1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፣የጤና ባለሙያዎች፣የሕወሓት መታገድና የብሪታንያ ሕግ

ነጋሽ መሐመድ
ሐሙስ፣ ግንቦት 7 2017

አድማዉ ይደረጋል በተባለበት ዕለት አንዳድ አካባቢ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ከመንግስት ባለሥልጣናት ጋር ለመደራደር ቀጠሮ ሥለተሰጣቸዉ፣ ሌሎች ማስፈራራትና ዛቻ ደረሰን በሚል፣ ደግሞ ሌሎች በየራሳቸዉ ምክንያት አድማ አልመቱም።ጥቂት ባለሙያዎች ግን አድማ መምታታቸዉ ተዘግቧል።

ምርጫ ቦርድ ትግራይን ለረጅም ጊዜ የሚገዛዉን ፓርቲ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን ያገደዉ ከተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ በኋላ ነዉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሐገሪቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች መመሥረቻ «ደንብ አላሟላም» ያለዉን ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይን (ህወሓትን) ከፖለቲካ ፓርቲነት አግዷል።ምስል፦ Ethiopian National Election Board

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፣የጤና ባለሙያዎች፣የሕወሓት መታገድና የብሪታንያ ሕግ

This browser does not support the audio element.

ጤና ይስልኝ እንደምን አላችሁ።የዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ሳምንቱን ከተዘገቡ ጉዳዮች የበርካታ ተከታታዮችን ትኩረት በሳቡ ርዕሶች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች ስድብ፣ ዘለፋና ቧልቱን በተቻለ መጠን ነቅሰን ጥቂቱን እናሰማችኋለ,ን።የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችየጠሩት የሥራ ማቆም አድማ  መደረግ-አለመደረጉ፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የህወሓትን ከፖለቲካ ፓርቲነት ማገዱና ብሪታንያ የሰደተኖች አያያዝ ደንቧን ለመቀየር ማቀዷን የቃኙት ዘገቦች በርካታ አስተያየቶች ተሰጥቶባቸዋል።በዚሁ ቅደም ተከተል እንዳስሳቸዋለን።አብራችሁን ቆዩ።
የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎ

የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸዉና ጥቅማጥቅሞች እንደሚከበሩላቸዉ በመጠየቅ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላደረጉት ዘመቻ  «ተገቢ» ያሉትን መልስ መንግሥት ባለመስጠቱ ባለፈዉ ማክሰኞ ግንቦት 5 አጠቃላይ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ አስጠንቅቀዉ ነበር።ዕለቱ ከመድረሱ በፊት ደሴ በሚገኘዉ ቦሩ ሜዳ ሆስፒታል የሚሰሩ አራት ሐኪሞች ላጭር ጊዜና የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ማሕበር ሊቀመንበር  መታሰራቸዉ ተዘግቧል።

አድማዉ ይደረጋል በተባለበት ዕለት አንዳድ አካባቢ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ከመንግስት ባለሥልጣናት ጋር ለመደራደር ቀጠሮ ሥለተሰጣቸዉ፣ ሌሎች ማስፈራራትና ዛቻ ደረሰን በሚል፣ ደግሞ ሌሎች በየራሳቸዉ ምክንያት አድማ አልመቱም።ጥቂት ባለሙያዎች ግን አድማ መምታታቸዉ ተዘግቧል።የአድማዉ ጥሪና ቅይጡን እዉነት፣ ቅድስት ንጉሴ በፌስ ቡክ «ፍርሃት፣ ዱላውን፣  መታሰር፣ አንድ አለመሆን፣ አሺቃባጭ መኖሩ፣ ሆድ አደር መኖር፣ የተሻለ ገቢ አና ጥቅም የሚያገኙ ስላሉ---እያለች ትርዝራዋለች። 
ኢሳያስ ፋንታዬ እዮብ ግን «በሰው ህይወት ላይ አድማ መምታት ሀጢያትም ወንጀልም ነው!!!» እያለ በሶስት ቃል አጋኖ አጠናክሮ ቀጠለ «ጥበብ የእግዚአብሄር ነው የተሰጠንን ፀጋና ጥበብ ደግሞ ማገልገል ሀላፊነታችን ነው!!!ኢሳያስ ፋንታዬ እዮብ ነዉ-ይኽን ባዩ።
ጄጄ ኦን የሚል ምሕፃረ ቃል ብጤ ሥም ያለዉ አስተያየት ሰጪ ግን ኢሳያስን ይቃረናል።«መንግሥት ከህዝቡ ግብር የሚሰበስበው ህዝቡ የተሻለ ህክምና እንዲያገኝም ጭምር ስለሆነ የህክምና ባለሙያዎች የሚገባቸውን ክፍያ ያግኙ! የጤናው ሥርዓት ይሻሻል!» ብሎ። 
ታመረ አማኖ በበኩሉ፣ «ሳይበላ ለመሥራት ቃል አይገባም ።» ብሏል በፌስ ቡክ።ደሞዝ ጃጃ ዱመራ እራሱም የጤና ባለሙያ ነዉ መሰል አራት ነጥቦችን ዘርዝሯል።ሶስቱን  እንጥቀስ «እየተራብን ለመሥራት ቃል አልገባንም፣የጤና አገልግሎት የሕሊና ሥራ ነዉ።ደስተኛ ሳትሆን የምትሰጠዉ አገልግሎት ተገልጋዩንም ደስተኛ አያደርገዉ----እያለ ይቀጥላል።
ጌትነት ግርማም ረጅም አስተያየት ፅፏል-በፌስ ቡክ።ከጥያቄ መሰሉ አስተያየት ገሚሱን እነሆ፣ «የደሞዝ ጭማሬ መጠየቁ አግባብ ቢሆንም ህመምተኛ በበዛበት ሐገር፣ ታማሚዎች ላይ የሞት ቅጣት መፈፀም ሲሆን ግን በየ ጤና ጣቢያና የምንግስት ሆስፒታል ያላችሁ ----ለህሙማን ትክክለኛ ምርመራ እና ትክክለኛ መድሃኒት ሰጥታችሁ ታውቃላችሁ ???-------» ጌትነት ግርማ ነዉ-ጠያቂዉ።ለዉጥ አሰፋ አጭር ግን መፈክር ብጤ አስተያየት አስፍሯል «መንግሥት በአፋጣኝ ይመልስላቸው ጥያቄዎቻቸውን። ኮሪድሩ ይቅር??????» በአምስት የጥያቄ ምልክት ነዉ ያሳረገዉ።
ደምድመዉ ናደዉ «ጥያቄው የጤና ባለሙያ ብቻ አይደለም የመላዉ የመንግስት ሰራተኛው ነው። ተራ በተራ ሌላው እስኪነሳ መጠበቅ የለበትም -መንግስት» ደምድመዉ ናደዉ በፌስ ቡክ ያሰፈረዉ ነዉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዉሳኔና ህወሓት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ «የሐገሪቱን የፖለቲካ ፓርቲ ሕግ አላሟላም» ያለዉ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)ን ከፓርቲነት አግዷል ወይም ሠርዟል።ቦርዱ ከዚሕ ዉሳኔ ላይ የደረሰዉ ህወሓት የፖለቲካ ፓርቲነት መመዘኛዎችን እንዲያሟላ በተደጋጋሚ ካስጠነቀቃና ፓርቲዉ ለሶስት ወራት ያክል ካገደ በኋላ ነዉ።የትግራይ ክልል የረጅም ጊዜ ገዢና የቀድሞዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ግን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ የሰጠዉን ማስጠንቀቂያ ጊዚያዊ እገዳ የተቀበለዉ አይመስልም።ቦርዱ በያዝነዉ ሳምንት ያሳለፈዉ እገዳ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታታዮች ዘንድ ተቃራኒ አስተያየትና ክርክር ቀስቅሷል።
ክስመት ክስመት  የተባለ አስተያየት ሠጪ «ህውሃት ምርጫ ቦርድን አቋቋመ እንጂ፣ ምርጫ ቦርድ ህውሃትን አላቋቋመም።» ይላል። ደጄና ታይምስ ከክስመት ክስመት አስተያያየት የሚቀራረብ ሐሳብ ሰንዝሯል።እሱም በፌስ ቡክ «ትላንት፣ ዛሬ፣ ነገ የትግራይ ህዝብና ህወሓት ይኖራሉ።» ባይ ነዉ።ቶላ ዋቆ ግን የሁለቱን አስተያየት ይቃረናል።«ህዋሀት በ1960 ፓለቲካ ላይ ተቸንክሮ የቀረ ፓርቲ ነው።» አለ ቶላ ዋቆ---ቀጠለም «መረዳት መግባባት የሚባል አይገባውም።» እያለ ይቀጥላል ቶላ ዋቆ።
የሺዋስ አንደርቃም ልክ እንደ ቶላ ዋቆ ህወሓትን ይወቅሳል  «ህወሀት ጠብቦ ተነሳ። እንኳን ለሀገር ለራሱ ገደልገባ።» ብሎ።ኤፍሬም ዋለ ግን «የብልፅግና መዳኒት ህወሀት ነው» ብሏል በፌስ ቡክ።ገርዬ ፖስት የሚል የፌስ ቡክ ሥም ያለዉ አስተያየት ሰጪ ይጠይቃል «ግን ለምድነው የፈረሙት በሰምምነትሰ?  አይቋጪም እንዴ» እያለ።አሳይ አማኑ በለጠ ባንፃሩ ግን እሱም በፌስ ቡክ «የፕርቶሪያ ስምምነት የእግዚአብሔር ቃል አይደለም።» ብሏል።ኬሲ ዌብ ወንድ ይሁን ሴት እናወቅም ብቻ ፈጣሪን ትማፀናለች ወይም ይማፀናል።«ጌታ ሆይ እባክህን ይህን የፖለቲካ ጨዋታ በቶሎ አስቁምልን»
                                 የብሪታንያ አዲስ የስደተኞች ጉዳይ ደንብ
ሶስተኛዉ ርዕስ የብሪታንያ መንግሥት ሐገሪቱ እስካሁን የምትመራበትን የዉጪ ስደተኞች አቀባባል፣አያያዝና አኗኗር ደንብን ለመቀየር ማቀዱን የሚመለከት ነዉ።ግራ ዘመሙ የሠራተኛ ወይም ሌበር ፓርቲ የሚመራዉ የብሪታንያ መንግስት እንደሚለዉ የዉጪ ዜጎች ብሪታንያ ዉስጥ ለመሥራት ይሁን ለመማር ወደ ሐገሪቱ የሚገቡበት ቪዛን ጨምሮ ጠንካራ ቁጥጥር ይደረግበታል።ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር እንደሚሉት የውጭ ዜጎች ብሪታንያ ዉስጥ መኖር የሚያስችላቸዉ ፈቃድ የሚያገኙት ለፍተዉ እንጂ «መብታቸዉ» ሆኖ አይደለም።
ብሪታንያ እስካሁን ድረስ በሐገሯ ለሚኖሩ የዉጪ ዜጎች አምስት ዓመት እየሰሩ ከኖሩ ዜግነት ትሰጥ ነበር።ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ እንዳሉት ግን ከእንግዲሕ ዜግነት የሚያገኙት 10 ዓመት እየሰሩ የኖሩ ብቻ ናቸዉ።
ፉዓድ የዳኒ ልጅ በፌስ ቡክ «ዉሸት ነዉ» ባይ ነዉ።«የሰዉ ኃይል በጣም ስደተኛ ይፈልጋሉ»----ይልና  «ይህን ዜና ጀርመኖች ይሰሙና ስደተኛ ያባርራሉ» ብሎ ያስጠነቅቃል ፉዓድ የዳኒ ልጅ።ዳዊት ክንዳዬ ግን በምዕራቡ ዓለም ስደተኞችን የመጥላት አስተሳሰብና እርምጃ እየተጠናከረ መምጣቱ ያሳሰበዉ ይመስላል።ከሰጠዉ ረጅም አስተያየት ጥቂቱን እናሰማችሁ «ጎበዝ የአውሮፖም ሆነ የስሜን አሜሪካ ነጭ ዝርያ፣ ያላቸዉ የመረራቸው እለት እኛን በተለይ ጥቁሮችን ጠራርገዉ ነው የሚያስወጡን» ይላል ዳዊት ክንድያ።
ይማም ኢብራሒም  ብሪታንያን ይወቅሳል «በሰው ጉልበት እና ደም ሀገሯን ለማሳደግ ነዉ---እንደለመደችው» እያለ።ዩሪ ስጦታዉ «USA Style» ብሎታል የብሪታንያን ዕቅድ።ፃቃዬ ካስ በፌስ ቦክ ግን በእንግሊዘኛ «የማይረባ ዜና፣ ማን ይጨነቃል» ብሎታል።የብሪታንያን ዕቅድ።በሶስት ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ባጫጭሩ የዳሰስንበት የዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የእስካሁኑ ነበር።

የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር የሚመሩት መንግስት ሐገሪቱ እስካሁን የምትከተለዉን የዉጪ ስደተኞች ደንብን እንደሚቀይር ጠቅላይ ሚንስትሩ አስታዉቀዋል።ምስል፦ Ian Vogler/AP/picture alliance
የቀድሞዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድንና ትግራይን ለረጅም ዓመታት የገዘዉ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፓርቲነት መታገዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈዉ ግንቦት 7 አስታዉቋል።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW