የማሊ ወጣቶች ማንን ለመምረጥ ያስባሉ?
ዓርብ፣ ሰኔ 8 2010የማሊዋ መዲና ባማኮ የሀገሪቱን ቀጣይ ፕሬዝዳንት ብቻዋን አትወስን ይሆናል። ነገር ግን ለምርጫው አስፈላጊ ቦታ መሆኗ እሙን ነው። ይህን ለመረዳት በከተማይቱ የተመዘገቡ መራጮችን ቁጥር መመልከት በቂ ነው። በባማኮ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ሰዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሲሆኑ በቀሪው የማሊ ክፍል ደግሞ ወደ አምስት ሚሊዮን ገደማ መራጭ አለ።
ማሊ በመጪው ሐምሌ 22 ለምትካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እየተዘጋጀች ነው። ከፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች መካከል አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የ73 ዓመቱ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ ይገኙበታል። የእርሳቸው ዋነኛ ተፎካካሪ የሚባሉት የ68 ዓመቱ ሶማዪላ ሲሴ ናቸው። ከተፎካካሪዎቹ መካከል ወጣቱ የሚባሉት የ45 ዓመቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሳ ማራ የመመረጥ ዕድላቸው የመነመነ ነው ተብሏል። እንደተቀረው የአፍሪካ አካባቢ ሁሉ በማሊ ወሳኝ የሚባለው የህዝብ ክፍል ወጣቱ ነው። ከማሊ ህዝብ ውስጥ ሶስት እጁ ከ35 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በመጪው ሐምሌ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ የሚሳተፉ ናቸው። ወጣቶቹ ስለቀጣዩ ምርጫ ምን ያስባሉ? ከ22 ዓመቷ የሂሳብ ሰራተኛ ማርያም ዲኮ እንጀምር።
“ገንዘብ ስለሰጠን ብቻ አንድን ዕጩ አንመርጥም። በዚህ ሀገር በርካታ ችግሮች አሉ። እነዚህ መፍትሄ ማግኘት አለባቸው። ስለዚህ ድምጽ የምንሰጠው ቃሉን ለሚጠብቅ እና ሀገሪቱን ለሚያሳድግ ዕጩ ነው” ትላለች ወጣቷ።
አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ኬይታ ለራሳቸው ተጨማሪ ስልጣን ለመስጠት በሚል ባለፈው ዓመት ሕገ መንግስቱን ለመቀየር ማቀዳቸው ችግር ፈጥሮ ነበር። በወጣቶች የተመራ እንቅስቃሴ በርካቶችን ለተቃውሞ ወደ አደባባይ በማስወጣቱም ፕሬዝዳንቱ ዕቅዳቸውን እንዲቀይሩ ተገደዋል። የዚያ እንቅስቃሴ አንድ አካል “ሪፕብሊኩን የመከላከል ስብስብ” (በእንግሊዘኛው ምህጻረ ቃል - CDR) ወደ ተሰኘ ድርጅትነት አድጓል። ድርጅቱ በማሊ ብቻ ሳይሆን የማሊ ዜጎች በሚኖሩባቸው እንደ ኮት ዲ ቯር ባሉ ሀገራት ጭምር በርካታ ተከታዮችን አፍርቷል።
“ጋኩ አብዱላኤ እባላለሁ። በኮት ዲ ቯር ያለው የCDR ድርጅት ቃል አቃባይ ነኝ። CDR ማለት ራስህን የምትገልጽበት ቦታ ነው። እንደ ወጣት የማሊ ዜጎች በራስ መተማመን አግኝተናል። አሁን የተሻለ እናውቃለን፤ ማንም ወደታች ሊጎተት እና ሊያስፈራራን አይችልም” ይላል ቃል አቃባዩ።
የCDR መሪ የሆነው ሞሃመድ ዩሱፍ በማሊ የተለያዩ አካባቢዎች ራስ ባዝ ተብሎ ነው የሚታወቀው። “ለህዝብ የኃላፊነት ቦታ መመረጥ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከዜጋው ጋር የኮንትራት ስምምነት መፈጸም አለበት። ጉዳዩ ስለዜጎች ነው። የመግስት ስልጣንን ለሚይዙ ሰዎች ስለኑሯቸው፣ የት ቦታ መሻሻል ማየት እንደሚሹ ሊነግሯቸው ይገባል” ይላል ሞሃመድ።
እነዚህ ማሻሻያዎች በየትኛውም ዘርፍ ሊሆኑ ይችላሉ። በማሊ ትምህርት ጥራቱ በጣም የወረደ ነው። የጤና አገልግሎቱም እንደዚያው ነው። በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ነው። በርካታ የማሊ ክፍሎች ለጉዞ አስጊ ተብለው ተመድበዋል። ፖለቲካውን የተቆጣጠሩቱ ላለፉት አስርት ዓመታት ከወጣቶቹም ሆነ ከአዛውንት ማሊያውያን ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል። እና ይህ መለወጥ ይኖርበታል።
ማጂክ ብላክ ሜን የተሰኘው የወጣት ሙዚቀኞች ቡድን ማሊባ በተሰኘው ዘፈን ማሊያውያን እንዲነሱ እና ሀገራቸውን እንዲገነቡ ይጠይቃሉ። ወጣቶቹ ማሊያውያንም ይህንን የሚያደርግላቸው ሰው ይፈልጋሉ። ጥያቄው “ያ ሰው ማነው?” የሚለው ነው። የ18 ዓመቷ አራባ ኬይታ በበማኮ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ናት። “ማሊን ወደፊት ሊያራምድ ለሚችል ሰው ድምጼን እሰጣለሁ። ያ ሰው ማሊን አሁን ካለችበት መጥፎ ሁኔታ የሚያወጣት መሆን አለበት ” ትላለች አራባ።
ብራም ፖስትሁመስ/ ተስፋለም ወልደየስ
አርያም ተክሌ