1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሊ እና የሩሲያ ትብብር ፤ የስደተኞች ችግር በጁሀንስበርግ

ቅዳሜ፣ የካቲት 4 2015

ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ማሊ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ መስኮች እያጠናከረች ነው።ተንታኞች እንደሚሉት ግን ትብብሩ የሀገሬውን ኑሮ የሚለውጥ አይደለም ይላሉ።በሌላ በኩል የደቡብ አፍሪቃዋ ጆሀንስበርግ ከተማ በመንገድ ላይ ንግድ አዲስ ህግ አወጥታለች። ሀጉ ስደተኞችን የዕለት ጉርስ የሚያሳጣ በመሆኑ በመብት ተሟጋቾች እየተተቸ ነው።

Symbolbild Südafrika soziale Ungleichheit | Johannesburg Skyline
ምስል Graham de Lacy/Greatstock/IMAGO

ትኩረት በአፍሪቃ 11.02.2023

This browser does not support the audio element.


ሰላም ጤና ይስጥልን አድማጮች በዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት የማሊ እና የሩሲያ ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ማጠናከራቸውን እንዲሁም በደቡብ አፍሪቃ ጆሀንስበርግ ከተማ የሚገኙ ስደተኞችን ሁኔታ የሚቃኝ ይሆናል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ  በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ማሊ በቅርቡ ጉብኝት አድርገዋል። በጉብኝታቸው ከአቻቸው አብዱላዬ ዲዮፕ እና ከጊዚያዊ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ጋር ውይይት አድርገዋል። በውይይቱም የሩሲያው ከፍተኛ ዲፕሎማት ሰርጌ ላቭሮቭ በሞስኮ እና በባማኮ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት አድንቀዋል።
እንደ ወታደራዊ ባለስልጣናት ከሆነ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ማሊን ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያቸው ጊዜያቸው ነው።ጉብኝቱ  የተካሄደው ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በማሊ ውስጥ በመንግስት ሃይሎች እና ዋግነር ተብሎ በሚጠራው የሩሲያ የግል ወታደራዊ ቅጥረኛ ቡድን በተፈፀሙ የጦር እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።
 በሌላ በኩል ባለፈው አመት ሞስኮ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ  ሩሲያ በአህጉሪቷ ያላትን ሰፊ ተቀባይነት ለማስፋት ከጎርጎሮሳዊው  ከጥር  2022 ዓ/ም ጀምሮ ላቭሮቭ ወደ አፍሪካ ያደረጉት ሶስተኛው ጉዞ ነው።
ጉብኝቱ  የማሊ እና የሩሲያን  ወዳጅነት እና የሁለትዮሽ ትብብር .ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች በተለይም በመከላከያ እና በፀጥታ ላይ መሆኑን የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ተናግረዋል።  
ሚንስትሩ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ባለፈው ዓመት እና በዚህ ዓመት መጀመሪያ  ሩሲያ የጦር  መሣሪያዎችን ወደ ማሊ ልካለች።በዚህም የማሊ ብሔራዊ ጦር አሸባሪዎችን በመዋጋት ረገድ ስኬታማ ሥራዎችን ማከናወን ችሏል። ብለዋል። 
የማሊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫም ጉብኝቱን « የሽግግር መንግስት ስትራቴጂካዊ አጋርነቶችን ለማስፋት  ከወሰደው የፖለቲካ ምርጫ ጋር የሚሄድ ነው» ብሏል።
 ባለስልጣኑ አክለውም  ሀገሪቱ ከአሸባሪዎች ጋር በምታደርገው ውጊያ  ከሩሲያ ጋር በመተባበሯ  በመከላከያ እና በብሄራዊ ደህንነት ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግባለች ብለዋል።የዶቼ ቬለው በራም ፖስተሀምስ  ግን በዚህ አይማም። ምክንያቱም ከዚህ ቀደምም ሌሎቹ ሀገራት በወታደራዊ መፍትሄ ሽብርተኝነትን ማቆም አለመቻላቸውን ይገልፃል።
«ምንም ልዩነት የለውም። ፈረንሣይ፣ አውሮፓውያን እና አሜሪካውያን በዋናነት ወታደራዊ መፍትሄን ይከተሉ ነበር።ነገር ግን ወታደራዊ መፍትሄ የማይሰራ በመሆኑ በግልፅ ታይቷል። ሩሲያም የሽብርተኝነትን የሚዋጉ ሀገራትን  ለማገዝ የምትከተለው መንገድ  ከሌሎች ሀገሮች ጋር ተመሳሳይ ነው ። ለውትድርና ቅድሚያ መስጠት። እናም ልክ  ሌሎቹ ሀገሮች  እንዳልተሳካለቸው ሁሉ ሩሲያም አይሳካላትም።»በማለት ገልፀዋል። 
ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር
ከወታደራዊ እና ከመከላከያ ግንኙነት በተጨማሪ ማሊ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት በኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር እና አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ከሩሲያ ለማግኘት ትፈልጋለች። ሁለቱ ወገኖች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም  ሩሲያ "በኢኮኖሚ ፣በንግድ እና በልማት ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በሰብዓዊ እርዳታዎች ጭምር ወዳጆቿን እንደምትደግፍ ላቭሮቭ ገልፀዋል።በጎርጎሪያኑ  2020 ዓ/ም በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጡት የማሊ ወታደራዊ ሀይሎች  ከጎረቤት ሀገራት እና ከምዕራባውያን ጋር ከሀገሪቱ በምርጫ መዘግየት ጋር ተያይዞ ግንኙነታቸው ቢሻክርም፤ ከሩሲያ ቅጥረኞች ጋር በመሆን እስላማዊ አማፅያንን ለመዋጋት በሚል ፊታቸውን ወደ ሞስኮ አዙረዋል። 
ባለፈው አመት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን  እንደተናገሩት ሞስኮ ሽብርተኞችን ለማስወገድ ከማሊ ጋር ትብብሩን ለማጠናከር ቁርጠኛ ነች። በተጨማሪም ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር (93 ሚሊዮን ዩሮ) ነዳጅ፣ ማዳበሪያ እና ምግብ  እንደሚላክ ቃል ገብተዋል።
የማሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላዬ ዲዮፕ  ለጋዜጠኞች እንደተናገሩትም « በተለይ አስቸጋሪ በሆነ የዓለም ኢኮኖሚ አውድ ውስጥ ሀገሬ መሰረታዊ ፍላጎቶችን እንድታገኝ ተመራጭ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሩሲያ ፌዴሬሽን ባለስልጣናት የተወሰዱትን እርምጃዎች በሙሉ በደስታ እንቀበላለን።»ሲሉ ተደምጠዋል።
የማሊው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ይህን ይበሉ እንጅ ፤ በራም ፖስተሀምስ ግን የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎች ልክ እንደ ቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የጅኦ ፖለቲካ ጫወታ ከመጫወት እና የራሳቸውን ጥቅም ከማስጠበቅ በቀር ለህዝቡ ጠብ የሚል አንዳች ነገር የለም ይላል።
«ነገር ግን ጥሩ የጂኦፖለቲካ ጨዋታ ነው። በዚህ ጨዋታ የአፍሪካ መሪዎች፣ በጣም በጣም ጎበዝ ናቸው። እና አስደሳች ትዕይንት ይፈጥራል። ታውቃለህ  አሁን ላቭሮቭ  ጎበኘ ከዚያ ቻይናውያን ከዚያ ደግሞ  አሜሪካውያን ይመጡ ይሆናል።ነገር ግን ከራሳቸው በስተቀር  መጨረሻ ላይ ህዝቡ ይረሳ እና ምንም ለውጥ አይኖርም ማለት ነው።»ብለዋል።
የሩሲያ ድል  ከፈረንሳይ መውጣት በኋላ 
ማሊ ከሩሲያ ጋር የነበራት ወዳጅነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሀገሪቱ የቀድሞ ቅኝ ግዛት ከነበረችው ፈረንሳይ ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጡ ነው። ባለፈው አመት በሁለቱ ሀገራት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ፓሪስ ከ2013 ጀምሮ ማሊ ውስጥ የቆዩትን  ወታደሮቿን እንድታስወጣ አድርጓታል።
የምዕራባውያን መንግስታት በማሊ ውስጥ ያለው የሩሲያ የግል ወታደራዊ ቡድን የዋግነር ተሳትፎ ያሳስባቸዋል። ምክንያቱም ከሩሲያ ጎን ከዩክሬን ጦር ጋር እየተዋጋ ነው። በጥር ወር መገባደጃ ላይ የአሜሪካ ግምጃ ቤት የዋግነር ቡድንን ተሻጋሪ የወንጀል ድርጅት ብሎ ሰይሞታል። በዩክሬን ውስጥ እንዲሁም በሶሪያ ለተፈጸመ ግፍም  በአረመኔነት ይወቅሱታል። ምዕራባውያንን በቡድኑ ላይ  የሚሰነዝሩትን ይህን መሰል ትችት ግን ላቭሮቭ  አይቀበሉትም።የማሊ መንግስትም እንዲሁ።
የረጅም ጊዜ የግንኙነት ታሪክ
ማሊ እና ሩሲያ  የቆየ የግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ፤ ማሊ ነፃነቷን ካገኘች ከጎርጎሪያኑ መስከረም 22 ቀን 1960 ዓ/ም ወዲህ  በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በባህል ትብብር የመጀመሪያ ግንኙነቷን የመሰረተችው ከሩሲያ ጋር ነው።
የሞዲቦ ኬይታ (የማሊ የነጻነት አባት፣ የአርታዒ ማስታወሻ) መጽሃፍ ደራሲ የሆኑት ዳውዳ ተክቴ እንዳሉት፣ የመጨረሻዎቹ የፈረንሳይ ወታደሮች ከማሊ ከለቀቁ በኋላ፣በጎርጎሪያኑ የካቲት 21 ቀን 1961 የማሊ መንግስት የመጀመሪያውን ስምምነት ወደ ፈረመችው ሞስኮ  የልዑካን ቡድን ልኳል። በስምምነቱ መሰረት ሞስኮ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እና ተዋጊ አውሮፕላኖችን ለማሊው የመጀመሪያ  ፕሬዚደንት ሞዲቦ ኬይታ አስታጠቃለች።
የስደተኞች ዕጣ ፋንታ በጁዋንስበርግ ከተማ 
በደቡብ አፍሪቃ የጆሃንስበርግ ከተማ አብዛኛው የውጭ ሀገር ዜጎች የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መደበኛ ባልሆነ ንግድ ተሰማርተው ይገኛሉ። የከተማው አስተዳደር የውጭ ሀገር ዜጎችን ከዚህ ንግድ የሚያርቅ ህግ በማውጣቱ ብዙዎች ተጨንቀዋል። በከተማዋ በቅርቡ የፀደቀው የንግድ ፖሊሲ ሁሉም መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች ለፈቃድ እንደገና እንዲያመለክቱ የሚጠይቅ ቢሆንም፤ የፈቃዱ አሰጣጡ ከሀገር ውስጥ ጉዳይ መምሪያ እና ከፖሊስ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎችን በአብዛኛው ሰነድ አልባ ስደተኞችን ያስወግዳል። የ40 ዓመቷ የዚምባብዌ ስደተኛ ሉቺያ ሞዮ ከነዚህ መካከል አንዷ ነች። ሞዮ  ከሀገሯ ከወጣች ካለፉት ሶስት  ዓመታት ጀምሮ በጆሃንስበርግ ጎዳናዎች ላይ አትክልት በመሸጥ ትተዳደራለች።በዚህ ንግድ ምክንያት ሶስት ልጆቿን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ፣ መመገብ እና የመኖሪያ ቤት ኪራይ መክፈል ችላለች። በሌላ በኩል የከተማዋ አዲስ የንግድ ህግ ብቸኛ የገቢ ምንጫዋን ሊያቆም ነው። ከተማዋ በአሁኑ ወቅት 14,000 የንግድ ቦታዎች እንዳላት የከተማዋ ባለስልጣናት ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አዲሱ ደንብ በእግረኛ መንገድ ላይ ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ ይህንን ቁጥር በ 8,100 ለመገደብ ያለመ ነው። እንደ ሞዮ ገለጻ ፤ ይህ እንደ እሷ ላሉ  በሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች ትልቅ ውድቀት ይሆናል።
«በዚህ ምክንያት ብዙ ወንጀሎች እንደሚመጡ ይታየኛል። እናም በሂደቱ ውስጥ ብዙ ግራ መጋባት ፣ ህመም ስቃይ እና ግርግር አለ።»
የጆሃንስበርግ የከንቲባ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ንኩሉሌኮ ምቡንዱ የውጭ ሀገር ዜጎች ግምት ውስጥ የሚገቡት የስራ ቦታውን ደቡብ አፍሪካውያን የማይፈልጉት ከሆነ ብቻ ነው ብለዋል።
«መደበኛ ባልሆኑ ነጋዴዎቻች  እና ባለሱቆች የውጭ ዜጋ ወረራ ደርሶብናል። እና ደቡብ አፍሪካውያንን የመጠበቅ ሃላፊነት ያለብን ይመስለኛል። እነዚያ 8,100 የንግድ ቦታዎች በደቡብ አፍሪካውያን ይያዛሉ  ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ነገር ግን ይህንን የምንሰራው በህጉ መሰረት ነው።»ደቡብ አፍሪካዊቷ  ሲዛንዳ ሞጋሌም  ርምጃውን በክፋ አያዩትም።  
«በዚህ ላይ ምንም ስህተት አይታየኝም። በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ወደ ሌላ ሀገር ሄደህ መደበኛ ባልሆነ ንግድ የስራ ፍቃድ ማመልከት አትችልም።ያንን ከነዚህ ጥቃቅን ስራዎች ጋር እንዲታገሉ ለአካባቢው ሰዎች ብቻ  መተው ነው።»
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት  በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች ረዝም መንገድ አቋርጠው ጥገኝነት ፍለጋ ወደ ደቡብ አፍሪካ ገብተዋል። ነገር ግን የሀገሪቱ የስራ አጥነት መጠን ወደ 35 በመቶ በማደጉ መደበኛ ባልሆኑ የመንገድ ላይ ንግዶች ለመሰማራት ይገደዳሉ።ይህንን ለመስራት  ደግሞ ህጋዊ ፈቃድ ማግኘት  አይችሉም።  ሆኖም የህግ ባለሙያ እና የአፍሪካ ዳያስፖራ ፎረም ሊቀመንበር ቩሱሙዚ ሲባንዳ ለDW እንደተናገሩት የከተማዋ መተዳደሪያ ደንብ ህገ መንግስቱን የጣሰ እና በተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ላይ የተደነገገውን የጥገኝነት ጠያቂዎች እና የስደተኞችን መብትን  የሚጥስ ነው። .
«እነዚህ ሰዎች ህይወታቸውን ማስቀጠል አለባቸው። ስለዚህ የመመዝገብ ዕድሉን መንፈግ ማለት በደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሠረት በረሃብ በመቅጣት እና ሰብዓዊ ክብራቸውን እንዲያጡ ማድረግ ነው። እና በዚህ የተነሳ ሁኔታው ፈታኝ እና እጅግ በጣም ከባድ ነው ።»
ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ሕጎቹን ይተቻል።የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጄኔቪቭ ኩንታል እንዳሉት፣ የመተዳደሪያ ደንቡ፣ በጥገኝነት ጠያቂዎች፣ በስደተኞች እና በቤተሰቦቻቸው ላይ አስከፊ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
«የዚህ አይነት ህግን ማስከበር ስርዓታዊ የውጭ ዜጋ ጥላቻን የበለጠ ያጠናክራል። ይህም በቅርቡ በዲፕስሎት ላይ እንዳየነው ወደ ጥቃት የሚወስድ ነው ። በደቡብ አፍሪካ መንግስት በቂ የስራ እድል መፍጠር ስላልቻለ፤ ይህንን ስህተቱን ለመሸፈን የውጪ ዜጎችን እንደ ሰበብ  እንዲጠቀም መፍቀድ የለብንም።»በማለት ገልፀዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት  በደቡብ አፍሪካ ፀረ-የውጭነ ዜጋ ስሜት እየጨመረ መጥቷል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ስደተኞችን ወንጀል ሰርተዋል ስራዎቻችንም እየወሰዱ ነው በሚል ይወነጅሏቸዋል። ለአብነትም እንደ «ኦፕሬሽን ዱዱላ» ያሉ ቡድኖች የውጭ ሀገር ዜጎች ስራቸውን እና መደበኛ ያልሆኑ የንግድ ቦታዎቻቸውን ለደቡብ አፍሪካውያን እንዲሰጡ በመወትወት ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል የደቡብ አፍሪካ መንግስት ሰኔ 30 የዚምባብዌያን ስደተኞች በሀገሪቱ የሚቆዩበት ፈቃድ  የሚያበቃበት ቀን መሆኑን ወስኗል። ይህ ሂደት ወደ 180,000 የሚጠጉ ዚምባብዌዊያንን ይጎዳል። ደቡብ አፍሪካ እነዚህ ዚምባብዌውያን በሀገሪቱ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ፍቃድ እንዲያገኙ ለአንድ አመት ተኩል ቀነገደብ ብትሰጥም አብዛኞቹ  ፈቃዱን ለማግኘት መስፈርቱን  ማሟላት አልቻሉም። በዚህ የተነሳ የዚምባብዌ ኤምባሲ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቹን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በዝግጅት ላይ ነኝ ብሏል።በቀጣይም ደቡብ  አፍሪካ በሌሴቶ እና በሞዛምቢክ ዜጎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደምትወስድ ጠቁማለች።

ምስል Milton Maluleque/DW
ምስል SHELLEY CHRISTIANS/REUTERS
ምስል James Oatway/Getty Images
ምስል Flourish Chukwurah/DW
ምስል Annie Risemberg/AFP/Getty Images
ምስል Alexander Shcherbak/dpa/picture alliance

 

ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW