1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፣ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ዲፕሎማትን አባረረች፣ የጉራጌ ዞን እስራት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 21 2017

ሶማሊያ የኢትዮጵያን ዲፕሎማት ከሐገሯ ማበረሯ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን በርካታ ሰዎች መታሰራቸዉና የዩናይትድ ስቴትስ የምርጫ ዝግጅትን የቃኙ ናቸዉ።በየርዕሶቹ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች ከስድብና ዘላፋ የፀዱትን መርጠናል

ከግራ ወደ ቀኝ የሶማሊያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አሕመድ ሙዓሊን ፈቂ፣ የቱርክ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሐካን ፊዳንና የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ታዬ አፅቀስላሴ
ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የወደብ ኮንትራትን የሚመለከት የመግባቢያ ሥምምነት ከተፈራረሙ ወዲሕ የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ መሪዎች የገጠሙትን ዉዝግብ ለማስወገድ ቱርክ የጀመረችዉ ሽምግልና እስካሁን ለዉጤት አልበቃም።ምስል Arda Kucukkaya/Anadolu/picture alliance

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

31 10 24

በዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችን ሳምንቱን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታታዮችን ትኩረት ከሳቡ ርዕሶች በሶስቱ ላይ የተሰጡትን አስተያየቶች ቃርመናል።ርዕሶቹ ሶማሊያ የኢትዮጵያን ዲፕሎማት ከሐገሯ ማበረሯ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን በርካታ ሰዎች መታሰራቸዉና የዩናይትድ ስቴትስ የምርጫ ዝግጅትን የቃኙ ናቸዉ።በየርዕሶቹ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች ከስድብና ዘላፋ የፀዱትን መርጠናል።

ሶማሊያ የኢትዮጵያን ዲፕሎማት ማበረሯ

የኢትዮጵያና ራስዋን የሶማሊ ላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራዉ ግዛት መሪዎች አምና ታሕሳስ የወደብ ኮንትራትን የሚመለከት የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲሕ የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክና ኢትዮጵያ የገጠሙት ዉዝግብ አሁንም እየተካረረ ነዉ።የአዲስ አበባና የሐርጌሳ መሪዎች የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር «ወረራ» ነዉ ያለችዉ ሞቃዲሾ ከቀጥታ ዉዝግብም አልፋ የግብፅና የኤርትራን ድጋፍ እያማተረች ነዉ።

የሶማሊያ መሪዎች ከዚሕ ቀደም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሶማሊያ የአየር ክልል እንዳይበር አግደዋል።ሶማሊያ የሠፈረዉ የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሠራዊትን ለማስወጣት ዝተዋል።በሞቃዲሾ የኢትዮጵያ አምባሳደርን አባርረዋልም።ሌላም ርምጃ ወስደዋልም።ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የወደብ ኮንትራትን የሚመለከት የመግባቢያ ሥምምነት ከተፈራረሙ ወዲሕ የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ መሪዎች የገጠሙትን ዉዝግብ ለማስወገድ ቱርክ የጀመረችዉ ሽምግልና እስካሁን ለዉጤት አልበቃም።በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ ደግሞ አንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ከሐገራቸዉ እንዲወጡ አዘዋል።ወይም ፐርሶናነን ግራታ (የማይፈለግ ሰዉ) ብለዋቸዋል።

ዘዉዱ መንገሻ፣ «ለሀገራችን ምንም የሚቀርባት ነገር የለም» ይላል በፌስ ቡክ «ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ሆናለች።» አከለ ዘዉዱ።እግዚአብሔር ይመስገን የሚል ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪ ግን ተቃራኒዉን ባይ ነዉ።«ኢትዮጵያ ምን ያህል በጎሮቤቶችዋ እንደ ተናቀች ያሳያል።ጎዶሎችዋን እንድታስተካክልም የሚጦቁም መልእክት ነው።»እግዚአብሔር ይመስገን ነዉ ይሕን ባዩ።

አብዱረሕማን ደጉ ምርት፣ ደግሞ «ዲፕሎማሲያዊ ክስረት ለሃገሬ ለኢትዮጲያ» ብሎታል።

(ከግራ ወደ ቀኝ) የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድና የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ።የወደም ኮንትራትን የሚመለከት የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅትምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

ደስባለኝ መንግሥተአብ አሰግድ «ኢትዮጵያ ኢንባሴዋን ዘግታ፣ መቆደሾ የሚገኘውን መከላከያ ይዛ መውጣት ከቻለች።» እርግጠኛ ነኝ በወራት ውስጥ ሱማሊያ ትፈርሳለች።» ይላል።ያምኤል ያምኤል ግን »እውነት ነዉ» አለ በፌስ ቡክ  «ኢትዮጵያ ዉስጥ ትክክለኛ መንግስት እስኪመሠረት።»

ሶሎሞን ታፈሰ ሹባና ግን «እኛ ምን ቸገረን» አለና ቀጠለ በፌስ ቡክ« ሰላም አስከባሪውን ኃይልንም ይዞ ይውጣ። ድሮውንም ከሶማሊያ ምን እናተርፋለን?» ይጠይቃል።አምላኬ የባሳ አታምጣ-የፌስ ቡክ ስም ነዉ።የፖለቲካዉ ጣጣ ያስጨነቀዉ ወይም ያስጨነቃት በሌላ መንገድ ነዉ።«ውይ! እዚህ እንዳይመጡ» ይላል ወይም ትላለች ዲፕሎማቱን መሆኑ ነዉ «እዚህ ያሉትም ጠብሰውናል።» የአምላኬ የባሳ አትምጣ አስተያየት ነዉ።

ጉራጌ ዞን በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ታሰሩ

ወደ ሁለተኛ ርዕስ እንለፍ።ጅምላ እስራት በጉራጌ ዞን።የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች «ከፋኖና ከሸኔ ጋር ግንኙነት አላችሁ» ያሏቸዉን በመቶ የሚቆጠሩ የጉራጌ ዞን ነዋሪዎችን ማሰራቸዉን ያካባቢዉ ነዋሪዎች ሰሞኑን አስታዉቀዋል።ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ባንድበኩል ታጣቂዎች፣ በሌላ በኩል የመንግሥት ኃይላት ዘመድ-ወዳጆቻቸዉን ያግታሉ።ያስራሉ።ይገድላሉም።

አሚ ሲሳይ አጭር አስተያየት ፅፏል።«የደነገጠ መንግሥት» የሚል።ሙሳ መኮንን አሕመድ ግን « ፍዬል ወድህ ቅዝምዝም ወዲያ» የሚል ምፀት አዘል ተረት አስፍሯል።እሱም በፌስ ቡክ።«ኑሮ ተወድዷል።መንግሥት አስሮ ይቀልብ» የሚለዉ ደግሞ ጌታቸዉ ጉራች ነዉ።

ቴዛ ሉሉ «አሉ፣ ከፋኖ ግንኙነት?» ይጠይቃል።ሰይድ እንድሪስ «የምን በጉራጌ በኢትዮጵያ በሁሉም ቦታ ነው።»፣ መብራቱ ከበደ፣ እንዲያዉ ሥልችት ያለዉ ይመስላል።«መቼ ነው አገር ለደቂቃዎች ሰላም ውላ ሰላም የምታድረው?» ይጠይቃል።ይቀጥላልም «መንግስት አለ ለመሆኑ?» እያለ።ደግሞ ራሱ መልሶ «መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ !!» ብሎ በሁለት ቃለ አጋኖ ምልክት አሳረገ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ዉስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የፋኖና የሸኔ ደጋፊዎች ናቸዉ ተብለዉ መታሰራቸዉን ነዋሪዎች አስታዉቀዋል።ምስል Central Ethiopia Communication Bureau

የአሜሪካ ምርጫ

ወደ መጨረሻዉ ርዕስ እንለፍ።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንታዊዉ ምርጫ።

አሜሪካኖች ትራምፕ ወይስ ሐሪስ እያሉ ነዉ።የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት በመጪዉ ማክሰኞ ለሚደረገዉ ምርጫ የሪፐብሊካኖቹ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕና  የዲሞክራቶቹ ዕጩ ካማላ ሐሪስ በተቀራራቢ ርቀት እየተፎካከሩ ነዉ።የምርጫዉ ዉጤት የዓለም ልዕለ ኃያሊቱን ሐገር ቢያንስ የ4 ዓመት መርሕ እንዴትነትን የሚወስን፣በዓለም ፖለቲካዊ ርምጃ ላይም ተፅዕኖ የሚያሳርፍ ነዉ ይባላል።

ሐናን አሕመድ ግን «ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም» ትላለች።«ሁሉም ያው ናቸው፣ ፍትህ ከአሏህ ነው። ይሄ ሁላ ህፃናትና ሴቶች በግፍ ሲገደሉ፣ ዓለም  ዝም ያሉት ሰብአዊነት ስለማይሰማቸው ነዉ።» እያለች ቀጠለችና በሌላ አባባል አሳረገች።«ከዝንብ ማር አይጠበቅም» ዳምጠዉ ታዬ ግን «እስካሁን ባለው፣  ካማላ ሀሪስ ጠንካራ አስተሳሰብ አላቸው።»

 በሌ አለ ጋሞ ባንፃሩ «ትራምፕ ይሁንና በሚገባ ያስታግሳቸዋል።» እነማንን ይሆን? ብቻ ማሪያ ምኒሊክ «ትራምፕ» አለች ባጭሩ።

አሜሪካኖች ሐሪስ ወይም ትራምፕ እያሉ ነዉ።የምርጫዉ ዉጤት የዓለም ልዕለ ኃያሊቱን ሐገር ቢያንስ የ4 ዓመት መርሕ እንዴትነትን የሚወስን፣በዓለም ፖለቲካዊ ርምጃ ላይም ተፅዕኖ የሚያሳርፍ ነዉ ይባላል።ምስል Matt Bishop/Sipa USA/Charlie Neibergall/AP/Picture Alliance

ማቲን ሳቢት ረዘም ያለ አስተያየት አስፍሯል ወይም አስፍራለች።«ሁለቱም የዘር ጭፍጨፋ አስቻዮች ናቸው :: በእርግጥ ካማላ ባይሆን እየበላችሁ፣ በየመሀሉ እረፍት እያደረጋችሁ ጨርሱዋቸው፣ ሠውስ ምን ይለናል ባይ ናቸው» የማቲን ሳቢት አስተያየት ነዉ።

በላይነሕ ታዘብኩ የዩናይትድ ስቴትስና የእስራኤልን ባዲራዎች ደርድሮ «ትራም፣ ትራምፕ፣ ትራም።» አለ ሶስት ጊዜ።መራቾቹ  አሜሪካዉያን ናቸዉ።ለዚሕም ይመስላል ሙስጠፋ ኢትዮ «እኛን በእነሱ ጉደይ ምን አገባን» ያለዉ።

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የዛሬዉ አበቃ።መልካም ጊዜ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW