የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፣ የኢትዮጵያ ክስ፣ የኤርትራና የሕወሓት መልስ፣ የጎፋ ቅሌት
ሐሙስ፣ መስከረም 29 2018
ጤና ይስጥልኝ እንደምን አላችሁ።በዚሕ ሳምንት አጋማሽ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥትና ህወሓት ኢትዮጵያን ለመዉጋት እየተዘጋጁ ነዉ ማለቱ እስከ ሳምንቱ ከነበሩት ርዕሶች ሁሉ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ መስሏል።በሁለቱ የወሎ ዞኖች የሚደረገዉ ዉጊያ ማየል የሰዎችን እንቅስቃሴ ማጎሉ ተዘግቧል።የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ደግሞ በክልሉ በሚደረገዉ ዉጊያ ምክንያት የሰዎች እገታ፣ ዘረፋና ግድያ ማየሉን ጠቅሷል።
አብን ልክ እንደ ኢትዮጵያ መንግስት ሁሉ አማራ ክልልን ለሚያዉከዉ ጦርነት ኤርትራን በንቅናቄዉ አገላለፅ ሻዕብያና ህወሓትን ተጠያቂ አድርጓል።ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጎፋ ዞን ባለሥልጣናት ለተፈናቃዮች የተዋጣ ገንዘብ አጭበርብረዉ ለመዉሰድ ሲሞክሩ ተያዙ መባሉም ጥቂቶችን «ጉድ» ሲያሰኝ ሌሎችን ግን ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ክስ፣ የኤርትራና የህወሓት ማስተባበያ
የኢትዮጵያ መንግሥት የሰነዘረዉ ወቀሳ፣ የኤርትራና የህወሓትን ማስተባበያ በሚመለከቱት ዘገቦች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች እንጀምር።
«ጦርነቱ የማይቀር ነዉ» ይላል ጥላሁን ተመስገን በፌስ ቡክ ቀጠለም «በኢትዮጵያ በኩል እንደማይጀመር እርግጠኛ ነኝ፤ኤርትራ ደግሞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከጣሰች ቆይታለች ፤ዝም ተባለ እንጅ፣----» የጥላሁን ተመስገን አስተየት ነዉ።
አሁን አሸናፊ ግን ጥያቄ ብጤ አለዉ «ሻዕቢያ እስከ አማራ ክልል ከወረረ መንግሥት አዲስአበባን ብቻ ነው እንዴ የሚጠብቅ? ህወሃትስ ቢሆን ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ነውን» ሌላም ጥያቄ አንስቷል አሁን አሸናፊ ---ሌላዉን ትተነዋል። ሰለሞን ሞክ---የሰላም ጥሪ ያደርጋል።በፌስ ቡክ።«በአፍሪቃ ቀንድ ያንዣበበውን አደገኛ ጦርነት ለማስቀረት በጋራ እንስራ''።ጩርቆ ጩሌ የሚል የፌስ ቡክ ሥም ያለዉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ለህወሓት መሪዎች ጥያቄ ቢጤ አለዉ።«ጦርነትን ለማስቀረት ከተፈለገ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንጂ ከኤርትራ ጋር መስራት ለምን አስፈለገ?»
ሐብታሙ ቤፍትታም ጥያቄ አለዉ።ግን ከሰለሞን ሞክ ለየት ያለ ጥያቄ «ህወሐት ከኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ውጭ በየት ነው ከኤርትራ ጋር መገናኘት የሚችለው?»---ነብዩ ኢድሪስም ጠያቂ ነዉ።«ከሀገር እዉቅና ዉጪ ምን አይነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ነዉ።» የሚል ጥያቄ።ብዙ ጥያቄ። ትክክለኛ መልስ ግን የለም።ብቻ አሰፋ ኢሳያስ «ጦርነትን ለማስቀረት እንስራ ይላል።በፌስ ቡክ።አስተያየቱን በሶስት ቃል አጋኖ አጅቦታል።
በአማራ ክልል የሚደረገዉ ዉጊያ መባባስ፣ የአብን መግለጫ
ወደ ሁለተኛዉ ርዕሥ አለፍን።አማራ ክልል በተለይም ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዉስጥ የመንግሥትና የፋኖ ታጣቂዎች ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት የገጠሙት ዉጊያ በሰዉ ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ከሚያደርሰዉ ጥፋት በተጨማሪ የሕዝብን እንቅስዋሴ እያጎለ፣ ነጋዴዎችንም እያከሰረ መሆኑ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በዚሕ ሳምንት ባወጣዉ መግለጫ ደግሞ በዉጊያዉ ምክንያት በክልሉ «የሰዎች እገታ፣ የዘረፋና የግድያ ወንጀሎች እየተስፋፉ ነዉ» ይላል።አብን ለጦርነቱና ለወንጀሎቹ መስፋፋት ሻዕቢያና ህወሓትን ተጠያቂ አድርጓል።
አበቡ መርሻ ማሩ----«ሲጀመር አብን ማለት ትርጉሙ ምንድን ነው።» ጠየቀች አበቡ በፌስ ቡክ ሳይተነተን ተርጉሙት። እንደኔ ፓርቲ አይመስለኝም» የአበቡ መርሻ ጥያቄ አዘል አስተያየት ነዉ።
አክሉሊሉ መንግሥትም---አብንን ይተቻል።«ምርጫ ፣ሲቃረብ ከእንቅልፋቸው ነቁ። የካድሬ ስብስብ ድርጅት» እያለ ።ዘዉዱዓለም ጌታቸዉ እሱም በፌስ ቡክ «ፓርቲውን ያሳሰባው በጦርነቱ በዋናነት የትገደሉትና የተጎዱት፣ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው አማሮች ጉዳይ ወይስ ጦርነቱን ተከትሎ እርሱ (ፓርቲዉ) የጠቀሳቸው ሁለተኛ ደረጃ ጉዳቶች ናቸው?» ታዛቢዉ ዘዉዱዓለም ጌታቸዉ ነዉ።
አሕመድ ሰዒድ ----አጭር መልዕክት አለዉ።«ዘረፋውን መደበኛ ስራ በሉት» የምትል።
የከዲጃ ሺበሺ አስተያየትም አጭር ነዉ። ግን አቤቱታ ብጤ «እረ ተቸግረናል» ትላለች ከዲጃ ሺበሺ።----ደሰድ ማኔድ የሚል የፌስ ቡክ ሥም ያለዉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ተዋጊዎችን በሙሉ ይወቅሳል።-ተረት እየጠቀሰ-«እብድ ቤቷን አቃጥላ አሁንስ በራልኝ አለች እንደሚባለው» ይላል ደሰድ ማኔድ በፌስ ቡክ« በየትኛውም ወገን ያለ ታጣቂ ፣ ዘራፍና አጥፊ ነው።» ይላል።አፄ አፄ ወልዴ «ፀልዩ» ብሎ አረፈዉ።
ለጎፋ ዞን የማጭበርበር ቅሌት ተጠያቂዉ ማነዉ?
ሰወስተኛዉ ርዕሥ ደረሰን ።በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ሻቻ ጎዝዴ ቀበሌ ሐምሌ 2016 በደረሰዉ የመሬት መደርመስ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል።በ,ሺ የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል።
ለተፈናቃዮቹ መርጃ ሐገር ዉስጥም ዉጪም የሚኖሩ ኢትዮጵያዉን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆችና ድርጅቶች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና ቁሳቁስ ለግሠዋል።በየአካባቢዉ፣ በየጊዜዉ ከሕዝብ-ለሕዝብ የሚዋጣ ገንዘብና ቁሳቁስ ብዙ ቁጥጥር ክትትል እንደማይደረግበት ሁሉ ለጎፋ ችግረኞች የተዋጣዉ የገንዘብና የቁሳቁስ ትክክለኛ መጠን፣ ለሕዝብ የደረሰዉና የተጠቃሚዉ በዝርዝርና በይፋ አልተነገረም።በቅርቡ ግን ለሕዝብ ከተዋጣዉ ገንዘብ ከ60 ሚሊዮን ብር የሚበልጠዉን ለግል ጥቅማቸዉ ለማዋል «የሞከሩ» የተባሉ ተጠርጣሪዎች ታስረዉ እየተመረመሩ መሆን ፖሊስ አስታዉቋል።
እየሱስ ክርስቶስ ያድናል፣ ይታደግማል---የሚል የፌስ ቡክ ስም የለጠፈዉ አስተያየት ሰጪ «የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዴት እስካሁን ለተጎጂዎች እርዳታውን ሳያደርሱ አስቀመጡት?» ጠየቀ። መልስም አለዉ «ምክንያቱም ሊበሉት አስበው ነበር» የሚል መልስ።
ተመስገን ተስፋዬ በበኩሉ--የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስትን ተጠያቂ ያደርጋል።«ይሄ ነገር እውነት ከሆነ ሲጀመር የፈደራል መንግሥት ተጠያቂ ነው።» እያለ ቀጠለ ተመስገን ተስፋዬ ክልሎች በኢህአዴግ ጊዜ ታፍነዉ ስለነበረ ለቀቅ እናድርጋቸው በሚል ተልካሻ አስተሳሰብ ህዝቡን ለጅቦች ትተዉታልና።» ይላል
ላንኮሞ ጉዬም እንደ ብዙዎቹ ሁሉ ጥያቄ አለዉ---ገንዘቡ እስካሁን ለሕዝብ ለምን አልተሰጠም የሚል ጥያቄ አለዉ።«ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ለተጎጂዎች ሳይደርስ ከአስራ አራት (14) ወር በላይ ባንክ ላይ ምን ሲያደርግ ቆየ?
ከበቡሽ ካንኮ----«የጎፋ መንግስት እጁ የለበትም ብለው ያምናሉ?» ጠየቀች በፌስ ቡክ።---ጎበዜ ኃይሉ ጎበዜ በፌስ ቡክ «ጠያቂም ተጠያቂም የለም።» አ,ስመላሽ ዱባለ ግን «አይ መሬት ያለ ሰዉ--» ይላል።
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫኔ