ዜጋ የማያየው ማህበረሰብ ድጋፍ አለማግኘታቸውም ጭምር ነው። ይህ ደግሞ መላው የሊቢያን ህዝብ እንጂ ከስልጣን የወረዱትን አቡ ሻጉርን ብቻ አይደለም ችግር ላይ የሚጥለው ይላሉ ። በኖቲንግሃም ትሬንት ዮንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና የሰሜን አፍሪቃ ተንታኝ ኢማድ ኤል አኒስ « ስራቸውን በትክክል በሚፈጽሙ እና አንድን ቡድን ወክለው ለማስደሰት በሚሳተፉ ቡድኖች መካለል ትልቅ ልዩነት አለ። ይህ ነው አዳጋች የሚያደርገው። በተለይ በደቡብ የሀገሪቷ ክፍል «ሰብሃ» አካባቢ የሀገሪቷን ጎሳ፣ ቡድን እና ማህበራዊ ፍላጎት የሚወክል በዛ ላይ ደግሞ የፖለቲካ እውቀት ያለው ፖለቲካዊ የለም። ይህንን ነው ለሚቀጥሉት ወራት ሊቢያ መወጣት የሚኖርባት»

ይህንን ሀሳብ አሊ አልጊበሺም ይጋራሉ። ዋናው የፖለቲካ ብቃት ነው።

የተቃውሞ ሰልፍ በሊቢያምስል Reuters

«ለአዲሷ ዲሞክራሲያዊት ሊቢያ እንደዚህ አይነት መንግስት አይደለም የምንመኘው ። ምኞታችን ሀገሪቷን በሙሉ የሚወክል ነው። በአሁኑ ሰዓት ለሊቢያ ጠንካራ መንግስት ያስፈልጋል። ወሳኙ ውክልና ሳይሆን ችሎታና ኃላፊነት መውሰድ መቻሉ ነው።»

ይህ ካልሆነ እና ሊቢያ በመንግስት አመሰራረት ላይ ጊዜዋን የምታጠፋ ከሆነ በሀገሪቷ ሰላም የመስፈኑ ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል  ይላሉ አሊ አልጊበሺ፤

«የፀጥታው ሁኔታ በአጠቃላይ ተበላሽቷል። ሊቢያ ከጋዳፊ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ወዲህ ካለው ሁኔታ የባሰ ነው አሁን የሚታየው። በአንዳንድ የሊቢያ አካባቢዎች በተለያዩ ቡድኖች መካከል ግጭት ይነሳል። ሰዎች ይታሰራሉ፣ ይጠለፋሉ። እነዚህ ሁሉ መፍትሄ የሚፈልጉ ናቸው። ያለፈው መንግስት ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት አቅም አልነበረውም።»

አዲስ በመመስረት ላይ ያለው የሊቢያ መንግስት ለአንድ አመት በስልጣን ላይ ይቆያል። በዚህም ጊዜ አዲስ ህገ መንግስት እና ምርጫ ህግ መውጣት ይኖርበታል።

ማሊ

ካለፉት ወራት አንስቶ ሰሜን ማሊ በአክራሪ ሙስሊም ቡድን ቁጥጥር ስር ትገኛለች። በማግሬብ ያለው የአል-ቃኢዳ ቡድን እና አክራሪው ቡድን ቦኮ ሀራም ይገኙበታል። እንደ አንድ የተመድ ቃል አቀባይ ገለፃ ከሆነ አማፂ ቡድኖቹ በዘዴ የሰብዓዊ መብትን እየጣሱ ይገኛሉ። ቃል አቀባዩ እንደውም አማፂዎቹ ከወላጆች ልጆችን እየገዙ ለውትድርና እንደሚያሰለጥኑ ገልፀዋል።

ሰሜን ማሊ በአክራሪ ሙስሊም ቡድን ቁጥጥር ስር ትገኛለችምስል Reuters

 በሰሜን ማሊ ያለውን የአመፅ እንቅስቃሴ በመቃወም ባለፈዉ ሐሙስ ዕለት በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች በመዲና ባማኮ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል። ህብረተሰቡም ይሁን  መንግስት ፤ የሀገሪቱ ሠራዊት  ብቻውን እነዚህን አማፂያን  ታግሎ ሰሜን የሀገሪቱን ክፍል ማስለቀቅ  እንደማይችል ያውቁታል።  የሰልፉ አላማ ታዲያ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን አካባቢ ከአማፅያኑ ለማስለቀቅ ወታደራዊ ርምጃ እንዲወስድ ለመጠየቅ ነዉ። ሰልፈኞቹ በጠዋት መፈክር ይዘው ነው ወደ አደባባይ የወጡት። ጠቅላይ ሚኒስትር ቼክ ሞዲቦ ዲአራም ለማሊ መንግስት የውጭ ሀገራት ድጋፍ እንዲሰጡት  ጠይቀዋል።

«ግርፍያ ፣ አካል መቁረጥ፣ ግድያና  መደፈር  ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ እና ባህላዊ ሀውልቶችን ማውደምና የመሳሰሉት የሰሜን ማሊ ኗሪዎች የቀን ተቀን እጣ ፋንታ ሆኗል። የሀገሪቷን አንድነት መልሶ ለመገንባት የተመድ የፀጥታ ም/ቤትን የምንጠይቀው አለም አቀፋዊ አጥቂ ጓድ  እንዲልክልን ነው።»

አጥቂ ጓዱ 3000 ሰዎችን ያቀፈ መሆን እንደሚኖርበት ሲነገር፤ ወታደራዊ ኃይሉን አቅራቢዉም የምዕራብ አፍሪቃ የኢኮኖሚ ትብብር ማህበረሰብ በምህፃሩ ECOWAS እንደሚሆን ነው የተገለፀዉ። ይህ ሠራዊት ልምምዱን ከጀመረ ቆይቷል። የሚጠበቀዉ የፀጥታው ምክር ቤት ምላሽ ብቻ ነው። በተቃራኒዉ ግን የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪቃውያንን እቅድ እየጠበቀ ይገኛል። ፈረንሳይ በበኩሏ ግን የጦር ተልኮው ምን ሊመስል እንደሚችል አንድ የመፍትሄ ሀሳብ አውጥታለች። ይህም ሀሳብ በ30 ቀናት ጊዜ ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል። እንዲያም ሆኖ ወታደራዊ ርምጃ በሰሜን ማሊ የማካሄዱ ነገር  አጠራጣሪ እንደሆነ ነው የፈረንሳይ የሽብር ተግባር ተመራማሪ -ማቲው ጉይደሬም የጠቆሙት፤

ከሰሜን ማሊ ሸሽተው የሚሄዱምስል picture-alliance/dpa

«በሰሜን በኩል ያለዉ ሁኔታ ማሊ አጣብቂኝ ዉስጥ ከቷታትል። ሙስሊም አማፂዎቹ ዝም ቢባሉ «አፍሪቃኒስታን» ያሉትን እንዲያደራጁ እና ለአሸባሪዎች መደበቂያ እንዲመሠረት መንገድ ይከፍታል። አይ ወታደራዊ ርምጃ ይሻላል ቢባል ደግሞ ጦርነቱ የበለጠ የንፁሀን ህይወት እንዲጠፋና በአካባቢዉም ይበልጥ አለመረጋጋት እንዲሰፍን ያደርጋል።»

በዚህም የተነሳ የተመድ ዋና ፀሀፊ ባን ኪ ሙን  ግጭት ዉስጥ የተገቡት ቡድኖች እንዲደራደሩ ጥሪ ማቅረቡን መርጠዋል። ይሁንና ከሁሉም ወገኖች የሚታየዉ ፍንጭ  ወታደራዊ ርምጃን  የሚያመላክት ነዉ። ጦርነት የማይቀር ከሆነ ፈረንሳይ አስፈላጊዉን የቁሳቁስ ርዳታ እንደምታቀርብ አሳውቃለች። የአውሮፓ ህብረት ደግሞ የማሊን ወታደሮች በማሰልጠን  የሚተባበርበት ሁኔታ እንደሚኖር ነዉ የተገለፀዉ። ዮናይትድ እስቴትስም እንዲሁ ለማሊ ተፈላጊዉን ድጋፍ ትለግሳለች።  እንደ « ዋሽንግተን ፖስት» ዘገባ ከሆነ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መጠቀም ስለመቻሉ እያጣራ ይገኛል።

አላኢን አንቲል IRIS በተሰኘ የፈረንሳይ ተቋም የአፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኝ ናቸው።

« ማሊ ፤ ኤኮዋስን እና ፈረንሳይ፤ ዮናይትድ ስቴትስን ሰው አልባ አውሮፕላ በመጠቀም ሰሜን ማሊን በማስመለሱ ሂደት ላይ እንድትተባበር ቢጠይቁ፤ አሜሪካውያን በርግጠኝነት ይህን ለማድረግ ፍቃደኞች ይሆኑ ነበር። ሰው አልባ አውሮፕላኖች በአንዳንድ አካባቢዎች በህብረት የማጥቃት ችሎታ አላቸው። ሰሜን ማሊን ለማፅዳት እነዚህ ጥሩ መሳሪያዎች ናቸው።»

ይሁንና በሰው አልባ አውሮፕላኖች ድጋፍም ቢሆን አክራሪ የሙስሊም ቡድኖቹን ከሰሜን ማሊ ለማስወጣት ቀላል አይሆንም። የፈረንሳይን እጥፍ በሚያክለዉ በዚህ አካባቢው ለሸማቂዎቹ በቂ መሸሸጊያ ቦታ ይኖራልና።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW